የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፤ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቅርንጫፍ በየሁለት ዓመቱ የሚሰጠውን የሰብዓዊ መብት ሽልማት አሸነፈ። ሽልማቱ “እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ለሚሰሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች” የሚሰጥ ሲሆን አስር ሺህ ዩሮ የገንዘብ ስጦታን ያካተተ ነው።
መቀመጫውን በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ያደረገው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቅርንጫፍ፤ የ2022 የሰብዓዊ መብቶች ሽልማት ለኢሰመጉ እንደሚያበረክት ይፋ ያደረገው ዛሬ ሰኞ መጋቢት 5፤ 2014 ነው። ገለልተኛው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፤ ከ30 ዓመታት በላይ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ድምጹን ሲያሰማ እንደቆየ የአምነስቲ የጀርመን ቅርንጫፍ ሽልማቱን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ጠቅሷል።
የኢሰመጉ ሰራተኞች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንደሚመረምሩ፣ በደል ለተፈጸመባቸው የህግ ምክር እንደሚያቀርቡ እና በሰብዓዊ መብቶች ትምህርት ዘርፍ እንደሚሳተፉ አምነስቲ በመግለጫው በማሳያነት አንስቷል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቅርንጫፍ ዋና ጸሀፊ ማርኩስ ቤኮ ኢሰመጉን የገለጹት በኢትዮጵያ “የማይደመጡ ወገኖች ድምጽ” ሲሉ ነው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ደጋፊዎች በሚያከናውኗቸው ስራዎች ምክንያት ስድብ፣ እስራት፣ ግርፊያ እና ግድያ ጭምር እንደገጠማቸው የገለጹት ዋና ጸሀፊው፤ ይህም ሆኖ ኢሰመጉ በተግዳሮቶቹ ምክንያት ሳያፈገፍግ ስራውን ሲያከናውን በመቆየቱ ለሽልማት መብቃቱን ጠቅሰዋል። የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ “ይህን ሽልማት መቀበል እና እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ካሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ጋር መስራት ለእኛ እጅጉን ጠቃሚ ነው” ብለዋል።
“በኢትዮጵያ መንግስት እና ፖለቲከኞች የሕዝቡን በርካታ ድምጾች በብዙ መንገዶች ያፍናሉ። እነዚህ ድምጾች የሚገባቸውን ትኩረት እያገኙ አይደለም። ለ33 አመታት ኢሰመጉ ያለ ማቋረጥ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ላደረጋቸው ጥረቶች እውቅና የሰጠው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰብዓዊ መብቶች ሽልማት እነዚህ ድምጾች እንዲሰሙ ያግዛል” ሲሉ የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር የሽልማቱን ፋይዳ አብራርተዋል። “በእኛ ላይ አንዳች ነገር ቢደርስ ሌሎች ድምጻቸውን በማሰማት በአጋርነት ከእኛ ጎን እንደሚቆሙ አሁን አውቀናል” ሲሉም አክለዋል።
በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ እና በመሰነድ የሚታወቀው ኢሰመጉ፤ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ ባረፉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አማካኝነት የተመሰረተ ተቋም ነው። በ1984 የተመሰረተው ኢሰመጉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መንግስታዊ ያልሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ነው። ተቋሙ የቆመለት ዋነኛ ዓላማ የዲሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብት መከበር መሆኑን ይገልጻል።
በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በጥቅምት 2013 የተቀሰቀሰው ውጊያ የኢሰመጉን ስራ ይበልጥ “አስፈላጊ” እንደሚያደርገው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጀርመን ቅርንጫፍ አስታውቋል። ኢሰመጉን ጨምሮ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ እንዲፈቀድላቸውም ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም ጥሪ አቅርቧል።
ከዚህ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት፤ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን መብት እንዲጠብቅ፣ ሃሳባቸውን የመግለጽ ነጻነታቸውን እና የፕሬስ ነጻነትን እንዲያከብር፣ የጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን በዘፈቀደ ከማሰር እንዲያቆም እንዲሁም በፖለቲካ እና በብሔራቸው ምክንያት የታሰሩትን እንዲፈታ አምነስቲ የኢሰመጉን ሽልማት ይፋ ባደረገበት መግለጫው ጠይቋል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽል የጀርመን ቅርንጫፍ የሚሰጠው ሽልማት፤ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚሰሩ ግለሰቦችን ቁርጠኝነት እውቅና የሚሰጥ ሲሆን የተሸላሚዎችን ስራ የመደገፍ እና የማስተዋወቅ ዓላማም አለው። ይህን ሽልማት ከሁለት ዓመት በፊት ያሸነፉት ከሜድትራኒያን ባህር ላይ 14 ሺህ በላይ ሰዎችን የታደገው ዩቬንታ የተባለ የነፍስ አድን መርከብ ሰራተኞች ናቸው።
መቀመጫውን በካይሮ ያደረገው ናዲም የሁከት እና ስቅየት ሰለባዎች ማገገሚያ ማዕከል የተባለ የግብጽ ድርጅት እና ካሚሮናዊቷ ጠበቃ አሊስ ናኮም ሽልማቱን ካሸነፉ መካከል ናቸው። ኢትዮጵያዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የተበረከተለትን ሽልማት በይፋ የሚረከበው በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን በሚገኘው ማክሲም ጎርኪ ቴአትር በሚካሄድ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ይሆናል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ ይገኛሉ ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)