የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ኃላፊ፤ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ ማብራሪያ እንዲሰጡ ፍርድ ቤት ተጠሩ

በሃሚድ አወል

በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ ክስ ቀርቦባቸው እስካሁንም ላልተያዙ ተከሳሾች መጥሪያ ያልደረሰበትን ምክንያት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ተሰጠ። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዙን ዛሬ ሰኞ የሰጠው የፌደራል ፖሊስ በሁለት ተከታታይ ችሎቶች ተከሳሾቹን ማቅረብ ባለመቻሉ ነው። 

የተከሳሾቹን ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ-ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ በሌሉበት ለተከሰሱ ግለሰቦች የፌደራል ፖሊስ መጥሪያ በማድረስ በአካል እንዲያቀርብ የመጀመሪያውን ትዕዛዝ የሰጠው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ ነበር። በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ ክስ ከተመሰረተባቸው 58 ግለሰቦች ውስጥ የ37ቱ ጉዳይ ሲታይ የቆየው በሌሉበት ነበር። 

በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት 21 ተከሳሾች ውስጥ ስድስቱ ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ክሳቸው በመንግስት እንዲቋረጥ በመደረጉ፤ ጉዳያቸውን ችሎት ፊት በመቅረብ እየተከታተሉ ያሉት 16 ግለሰቦች ናቸው። አቶ ስብሃት ነጋ እና እህታቸው ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ የስድስት ተከሳሾች ክስ የተቋረጠው “የጤና እና እድሜ ሁኔታቸውን ከግምት በማስገባት” መሆኑን መንግስት አስታውቆ ነበር።

በዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ ከተካተቱት ስምንት የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም ተከስተ እና ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ ዛሬ ሰኞ የካቲት 28፤ 2014 በአካል በችሎት ተገኝተው የዕለቱን ውሎ ተከታትለዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎ በዋነኛነት የተመለከተው ጉዳይ፤ ያልተያዙ ተከሳሾችን በተመለከተ የፌደራል ፖሊስ የሰጠውን ምላሽ ለማድመጥ ነበር።   

የፌደራል ፖሊስ ለችሎቱ በጽሁፍ ያቀረበው ምላሽ፤ በክስ መዝገቡ የተካተቱ ሶስት ድርጅቶችን ብቻ የተመለከተ ነው። በትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) ስር የሚተዳደሩ ሶስቱ ድርጅቶች መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ እና ሱር ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበራት ናቸው። ፖሊስ የድርጅቶቹን አድራሻ ማወቅ ስላልቻለ መጥሪያ አለማድረሱን ለፍርድ ቤቱ ባስገባው በአንድ ገጽ የጽሁፍ ምላሽ አስታውቋል።

የፌደራል ፖሊስ በሁለት ተከታታይ ችሎቶች ለተከሳሽ ግለሰቦች መጥሪያ ሰጥቶ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ አለመፈጸሙ ችሎቱን አስቆጥቷል። የችሎቱ ዳኛ “ግልጽ ትዕዛዝ ነበር የሰጠነው” ሲሉ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አለመከበሩን ገልጸዋል። 

“ያልተያዙትን ተከሳሾች በተመለከተ ፖሊስ ያለው ነገር የለም” ያሉት ዳኛዋ፤ ፖሊስ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት ለተከሳሾች መጥሪያ አድርሶ ችሎት ፊት ያላቀረበበትን ምክንያት የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ በቀጣይ ቀጠሮ ችሎት ፊት ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በዛሬው ችሎት አራት ተከሳሾች በጠበቃቸው አማካኝነት በጽሁፍ አቤቱታ ቢያቀርቡም፤ ችሎቱ ይህንንም ጉዳይ በመጪው ሐሙስ መጋቢት 1፤ 2014 ለማስተናገድ ተለውጭ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱን ውሎ አጠናቅቋል።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ አቶ ጌታቸው ረዳ እና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄርን (ሞንጆሪኖ) ጨምሮ በ62 ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ክስ የመሰረተባቸው ከሰባት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ነበር። ተከሳሾቹ በሕገ መንግስትና በሕገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀልን እንዲሁም የሽብርተኝነት ድርጊቶች በመፈጸም መከሰሳቸውን ዐቃቤ ህግ አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)