የሰሜን ዕዝ ጥቃት እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት እገታን የሚያስቃኝ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው

በሃሚድ አወል

መቀመጫውን በትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ አድርጎ በነበረው የሰሜን ዕዝ የ20ኛ ክፍለ ጦር ማዘዣ ጣቢያ ላይ በጥቅምት 2013 ዓ.ም የደረሰውን ጥቃት በዝርዝር የሚያስቃኝ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው። መጽሐፉ ከክፍለ ጦሩ ማዘዣ ጣቢያ በህወሓት ኃይሎች “ታፍነው” ተወስደው የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በእገታ ያሳለፏቸውን ጊዜያት እና ገጠመኞቻቸውን ይተርካል ተብሏል።        

መጽሐፉን የጻፉት፤ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃቱ ሲፈጸም በስፍራው ላይ የነበሩ እና ከህወሓት ኃይሎች ጋር በእገታ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመዘዋወር አንድ ወር የሚጠጋ ጊዜ ያሳለፉት ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው ናቸው። ላለፉት 11 ዓመታት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከሪፖርተርነት እስከ የመሳሪያ ጥገና ባለሙያነት የሰሩት ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ የጻፉት ይህ መጽሐፍ፤ “የተካደው ሰሜን ዕዝ፤ የታፋኙ ወጥቶ አደር ማስታወሻ” የሚል ርዕስ ያለው ነው። 

መጽሐፉ በ20ኛው ክፍለ ጦር ላይ ጥቃት ከተፈጸመበት ጥቅምት 24 እስከ ታህሳስ 9፤ 2013 ባለው ጊዜ የነበሩ ሁነቶችን የሚዳስስ እንደሆነ ደራሲው ተናግረዋል። “ሰሜን ዕዝ ጥቃት ደርሶበት ከፈራረሰበት ቀን ጀምሮ ሰሜን እዝ እንደገና የህወሓትን ጥቃት አክሽፎ፤ ታፍኖ የነበረው ሰራዊት፣ ወደ ኤርትራ ወጥቶ የነበረው ሰራዊት፣ ተበታትኖ የነበረው ሰራዊት እንደገና ተቋቁሞ ሰሜን ዕዝ እንደ ዕዝ፤ ክፍለ ጦሮች እንደ ክፍለ ጦሮች እስከ ተቋቋሙበት ታህሳስ 9፤ 2013 ድረስ [ያለውን ጊዜ] ይሸፍናል” ሲሉ ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ስለ መጽሐፋቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

“አብዛኛው የመጽሐፉ ታሪክ ፍሰት የሚሄደው ከታፈነው ሰራዊት ጋር ነው። የታፈነው ሰራዊት ምን አይነት ጥቃት ደረሰበት? የታፈነው ሰራዊት የት ቦታ ተንቀሳቀሰ? ወደ የት ሄደ? እንዴት ከአፈና ሊወጣ ቻለ? የሚለውን ነው በመጽሃፌ ያካተትኩት” ሲሉ ደራሲው በመጽሐፋቸው ትኩረት ስላደረጉበት ጉዳይ አስረድተዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ታግተው ከአዲግራት እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በዕዳጋ ሐሙስ፣ አቢ አዲ፣ በተከዜ በረሃ ያሳለፏቸውን “ሀዘን፣ ለቅሶ እና ስቃይ” በመጽሃፋቸው ማስፈራቸውን ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ገልጸዋል። 

መጽሐፉን ሲጽፉ “ሚዛናዊ ለመሆን ሞክሬያለሁ” የሚሉት ደራሲው፤ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩበት ወቅት የነበሩ ሁሉንም አይነት ገጽታዎች ለማሳየት ጥረት ማድረጋቸውን ያስረዳሉ። “በወቅቱ በጎ ነገር ይኖራል ተብሎ ባይታመንም ግን እኛ ያየናቸው በጎ ነገሮች ነበሩ” የሚሉት ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ፤ “ስጽፍ በተቻለኝ መጠን ክላሽ ይዤ ከምዋጋበት መንፈስ ለመውጣት ሞክሬያለሁ። ወታደር ሆኜ ክላሽ ይዤ በምዋጋበት ስሜት ልጻፍ ካልኩኝ ሙሉ በሙሉ ሊሆን የሚችለው አንድ ጽንፍ የያዘ ነው” ሲሉ መጽሐፋቸው ተቃራኒ መልኮችን ጭምር የሚያሳይ እንደሆነ አብራርተዋል።

የእነዚህ ተቃራኒ መልኮች ሁኔታ መጽሐፉ በተጻፈበት አውድ ጭምር ተንጸባርቋል። ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ለአሁኑ መጽሐፍ ግብዓት የሆኑ የራሳቸውን እና የጓዶቻቸውን ማስታወሻዎችን ይመዝግቡ የነበረው፤ በህወሓት ኃይሎች ስር በነበሩበት ወቅት ደብቀው በያዙት የሞባይል ስልክ ነበር። ደራሲው፤ ማስታወሻ መጻፊያ ያለውን ዘመናዊውን የሞባይል ስልካቸውን ከአጋቾቻቸው አይን የሰወሩት የልብስ መያዣ ሻንጣቸውን ውስጠኛ ክፍል ቀድደው በመደበቅ እንደሆነ ይናገራሉ። 

እርሳቸው እና ሌሎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአቢ አዲ መምህራን ኮሌጅ ታስረው በነበረበት ጊዜ፤ በየዕለቱ ለሊት ያሳለፉትን ቀን ውሎ በማስታወሻ መልክ በሞባይል ስልካቸው ይመዝግቡ እንደነበር ደራሲው ይገልጻሉ። ይህችን ታሪካዊ የሞባይል ስልክ እርሳቸው እና ጓዶቻቸው ለአራት ጊዜያት ያህል ከህወሓት ኃይሎች ፍተሻ እንዳስጣሏትም መለስ ብለው ያስታውሳሉ። “አንድ ሰው እንኳን ተርፎ ቢወጣ ይኼንን ታሪክ፣ ይኼንን የደረሰብንን ነገር ይዞ ቢሄድ ብለን [እንነጋገር] ነበር” ሲሉም በታጋቾቹ ዘንድ ማስታወሻውን ለማድረስ የነበረውን ፍላጎት ያስረዳሉ።   

የመጽሃፍ ቅርጽ እስካያዘበት ጊዜ ድረስ አብዛኛው ረቂቁ በሞባይል ስልክ የተጻፈው “የተካደው ሰሜን ዕዝ፤ የታፋኙ ወጥቶ አደር ማስታወሻ”፤ የህወሓት ኃይሎች ዘጠኝ  ሺህ ገደማ የሰራዊቱን አባላት በተከዜ በረሃ “ከለቀቋቸው” በኋላ ያለውን ጊዜም በተወሰነ መጠን ዳስሷል። የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ከእገታ ነጻ ከወጡ በኋላ በአማራ ክልል ወደምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማ ያደረጉትን መሰባሰብ እና ከዚያ በኋላ እንደገና ተመልሰው ወደ ትግራይ ክልል ሲገቡ ያጋጠሟቸው ክስተቶች በመጽሐፉ ተተርከዋል።

በመጪው ሳምንት በሶስት መቶ ብር ዋጋ ገበያ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው ይኸው መጽሐፍ፤ ከሰሜን ዕዝ ጥቃት በፊት የነበሩ ሁኔታዎችን እንዲሁም በመከላከያ ሰራዊት እና በህወሓት ውስጥ የሚታዩ ምልክቶች እንዴት ያሉ እንደነበር ምልከታዎችን ያጋራል። ደራሲው በዚህ ጉዳይ ላይ ለከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች መጠይቆችን አዘጋጅተው መረጃ መሰብሰባቸውንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የየራሳቸው ንዑስ ርዕሶች ያሏቸው አስር ምዕራፎችን የያዘው የሃምሳ አለቃ ጋሻዬ መጽሐፍ፤ ታሪኩን ለአንባቢን የሚያደርሰው በአንደኛ መደብ ትረካ ስልት ነው። ከሳምንት በፊት  ወደ ማተሚያ ቤት የገባው ይህ መጽሐፍ፤ ለዘጠኝ ወራት ያህል አርትኦት ሲደረግበት ቆይቷል። በ600 ገደማ ገጾች የተዘጋጀውን የመጽሃፉን የመጀመሪያ ረቂቅ፤ አሁን ለንባብ በሚበቃበት 393 ገጾች እንዲጠናቀቅ ማድረግ ፈታኙ ስራ እንደነበር ደራሲው ይናገራሉ።

በቀጣዩ ሳምንት ከአንባቢያን እጅ የሚገባው የመጽሐፉ የመጀመሪያ ቅጽ መሆኑን የሚናገሩት ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ፤ በመጽሐፉ ቀጣይ ቅጽ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የነበራቸውን ተሳትፎ ለአንባቢያን የማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል። የመከላከያ ሰራዊትን በምልምል ወታደርነት ከመቀላቀላቸው በፊት ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት እርባታ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ፤ ከዚህ ቀደም ሁለት መጽሐፍትን ጽፈዋል።

የደራሲው የመጀመሪያ መጽሐፍ “ውሸታም” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን የግጥም መድብል ነው። ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 የታተመው ይህ መጽሐፍ በውስጡ 56 ግጥሞችን ይዟል። ደራሲው ከሁለት ዓመት በፊት መጋቢት 2012 ለንባብ ያበቁት “ኢትዮጵያ ትሙት” የተሰኘው መጽሐፋቸው ልብ ወለድ ቢሆንም ጭብጡን ያደረገው በውትድርና ህይወት ላይ ነው። መጽሐፉ ከ2010 በፊት “በሰራዊቱ ውስጥ የነበረውን ብልሹ አሰራር” በልብ ወለድ መልክ ያጋለጠ መሆኑን ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ተናግረዋል።

ከዩኒቨርስቲ ቆይታ በኋላ በመድፍ ተኳሽነት ለማገልገል ወደ መከላከያ ሰራዊት የገቡት ደራሲው፤ መጀመሪያ የተመደቡት በሰሜን ዕዝ 24ኛ ክፍለ ጦር ነበር። ከሁለት ዓመታት የመድፍ ተኳሽነት በኋላ ወደ ምዕራብ ዕዝ ተዘዋውረው በሰራዊቱ ሪፖርተርነት ሰርተዋል። ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ነሐሴ 2012 ከመከላከያ ኮሌጅ በጦር መሳሪያ ጥገና ዲፕሎማቸውን ካገኙ በኋላ በሰሜን ዕዝ 20ኛ ክፍለ ጦር የጦር መሳሪያ ጥገና ክፍል ተመድበው በሚሰሩበት ወቅት ለመጽሐፋቸው መነሻ የሆናቸው ጥቃት ገጥሟቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በጦር መሳሪያ ጥገና ክፍል ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙት ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ አዲሱን መጽሐፋቸውን የጻፉበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “አነሰም በዛም ታሪካችንን መጻፍ አለብን በምንችለው አቅም። እኔ የደረሰብኝ፤ ጓዶቼ ያለፉበት እንዲረሳ አልፈልግም፤ በፍጹም” ይላሉ።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)