የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ወደ ግል ለማዘዋወር የተጀመረው ሂደት መቋረጡን መንግስት አስታወቀ

የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ የጀመረውን የፕራይቬታይዜሽን ሂደት አቋረጠ። የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ አርብ መጋቢት 9 ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ወደ ግል ለማዘዋወር የጀመረውን ሂደት ለማራዘም የወሰነው “በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ መድረክ በታዩ ኩነቶች እና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ምክንያት ነው”።   

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋም የሆነውን ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል “ፕራይቬታይዝ” ማድረግ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ከተካተቱ አንኳር ጉዳዮች አንዱ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ከኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ መግዛት የሚፈልጉ አካላት ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ባለፈው መስከረም ወር ጥሪ አቅርቦ ነበር።

እነዚህ አካላት ምርጥ ተሞክሮዎቻቸውን በማምጣት፤ በስራ አፈጻጸም፣ በመሰረተ ልማት አስተዳደር እና በቀጣይ ትውልድ ቴክኖሎጂዎች ረገድ ለመንግስታዊው ተቋም እሴቶችን የመጨመር ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ታምኖባቸውዋል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት “ከበርካታ ተጫራቾች” ውይይት ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር በዛሬ መግለጫው ጠቅሷል። 

ሆኖም መንግስት የጀመረውን ይህን ሂደት፤ በሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች እና ለውጦች ምክንያት ለማራዘም ከውሳኔ ላይ መድረሱ በመግለጫው ተመላክቷል። የኢትዮጵያ መንግስት “የተሻሻለውን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፤ እንዲሁም እያደገ በመሄድ ላይ የሚገኘውን የኢትዮ ቴሌኮም የፋይናንስ አፈጻጸምን ጊዜ ወስዶ ከግምት ውስጥ ማስገባት ለሁሉም ተሳታፊዎች በተለይም ለኢትዮጵያውያን ዜጎች የተሻለ ጥቅም ያስገኛል” የሚል እምነት እንዳለው በመግለጫው ሰፍሯል።   

ከኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ከፊሉን ወደ ግል ለማዘዋወር የተጀመረው እንቅስቃሴ ላልተወሰነ ጊዜ ቢራዘምም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሂደቱን ለማጠናቀቅ “ቁርጠኛ” መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። ሂደቱ ዳግም የሚጀመርበት ጊዜ በሚኒስቴሩ መግለጫ ባይገለጽም፤ ፍላጎታቸውን ካሳወቁ እና ከተጨማሪ ኩባንያዎች ጋር ሂደቱን የመቀጠል ፍላጎት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እንዳለ ግን ይፋ ተደርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)