የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሶስት አዲስ ኤፍ ኤም ጣቢያዎች፤ ተጨማሪ አራት ወራት ተሰጣቸው

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ስርጭት ባለመጀመራቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ለነበሩ ሶስት አዲስ የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ተጨማሪ አራት ወራት ሰጠ። አንድ የሬድዮ ጣቢያ መደበኛ ስርጭቱን በተሰጠው ቀነ ገደብ በመጀመሩ፤ የተላለፈበት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተነስቶለታል። 

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ስርጭት ለመጀመር ፍቃድ ሰጥቷቸው ለነበሩ አራት ድርጅቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ከሁለት ሳምንት በፊት የካቲት 16፤ 2014 ነበር። ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ጄ ኤፍ ኤም፣ ሀበሻ ኤፍ ኤም፣ ትርታ ሬዲዮ እና ዋርካ ሬዲዮ የተሰኙ የሬድዮ ጣቢያዎችን ለመሰረቱ አራት ድርጅቶች ናቸው።

አራቱ ድርጅቶች በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በተደነገገው መሰረት ፍቃድ በወሰዱ በአንድ ዓመት ውስጥ መደበኛ ስርጭት ባለመጀመራቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በወቅቱ አስታውቆ ነበር። በድርጅቶቹ የተቋቋሙት የኤፍ ኤም የሬዲዮ ጣቢያዎች እስከ ዛሬ መጋቢት 1 ድረስ መደበኛ ስርጭት ካልጀመሩ፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ “እጅግ ውስን የሆነውን የሬድዮ ሞገድ ጨረታ አውጥቶ በማወዳደር ለሀገርና ህዝብ ጥቅም እንደሚያውል” አስጠንቅቆ ነበር።

ማስጠንቀቂያው ከተሰጣቸው ውስጥ አንዱ የሆነው እና በሟርሴ መልቲሚዲያ ኃ.የተ.የግ.ማ ስር የተመዘገበው ጄ ኤፍ ኤም 106.7 መደበኛ ስርጭት ስለጀመረ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያው እንደተነሳለት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። ጄ ኤፍ ኤም የሙከራ ስርጭቱን ላለፉት ስድስት ወራት በአየር ላይ ሲያውል ቢቆይም፤ ሙዚቃዎችን እና ማስታወቂያዎችን ብቻ ማስተላለፉ ለመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣኑ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ዳርጎታል። 

“ጄ ሬዲዮ ጣቢያ 106.7 የተሰኘው ባለፈቃድ የሬድዮ ፈቃዱን ካገኘ ጀምሮ ሙዚቃ ብቻ በማጫወት በውድድር ፈቃድ ከወሰደበት ውል ውጪ እየሰራና ውስን የሆነውን የሬድዮ ሞገድ ከታለመለት አላማ ውጪ ለብክነት እየዳረገ ይገኛል” ሲል የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በየካቲት አጋማሽ ባወጣው መግለጫው አስታውቆ ነበር። የሬድዮ ሞገድ “በውድድር የሚገኝ፣ ውድ የሀገር እና የህዝብ ሀብት” ነው የሚለው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ይህ ሞገድ “ለተፈቀደው እና ውል ለተገባበት አላማ” ይውል ዘንድ ለድርጅቱ “ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እና ማስጠንቀቂያ” ቢሰጥም የተለወጠ ነገር አለመኖሩን በመግለጫው ጠቁሞ ነበር። 

የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያው ውል በገባው መሰረት እስከ መጋቢት 1 ድረስ መደበኛ ስርጭቱን ካልጀመረ “ፈቃዱ በቀጥታ የሚሰረዝ” መሆኑን የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በየካቲት አጋማሽ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል። ጄ ኤፍ ኤም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማስጠንቀቂያውን ከሰጠ አስር ቀናት በኋላ፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 26፤ 2014 መደበኛ ስርጭት ማስተላለፍ ጀምሯል። 

በመጋቢት 2013 ዓ.ም በጸደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሰረት፤ የብሮድካስት ባለፍቃድ ፈቃድ ካወጣበት ቀን ጀምሮ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መደበኛ ስርጭቱን ያልጀመረ መሆኑ ሲረጋገጥ ፍቃዱ ሊሰረዝ እንደሚችል ተደንግጓል። ሆኖም የብሮድካስት ባለፍቃዱ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ያጋጠመው መሆኑን አመልክቶ በባለስልጣኑ ተቀባይነት ካገኘ ስርጭቱን ለመጀመር የሚያስችል ከአንድ ዓመት የማይበልጥ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደሚችል በአዋጁ ሰፍሯል።  

በዚህ ድንጋጌ መሰረት ተጨማሪ አራት ወራት ከተሰጣቸው ሶስት የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያዎች መካከል አንዱ የሆነው ትርታ ሬድዮ የስርጭት መጀመሪያ ጊዜው እንዲራዘምለት የተደረገው፤ “ባለስልጣኑ ያሰማራው ቡድን ካከናወነው ግምገማ በኋላ መሆኑን” “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መረዳት ችላለች። የሬዲዮ ጣቢያው ስቱዲዮ መገንባቱን፣ የማሰራጫ መሰረት መጣሉን፣ ቢሮ ማደራጀቱን እና የስርጭት ዕቃዎችን ማስመጣቱን ቡድኑ መመልከቱን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል። 

ስርጭት ለመጀመር የሚያስችለውን 80 በመቶ ገደማ ስራዎችን እንዳጠናቀቀ የተነገረለት ትርታ ሬዲዮ ጣቢያ ቀሪ ስራዎችን ለማገባደድ ተጨማሪ ስድስት ወራት ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፤ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ጣሪያ መሰረት የተሰጠው የጊዜ ገደን ለአራት ወራት ተራዝሞለታል። በትርታ ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ. ማህበር ስር የተመዘገበው ትርታ ሬዲዮ ፍቃድ ያገኘው በሐምሌ 2012 ዓ.ም ነው።

በተመሳሳይ ጊዜ ፍቃድ ያገኙት ዋርካ ሬዲዮ እና ሐበሻ ኤፍ ኤም ሬዲዮም፤ መደበኛ ስርጭት እንዲጀምሩ የተሰጣቸው ገደብ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሞላቸዋል። “ቢሮ ከመከራየት ውጭ ምንም አላደረጉም” የተባሉት ሁለቱ ጣቢያዎች ቀነ ገደቡ የተራዘመላቸው፤ “ያላቸውን ጊዜ ተጠቅመው ማድረግ የሚችሉት ነገር ካለ” በሚል መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከባለስልጣኑ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)