በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሞከሩ 20 ሰዎች ቀላል ጉዳት ደረሰባቸው

በሃሚድ አወል

በአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ፤ ትላንት ሐሙስ መጋቢት 8 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሞከሩ 20 ሰዎች የጸጥታ ኃይሎች ባደረሱባቸው ድብደባ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው የሰልፉ አስተባባሪዎች ገለጹ። አምስት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም በከተማይቱ ፖሊስ መታሰራቸውን አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል። የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዑመር ሃለቶ “የተጎዳም ሆነ የታሰረ ሰው የለም” ሲሉ አስተባብለዋል።

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የሰልፉ አስተባባሪ፤ በሰመራ ከተማ ትላንት ሐሙስ ጠዋት ሊደረግ ታስቦ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውቋል። “ጁንታውን የሚቃወም እና የፌደራል መንግስት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ መግባት አለበት የሚል ነበር” ሲል አስተባባሪው የሰላማዊ ሰልፉን ዓላማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድቷል።

በተመሳሳይ ማንነቱ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ሌላ የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪም፤ ሰልፉ በአፋር ክልል “በህወሓት ኃይሎች እየተፈጸመ ነው” ያለው “ወረራ”፤ ትኩረት እንዲሰጠው የሚጠይቅ እንደሆነ ገልጿል። “የአፋር ህዝብ እና ሚሊሺያ ብቻውን ነው እየተዋጋ ያለው” የሚለው አስተባባሪው፤ የፌደራል መንግስት ወረራውን ለመቀልበስ ድጋፍ ከመስጠት ተቆጥቧል ሲል ወንጅሏል።

ሰላማዊ ሰልፉ ሰመራ ከተማ ከሚገኘው የብሔር ብሔረሰቦች አዳራሽ በመነሳት መዳረሻውን በከተማይቱ ስቴድየም እንዲያደርግ ታስቦ እንደነበር የሰልፉ አስተባባሪ የሆነው የዩኒቨርስቲ መምህር ይገልጻል። ነገር ግን የክልሉ ልዩ ኃይል እና የከተማይቱ የፖሊስ አባላት፤ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ወደ መነሻ ቦታው ሳይደርሱ እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ተናግሯል። የጸጥታ ኃይሎቹ ሰልፈኞቹን ለመመለስ ኃይል ተጠቅመዋል ሲል የዩኒቨርስቲ መምህሩ ከስሷል።

ቀድመው የሰላማዊ ሰልፉ መነሻ ቦታ የደረሱት ሰልፈኞችም በጸጥታ ኃይሎች ድብደባ እንደተፈጸመባቸው አስተባባሪዎቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሰመራ ከተማ ነዋሪ የሆነው አስተባባሪ፤ “ቀጥታ ወደ ድብደባ ነው የገቡት። ሰልፉ ላይ የነበሩ እና ያልነበሩትንም መደብደብ ነው የጀመሩት” ሲል ትላንት ጠዋት የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል። በጸጥታ ኃይሎች ድብደባ ጉዳት የደረሰባቸው ሰላማዊ ሰልፈኞች ህክምና ለማግኘት ወደ ጤና ተቋማት አለመሄዳቸውን የገለጸው አስተባባሪው፤  ይህን ያደረጉት “አሁንም በፖሊስ እየታደኑ ስለሆነ ላለመታሰር” እንደሆነ አመልክቷል። 

የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዑመር ሃለቶ፤ የጸጥታ ኃይሎች በትላንትናው ዕለት በከተማው ተሰባስበው የነበሩ ሰዎችን እንዲበተኑ ማድረጋቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ሆኖም እንዲበተኑ የተደረጉት ሰዎች ሰላማዊ ሰልፈኞች ሳይሆን “ግርግር ፈጣሪዎች ናቸው” ብለዋል። የተሰባሰቡትን ሰዎች ያስተባበሩት ግለሰቦች “ህጋዊ ጥያቄ አላቀረቡም። ለጸጥታ አካላት እና ለከተማ አስተዳደሩም አላሳወቁም” ሲሉም ድርጊቱ ህገ ወጥ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ትላንት ሐሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ የትላንቱ ሰልፍም ሆነ ስብሰባው በአዋጅ የተቀመጠውን “ቢያንስ ከ48 ሰዓታት በፊት አስቀድሞ የማሳወቅ አካሄድ” ያልተከተለ በመሆኑ “ህገ ወጥ እንደሆነ አመጽ ተደርጎ ይተረጎማል” ሲል አስታውቋል። “ሰልፉ ህጋዊ አግባብነቱን ያልተከተለ ሰልፍ እንደመሆኑ ከህግ አግባብነት ውጪ የሚፈጸሙ ማንኛውም የቡድን እንቅስቃሴዎች አመጽ በመሆናቸው፤ አመጽን ለመከላከል የተቋቋሙ የጸጥታ ኃይሎች የታቀደውን አመጽ የማክሸፍና አመጸኞችን የመልቀም ስራን በአግባቡ አከናውነዋል” ሲል የከተማው አስተዳደር በመግለጫው አስፍሯል።

የከተማው አስተዳደር “ግርግር ፈጣሪዎች” ሲል የጠራቸው ግለሰቦች “እንዲለቀሙ ተደርገዋል” ሲል በመግለጫው ቢጠቅስም፤ የከተማው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ግን ከክስተቱ በኋላ “የታሰረ ሰው የለም” ሲሉ አስተባብለዋል። የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች ግን ከሰልፉ ጋር በተያያዘ አምስት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በከተማይቱ ፖሊስ ታስረዋል ብለዋል። ታስረዋል የተባሉ ተማሪዎችን በተመለከተ ከአፋር ክልል ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።    

የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች፤ ሰልፉ “ህገወጥ ነው” በሚል በከተማይቱ አስተዳደር የወጣውን መግለጫም አይቀበሉትም። ሰላማዊ ሰልፉ እንደሚካሄድ ለከተማ አስተዳደሩ፣ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ለከተማይቱ ፖሊስ የማሳወቂያ ደብዳቤ ቀደም ሲል ማስገባታቸውን የሚናገሩት አስተባባሪዎቹ፤ ሰልፉን “የክልሉ መንግስት አልፈለገውም” ይላሉ።   

ሰላማዊ ሰልፉ መጀመሪያ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እንደነበር የሚገልጹት አስተባባሪዎቹ፤ ለዚህም ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት “ረቡዕ የካቲት 29 ደብዳቤ አስገብተናል” ባይ ናቸው። ትላንት ሊካሄድ ለነበረው ሰልፍም፤ ከአራት ቀናት በፊት ሰኞ መጋቢት 5፤ 2014 ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ካስገቡ በኋላ፤ መልዕክቶቹን ማዘጋጀታቸውን እና በማህበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን አስተባባሪዎቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና የከተማይቱ ነዋሪዎች የትላንትናውን ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጁት፤ የህወሓት ኃይሎች “በወረራ” እንደያዙት በሚገልጹት የከልበቲ ረሱ ዞን ላለው የአፋር ህዝብ ድምጽ ለመሆነ በማሰብ እንደሆነ ይናገራሉ። ከልበቲ ረሱ ዞን “ምን ላይ እንዳለ የማይታወቀ የአፋር ህዝብ አለ” የሚለው የሰማራ ከተማ ነዋሪው የሰልፉ አስተባባሪ፤ በሰልፉ አማካኝነት የፌደራል መንግስት እና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለማግኘት ዕቅድ እንደነበራቸው ገልጿል።

የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ህወሓት ኃይሎች ከሁለት ወር ገደማ በፊት ባወጣው መግለጫ፤ “በከልበቲ ረሱ በተለያዩ ቦታዎች የአፋር ክልልን ወሰን ጥሶ በመግባት በአብአላ፣ በመጋሌ እና በበራህሌ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት በመክፈት በርካታ ንጹሃንን ለጉዳት ዳርጓል” ሲል ወንጅሎ ነበር። 

በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሰው አፋር ህዝብ ፓርቲም (አህፓ) በተመሳሳይ ክልሉ ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው አጎራባች ወረዳዎች የትግራይ አማጽያን “መጠነ ሰፊ ወረራ” ማካሄዳቸውን ገልጾ፤ የአፋር ክልል መንግስት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ እና “ጠንከር ያለ” ኮማንድ ፖስት እንዲያደራጅ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)