ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገዢው ፓርቲን እንዲመሩ በድጋሚ ተመረጡ

በተስፋለም ወልደየስ

ገዢው የብልጽግና ፓርቲን ከምስረታው ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፓርቲውን እንዲመሩ በድጋሚ ተመረጡ። ፓርቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ላደረገው ሁለት ምክትል ፕሬዝዳትነት ቦታዎች፤ ደመቀ መኮንን እና አደም ፋራህ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ተመርጠዋል።

ፓርቲው ከፍተኛ አመራሮቹን የመረጠው፤ በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ በሚገኘው አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው። በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው የፓርቲው የአመራሮች ምርጫ፤ 1,564 የጉባኤው ተሳታፊዎች ድምጽ የሰጡ ሲሆን 28 የፓርቲው አባላት ድምጽ ሳይሰጡ ቀርተዋል። ድምጽ ከሰጡት የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ስልሳ ዘጠኙ ድምጻቸው “ዋጋ አልባ” ሆኗል።  

ብልጽግና ፓርቲን በፕሬዝዳትነት እና በምክትል ፕሬዝዳትነት እንዲመሩ በዕጩነት የተጠቆሙት አራት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ነበሩ። በክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች የተጠቆሙት አራቱ ዕጩዎቹ፤ አብይ አህመድ፣ ተመስገን ጥሩነህ፣ አደም ፋራህ እና ደመቀ መኮንን ናቸው።   

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ዳሌሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በእጩነት ጠቁመዋል። በሁለተኛ ደረጃ የተጠቆሙትን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህን የጠቆሙት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ናቸው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በተራቸው የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ የቆዩትን አቶ አደም ፋራህን በእጩነት ጠቁመዋል። አቶ አዳሂስ አፍጌ የተባሉ የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፤ የአቶ አደምን በእጩነት መጠቆም ተቃውመው ነበር። 

“አቶ አደም እጩ ሆኖ መቅረብ የለበትም። አደም በአፋር እና በሶማሌ አካባቢ፤ በተለይም በኢሳ እና በአፋር ግጭት ላይ በቀጥታ እጅ ያለው ሰው በመሆኑ፤ ይህን ግዙፍ ፓርቲ ምክትል ሆኖ መምራት ስለማይችል በራሴ በኩል እቃወማለሁ” ብለዋል። ይሁንና ከጉባኤው ተሳታፊዎች ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆኑቱ፤ የአቶ አደምን እጩነት በመደገፋቸው ለምርጫ ቀርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ደርበው በመስራት ላይ የሚገኙትን አቶ ደመቀ መኮንንን በእጩነት ጠቁመዋል። የደመቀን በዕጩነት መቅረብ፤ ጉባኤውን በመምራት ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደግፈው ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

“አቶ ደመቀ ካሉት እጅግ አስደማሚ ባህሪዎች አንዱ ነገሮችን በእርጋታ፤ በጥሞና የማየት ብቃቱ ነው። አብሬ በሰራሁባቸው አራት አመታት የደመቀ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አቶ ደመቀን አሞግሰዋል። 

በፓርቲው አሰራር መሰረት፤ የጉባኤው ተሳታፊዎች በእጩነት ከቀረቡ አራት ግለሰቦች መካከል ለፕሬዝዳንት እና ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ብቻ ድምጽ የመስጠት ዕድል አላቸው። የፓርቲው ፕሬዝዳትነት ለመምረጥ ድምጽ ከሰጡ የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ 1,480 ድምጽ አግኝተዋል። አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ለፕሬዝዳንትነት ሁለት ድምጽ አግኝተዋል። 

ለምክትል ፕሬዝዳትነት ከተጠቆሙት ሶስት ዕጩዎች መካከል ከፍተኛውን ድምጽ በማግኘት ቀዳሚ የሆኑት አቶ አደም ፋራህ ሲሆኑ 1,330 ድምጽ አግኝተዋል። ከጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ውስጥ የ970ዎቹን ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ  ያገኙት አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው። አቶ ተመስገን ጥሩነህ 509 ድምጽ በማግኘታቸው ለምክትል ፕሬዝዳንትነት ሳይመረጡ ቀርተዋል።

ከምርጫው በኋላ ለጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች መልዕክት እንዲያስተላለፉ ዕድል የተሰጣቸው አቶ ደመቀ፤ ከስልጣን የመልቀቅ ፍላጎት እንደነበራቸው ተናግረዋል። በፖለቲካ አመራርነት ለ30 ዓመታት መስራታቸውን ያስታወሱት አቶ ደመቀ፤ “እኔ በውስጤ ይበቃኛል የሚለው ፍላጎት በጣም ገዢ ነው” ሲሉ “አሰናብቱኝ” የሚል ጥያቄ ለፓርቲያቸው ሊያቀርቡ በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል።

“ጉባኤው ከፈቀደ፤ ፈጣሪ በሚያውለን፤ የአቅሜን፣ የልቤን፣ የነበረውን ዊዝደም፤ ወደ በለጠ እና ወደ ተሟላ ይህን አገር ለማሻገር ኃላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ሲሉ አቶ ደመቀ ለጉባኤው ታዳሚዎች ተናግረዋል። የብልጽግና ፓርቲ አዲሱ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው፤ “ታላቅ” ላሉት ኃላፊነት ጠቅላላ ጉባኤው ስለመረጣቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት እና ለመትጋትም ቃል ገብተዋል።  

“ኢትዮጵያዊ ሆኜ ሁላችሁን በታማኝነት ሳላዳላ ማገልገል እንድችል፣ ጊዜ እና ሁኔታ ወደዚህ ወደዚያ እንዳይወስደኝ፣ በጨዋነት በትጋት ማገልገል ስለምፈልግ ጸልዩልኝ”

አብይ አህመድ – የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከፓርቲያቸው የአመራር ምርጫ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች እንድትጸልዩልኝ እፈልጋለሁ” የሚል ተማጽኖ አቅርበዋል። “ኢትዮጵያዊ ሆኜ ሁላችሁን በታማኝነት ሳላዳላ ማገልገል እንድችል፣ ጊዜ እና ሁኔታ ወደዚህ ወደዚያ እንዳይወስደኝ፣ በጨዋነት በትጋት ማገልገል ስለምፈልግ ጸልዩልኝ” ሲሉ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለዋል]