ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ በአፋር እና አማራ ክልሎች ከ700 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር እና በአማራ ክልሎች በነበረው የጦርነት ወቅት ብቻ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን በምርመራ እንደደረሰበት አስታወቀ። በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ወገኖች ደግሞ ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች በሁለቱ ክልል ስር ባሉ አካባቢዎች በሕገወጥ መንገድ መገደላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። 

ኢሰመኮ ይህን የገለጸው በአፋር እና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ጥሰቶች ከመረመረ በኋላ ዛሬ አርብ መጋቢት 2፤ 2014 ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ነው። በ153 ገጾች የተዘጋጀው ይህ ሪፖርት፤ ኮሚሽኑ ከዚህ ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ በሁለቱ አካባቢዎች ባሰማራው የሰብዓዊ መብቶች የምርመራ ቡድን የደረሰባቸውን ግኝቶች በስፋት የዘረዘረ ነው።

በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት “በአብዛኛው ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው የከተማ እና ገጠራማ አካባቢዎች መካሄዱን” የጠቀሰው የኮሚሽኑ የምርመራ ሪፖርት፤ በጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች መሞታቸውን” አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ለአካል እና ለስነ ልቦና ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸው በምርመራ ሪፖርቱ ተገልጿል። 

ኢሰመኮ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ምርመራ ባደረገባቸው ስፍራዎች፤ በጦርነቱ ወቅት ብቻ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን እና 309 ሲቪል ሰዎች ደግሞ ለቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን በምርመራ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። የኮሚሽኑን የምርመራ ሪፖርት አንኳር ጉዳዮች በንባብ ያሰሙት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የትግራይ ኃይሎች እና የመከላከያ ሰራዊት በሲቪል ሰዎች ላይ ፈጽመዋቸዋል ያሏቸውን ግድያዎች በምሳሌ ለማስረዳት በአፋር ክልል ጋሊኮማ እና በአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ የተፈጸሙ ክስተቶችን ጠቅሰዋል። 

የሰብዓዊ መብት ተቋሙ በምርመራ ሪፖርቱ ያነሳው ሌላው ጉዳይ፤ በሕገ ወጥ እና ከዳኝነት ውጭ (unlawful or extra-judicial killings) በሆነ ሁኔታ በአፋር እና አማራ ክልሎች ተፈጽመዋል ያላቸውን ግድያዎች ነው። ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው የሁለቱ ክልል አካባቢዎች፤ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ መግደላቸውን በምርመራ ሪፖርቱ ጠቅሷል። እነዚህን ግድያዎች “በዋነኝነት የፈጸሙት የትግራይ ኃይሎች ናቸው” ሲል ኮሚሽኑ ወንጅሏል።

“የትግራይ ኃይሎች ይህን መሰሉን ሕገ ወጥ ግድያ ሲፈጽሙ ምክንያት ሲያደርጉ የነበረው፤ ተጠቂዎቹን ‘ለመንግስት ኃይሎች ሰላይ ናችሁ፤ የግላችሁን የጦር መሳሪያ አምጡ፤ ንብረት እንዳይወሰድ ተከላክላችኋል፤ የመከላከያ፣ የልዩ ኃይል ወይን የፋኖ ታጣቂዎችን አግዛችኋል’ ወይም ‘የት እንዳሉ ታውቃላችሁ’ ወይም ‘የእነዚሁ አባላት የሆኑ ሰዎች ቤተሰብ ናችሁ’ በሚል [ነው]” ሲል ኢሰመኮ በምርመራ ሪፖርቱ አመልክቷል። 

የትግራይ ኃይሎች የተለያዩ አካባቢዎችን በሚቆጣጠሩባቸው ወቅት ለደረሰባቸው ጥቃት አሊያም በጥቅሉ በትግራይ ታጣቂዎች እና በትግራይ ክልል ላይ ለደረሰ ሞትና ጉዳት የበቀል ወይም አጸፋ እርምጃ ይወስዱ እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ይህንኑም “ራሳቸው ጭምር በግልጽ እየተናገሩ ብዙ ሰዎችን በጅምላ እና በነጠላ ገድለዋል” ሲል የምርመራ ሪፖርቱ ይከስሳል። 

የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች በነበሩ የመንግስት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ተመሳሳዩን ድርጊት ይፈጽሙ እንደነበር የኢሰመኮ ሪፖርት አመልክቷል። ታጣቂዎቹ በመንግስት ባለስልጣናት ሳይወሰኑ “መንግስትን ይደግፋሉ ባሏቸው ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያን ፈጽመዋል” ሲል ሪፖርቱ ወንጅሏል።  

መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ “ሕገ ወጥ እና ከዳኝነት ውጭ የሆኑ ግድያዎችን ፈጽመዋል” ሲል በሪፖርቱ የከሰሰው አማጽያንን ብቻ አይደለም። የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያዎችም፤ “የትግራይ ኃይሎች እና የኦነግ ሸኔ አባላት አሊያም ደጋፊ ናቸው” በሚል በጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ግድያዎችን ይፈጽሙ እንደነበር የኮሚሽኑ ሪፖርት ገልጿል።  

ኢሰመኮ በዚሁ የምርመራ ሪፖርቱ በአማራ እና አፋር ክልሎች በንብረት ላይ የደረሱ ጉዳቶችንም ዘርዝሯል። እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ ከሆነ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በአፋር እና አማራ ክልሎች ባሉ “ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ የመንግስት አስተዳደር ተቋማት እና በመሰረተ ልማቶች ላይ ሰፊ ዘረፋ እና ወድመት ተከስቷል።” በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለዘርፈ ብዙ ችግር መጋለጣቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በተጨማሪነት አንስቷል።

የምርመራ ሪፖርቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለተሳተፉ ኃይሎች እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ዝርዝር ምክረ ሃሳቦችን በማጠቃለያው ላይ አስፍሯል። በኢሰመኮ ከቀረቡት ምክረ ሃሳቦች መካከል የጦርነቱ ተሳታፊዎች “በአባሎቻቸው ለተፈጸሙ ጥሰቶች ኃላፊነት እንዲወስዱ” የሚጠይቀው ይገኝበታል። ኮሚሽኑ ከዚህ በተጨማሪም ተፈላሚ ወገኖች “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ፤ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ” በምክረ ሃሳቡ ጠይቋል። 

የሰብዓዊ መብት እና የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ሰዎች እንዲሁም ቡድኖችን ተጠያቂ ለማድረግ፤ “ገለልተኛ፣ ተአማኒና የሰብዓዊ መብቶች ደረጃውን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር” ኢሰመኮ በምክረ ሃሳቡ አሳስቧል። የጦርነት ተጎጂዎችን እና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎችን እና ተቋሞችን መልሶ የማቋቋም ስራም በልዩ ትኩረት እንዲከናወን ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)