በሃሚድ አወል
ከስምንት ወራት በፊት የስራ ዘመናቸውን ከጨረሱት የቀድሞ ፓርላማ አባላት መካከል 163 የሚሆኑት በመንግስት የተሰጣቸውን ቤት በሶስት ቀናት ውስጥ እንዲያስረክቡ ቀነ ገደብ ተሰጣቸው። እነዚህ የቀድሞ የፓርላማ አባላት እስከ ነገ ማክሰኞ ጠዋት የሚኖሩባቸውን ቤቶች እንዲለቅቁ ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ነው።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቤት መልቀቂያ ትዕዛዙን ለተሰናባች የፓርላማ አባላቱ ያስተላለፈው ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ የካቲት 26 በጻፈው ደብዳቤ ነው። ኮርፖሬሽኑ ደብዳቤውን የጻፈው፤ የመኖሪያ ቤቶቹን በተመለከተ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሲታይ የቆየው የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ በተደረገ ማግስት ነው።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 3ኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ባለፈው አርብ የካቲት 25 ባሳለፈው ውሳኔ፤ የቀድሞ ፓርላማ አባላት በመንግስት ከተሰጣቸው ቤት እንዲወጡ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ አጽንቷል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሰጠው 163 የቀድሞ ፓርላማ አባላት ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ነው።

በአምስት ዳኞች የተሰየመው ሰበር ሰሚ ችሎቱ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት “በጉዳዩ ላይ መልስ ሊሰጥ አይገባውም” ሲል የከፍተኛው ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ አጽንቷል። በውሳኔው ላይ የተለየ ሃሳብ እንዳላቸው የገለጹ አንድ ዳኛ የቀድሞ ፓርላማ አባላት “ ‘ጽህፈት ቤቱ ላይ ክስ ልታቀርቡ አትችሉም’ መባላቸው አግባብ አይደለም” ሲሉ የልዩነት ሃሳባቸውን አስመዝግበዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፤ በየአምስቱ አመቱ ተመርጠው ፓርላማውን ለሚቀላቀሉ አባላት የኪራይ ቤቶች ሲያዘጋጅ ቆይቷል። የፓርላማ አባላት የሚኖሩባቸውን ቤቶች ለተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በኪራይ የሚያቀርበው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ነው። የተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፤ ተሰናባች የፓርላማ አባላት “በመንግስት የተሰጣቸውን ቤት ለቅቀው እንዲወጡ” ከሁለት ወራት ገደማ በፊት ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተከትሎ፤ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አምርቷል።
የጽህፈት ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ለፍርድ ቤት አቤት ያሉት 163 የቀድሞ ፓርላማ አባላት፤ ባቋቋሙት ኮሚቴ እና በጠበቃቸው አማካኝነት በጉዳዩ ላይ ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንስቶ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲከራከሩ ቆይተዋል። ጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበለት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ በጉዳዩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምላሽ መስጠት አይጠበቅበትም የሚል ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኙት 163ቱ ተሰናባች የፓርላማ አባላት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበዋል። አቤቱታው የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የቀድሞ የፓርላማ አባላቱ በመንግስት ከተሰጣቸው ቤት እንዲወጡ በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የተላለፈው ትዕዛዝ በፍርድ ቤት ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ ታግዶ እንዲቆይ አድርጎ ነበር። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ እግዱን በማንሳት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ላስተላለፈው ውሳኔ የሰጠው አንደኛው ምክንያት፤ “የስር ፍርድ ቤትን የሚያሽር ነገር አላገኘሁም” የሚል ነበር። ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ “በመንግስት በተሰጣቸው ቤት ውስጥ ቆይተው የሚከራከሩበት የህግ መሰረት የለም” የሚለው ደግሞ ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው የጠቀሰው ሁለተኛ ምክንያት ነው።
በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ቅር የተሰኙት የቀድሞ ፓርላማ ተመራጮች፤ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ወስደውታል። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም እንደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሁሉ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የቀድሞ የፓርላማ አባላቱ ከሚኖሩባቸው ቤቶች ለቅቀው እንዲወጡ የተላለፈው ትዕዛዝ ታግዶ እንዲቆይ አድርጓል።

ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ እልባት ለመስጠት ግራ ቀኙ አለን የሚሉትን መከራከሪያ በጽሁፍ እንዲያቀርቡም ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። የተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፤ “ጥቅም እና መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለብኝ በስራ ላይ ያሉ የፓርላማ አባላትን እንጂ የተሰናበቱ አባላትን አይደለም። ኃላፊነት ያለበት የአስፈጻሚው አካል ነው” ሲል መከራከሪያውን አቅርቧል።
ተሰናባች የፓርላማ አባላት በበኩላቸው “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በስራ ላይ ያሉም ሆነ የተሰናባች ምክርቤት አባላት ጥቅማ ጥቅም የማስከበር ሃላፊነት አለበት” ብለው ተከራክረዋል። አባላቱ በጽሁፍ ባቀረቡት መከራከሪያቸው “በአዋጅ የተሰጠን መብት እና ጥቅማ ጥቅም እስኪሟላልን ድረስ በመንግስት በተሰጠን ቤት ውስጥ ልንኖርበት ይገባል” ሲሉም አክለዋል።
የቀድሞ ፓርላማ አባላት በክርክራቸው በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት አዋጅ፤ ከኃላፊነት የተነሱ የሀገርና የመንግስት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፥ የምክር ቤት አባላት እና ዳኞችን መብት እና ጥቅም ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ነው። ይህ አዋጅ ሁለት የምርጫ ዘመን ወይም ከዚያ በላይ ላገለገሉ የምክር ቤት አባላት ኪራይ እየከፈሉ የሚኖሩበት ቤት በመንግስት እንደሚዘጋጅላቸው ይደነግጋል።

ተሰናባች የፓርላማ አባላት ይህን አዋጅ ጠቅሰው በፍርድ ቤት ቢከራከሩም፤ ጉዳያቸውን ሲመረምር የቆየው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የሚጠይቁት መብት እና ጥቅም ምን እንደሆነ ለይተው አልጠቀሱም” ሲል ባለፈው አርብ ውሳኔው አመልክቷል። ለፍርድ ቤቱ በቀረበው አቤቱታ በሁለተኛ መልስ ሰጪነት የቀረበውን የተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤትን በተመለከተም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።
ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዚሁ ውሳኔው፤ ተሰናባች የፓርላማ አባላቱን በተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤቱ ላይ “ክስ ልታቀርቡ አትችሉም” ብሏቸዋል። ይህ ውሳኔ ግን በሌላ አካል ላይ ክስ ከማቅረብ እንደማያግዳቸው ጨምሮ ገልጾላቸዋል። ተሰናባች የፓርላማ አባላቱን ወክለው በፍርድ ቤት ሲከራከሩ የቆዩት ጠበቃ አቶ አንዷለም በውቀቱ፤ በአርብ ዕለት ችሎቱ ከተገኙ የአባላቱ ተወካዮች ጋር ከመከሩ በኋላ “እንደ አዲስ ስራ አስፈጻሚው ላይ ክስ እንመሰርታለን” ሲሉ ቀጣይ ሊሄዱበት ያሰቡትን ሂደት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ ሌላ ክስ ከመመስረታቸው አስቀድሞ ግን በፍርድ ቤት እግድ ምክንያት ለአንድ ወር እንዲዘገይ ተደርጎ የነበረው “የቤት ልቀቁ” ጥያቄው በድጋሚ ቀርቦላቸዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት፤ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት ማግኘቱን በመጥቀስ ለፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ባለፈው አርብ በጻፈው ደብዳቤ፤ ኮርፕሬሽኑ ቤቶቹን እንዲረከብ ጥያቄ አቅርቧል።

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽንም ይህን ጥያቄ በመንተራስ፤ የሚኖሩበትን ቤት በሶስት ቀናት ውስጥ ለቅቀው እንዲወጡ ለተሰናባች የፓርላማ አባላት በደብዳቤ ቀነ ገደብ ሰጥቷል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው በዚህ ደብዳቤ ላይ፤ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቶቹን በሚረከብበት ወቅት የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 አስተዳደር እና የገርጂ ፖሊስ ጣቢያ ትብብር እንዲያደርጉለት ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)