ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን ከሁለት ሳምንት በኋላ ሊያካሄድ ነው

በሃሚድ አወል

ተቃዋሚው ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ከምስረታው በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከሁለት ሳምንት በኋላ ሊያካሄድ ነው። ፓርቲው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ የሚያሻሽል ሲሆን አዳዲስ የማዕከላዊ እና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ይመርጣል። 

ፓርቲውን “ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻግረዋል” የተባለለት ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄደው መጋቢት 18፤ 2014 መሆኑን ነእፓ አስታውቋል። ነእፓ ጠቅላላ ጉባኤውን የጠራው፤ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ የማካሄድ “ግዴታውን ለማሟላት” መሆኑን የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑር ወለላ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የሰጠውን ቀነ ገደብ ለማስፈጸም፤ ነእፓ ጉባኤውን በዚህ ጊዜ ለማካሄድ ከውሳኔ ላይ መድረሱን አቶ ኑር ገልጸዋል። ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ የካቲት 9 ባወጣው መግለጫ፤ ነእፓን ጨምሮ 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ ቀነ ገደብ መስጠቱ ይታወሳል።

የምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ አራት ቀናት ቢቀሩትም፤ ማሳሰቢያው ከተሰጣቸው ፓርቲዎች ውስጥ በጊዜ ገደቡ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረጉት በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀሰው የህዳሴ ፓርቲ እና ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ብቻ ናቸው። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላላ ጉባኤውን በዚህ ሳምንት መጨረሻ መጋቢት 11 እንደሚያካሄድ ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር።  

ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው የነእፓ ጠቅላላ ጉባኤ 550 ገደማ የፓርቲው አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የጉባኤው “ዋነኛ አጀንዳ” ከሆኑት ውስጥ የፓርቲውን የማዕከላዊ እና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መምረጥ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ኑር፤ ይህም የሚደረገው በሚሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተመስርቶ መሆኑን አመልክተዋል። 

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የሚሻሻለው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ፤ የፓርቲውን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስያሜ ወደ ብሔራዊ ምክር ቤት የሚቀይረው ሲሆን የማዕከላዊ እና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ቁጥርም ከፍ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የነእፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አስረድተዋል። በዚህም መሰረት 50 የነበረው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥር ወደ 60 ያድጋል። 

ከእነዚህ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል አርባ አምስቱ ቋሚ ሲሆኑ ቀሪዎቹ አስራ አምስቱ ደግሞ ተጠባባቂ አባላት ይሆናሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቁጥርም ከ11 ወደ 15 ከፍ እንደሚል አቶ ኑር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ነእፓ ይህን ተግባራዊ ያደረገው “ከፓርቲው ስፋት አንጻር” ማስተካከያ ማድረግ በማስፈለጉ መሆኑን የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አስረድተዋል። “ብዙ አቅም ያላቸው ሰዎች ወደ ፓርቲው ተቀላቅለዋል” የሚሉት የጽህፈት ቤት ኃላፊው፤ መጪው ጠቅላላ ጉባኤ እነዚህን አባላት “መደበኛ የፓርቲው አመራር ማድረጊያም ጭምር ነው” ሲሉ ከጉባኤው በኋላ ፓርቲው አዳዲስ አመራሮች እንደሚኖሩት ጠቁመዋል።

ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የምስረታ ጉባኤውን ያካሄደው ከሶስት ዓመት በፊት መጋቢት 15፤ 2011 ነበር። ፓርቲው ከተመሰረተ ስድስት ወራት በኋላ፤ በመስከረም 2012 ከብሔራዊው ምርጫ ቦርድ የእውቅና የምስክር ወረቀት አግኝቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)