በኤደን ገብረእግዚአብሄር
በጅማ ከተማ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ለሊት በተከሰተው ከፍተኛ የእሳት አደጋ ከ45 እስከ 50 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ንብረት መውደሙን የጅማ ፖሊስ መምሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በእሳት አደጋው በ16 የንግድ መደብሮች ላይ ሙሉ በሙሉ መውደማቸው እና በ9 መደብሮች ላይ ደግሞ ከፊል ውድመት መድረሱን የጽህፈት ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን እና ሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አውጋቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ማክሰኞ መጋቢት 6 ለሊት በጅማ ከተማ በህምረታ መርካቶ ቀበሌ በቢሽሼ አካባቢ የተከሰተው የእሳት አደጋ መንስኤ እስካሁን አለመረጋገጡን የተናገሩት ኢንፔክተር ገዛኸኝ፤ ሆኖም በመደብሮቹ ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ ከአንድ ሱቅ ጭስ ከታየ በኋላ እሳቱ ወደ ሌሎች ሱቆች መስፋፋቱን መናገራቸውን ገልጸዋል። በፎረንሲክ ባለሙያዎች የተደገፈው የፖሊስ ምርመራ አሁንም ዛሬም ጭምር መቀጠሉን አክለዋል።
የእሳት አደጋው ከተቀሰቀሰ በኋላ ከለሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ በስፍራው የተገኙት አቶ አደም የሱፍ የተባሉ የጅማ ከተማ ነዋሪ፤ ከወደሙት ሱቆች ውስጥ ከፊሉ የልብስ ሱቆች መሆናቸውን እንደተመለከቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የተወሰኑቱ ሱቆች የሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫዎች መሆናቸውን የገለጹት የዓይን እማኙ፤ ቀሪዎቹ የህንፃ መሳሪያ መደብሮች እና መጋዝኖች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በጅማ ከተማ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ከትላንት በስቲያ እኩለ ለሊት ገደማ ከተቀሰቀሰ በኋላ ለሁለት ሰዓታት ያህል የቆየ መሆኑን የጅማ ከተማ ወረዳ 1 ፖሊስ የመረጃ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን ሄኖክ ቃለአብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች በተጨማሪ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የጸጥታ ኃይሎች ቃጠሎውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።
የእሳት አደጋውን በመከላከል ተሳትፎ ካደረጉ የጅማ ከተማ ተቋማት መካከል የጅማ አባ ጅፋር ኤርፖርት ይገኝበታል። የኤርፖርቱ ስራ አስኪያጅ አቶ በቃሉ ውለታው፤ የተቋማቸው የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሽከርካሪ በሶስት ጊዜ ምልልስ 18 ሺህ ሊትር ውሃ በመጠቀም የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)