በሁለት የአሶሴትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ 11 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቀደ

በሃሚድ አወል

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ በአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢ አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያ ቶማስ እንግዳ ላይ ተጨማሪ 11 የምርመራ ቀናት ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ ለፌደራል ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜውን የሰጠው፤ የሁለቱ ጋዜጠኞች ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ ነው። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ፖሊስ ከዚህ በፊት በነበረው ችሎት በተፈቀዱለት 14 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለማዳመጥ ነበር። የፌደራል ፖሊስን ወክለው የተገኙት ሁለት መርማሪዎች፤ የተጠርጣሪዎችን የሂሳብ እንቅስቃሴ ለማወቅ ደብዳቤ መጻፋቸውን እና ከተወሰኑ ባንኮች ምላሽ ማግኘታቸውን ለችሎቱ ገልጸዋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የፎረንሲክ ምርመራ መደረጉን በተጨማሪነት ያነሱት መርማሪዎቹ፤ የእዚሁኑ ውጤት አምስት ገጽ ከምርመራ መዝገቡ ጋር መያያዙን አስረድተዋል። ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን ይቻላቸው ዘንድም 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድላቸው ችሎቱን ጠይቀዋል። 

ጋዜጠኞቹን ወክለው በችሎቱ የተገኙ ሁለት ጠበቆች፤ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ውድቅ በማድረግ ለደንበኞቻቸው የዋስትና መብታቸውን እንዲያስጠብቅላቸው አመልክተዋል። አቶ ታደለ ገብረመድህን የተባሉት ጠበቃ፤ የፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቂያ “የቃላት መዛነፍ ሳይኖር” ከዚህ በፊት በሁለት ችሎቶች ከቀረቡት የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቅድ አይገባም” ሲሉ ተሟግተዋል። 

አቶ መልካሙ አጎ የተባሉት የጋዜጠኞቹ ጠበቃም፤ “የጨመሩት ነገር የለም። ያንኑ ገልብጠው ነው የመጡት” ሲሉ ምርመራውን እያካሄዱ ያሉ ፖሊሶችን በተመለከተ የቀረበውን ሙግት አጠናክረዋል። ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ለመጠየቅ ካቀረበው ምክንያት አንዱ “በወንጀል አብረው የተሳተፉ ግብረአበሮቻቸውን ተከታትሎ ለመያዝ” የሚል መሆኑን የጠቀሱት ጠበቃ ታደለ፤ “እነዚህ ግብረአበሮች የሚባሉትን ለመያዝ ፖሊስ ደንበኞቻችንን እንደመያዣ አድርጎ ሊይዝ አይገባውም” ሲሉ ችሎቱ ምክንያቱን ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቀዋል።

ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ለመጠየቅ ያቀረባቸው ሌሎች ምክንያቶች፤ ተጨማሪ የሰው እና ሰነድ ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኤሌክትሮኒክስ ምርመራ ውጤት መጠባበቅ፣  የተጠርጣሪዎችን የሂሳብ ዝውውር መረጃ ከሌሎች ባንኮች እስኪደርሱት መጠበቅ እንዲሁም በተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮችን ቃል መቀበል የሚሉ ናቸው። የፌደራል ፖሊስ ከዚህ በተጨማሪም “ተጠርጣሪዎች በዋስትና ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም” ሲል ተከራክሯል።

ጠበቃ ታደለ ገብረመድህን፤ ደንበኞቻቸው ፖሊስ የጠቀሳቸው የፋይናንስ እና የመንግስት ተቋማት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የማይችሉ መሆናቸውን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን እንዲያስጠብቅላቸው ጠይቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም “ደንበኞቼ ለምርመራው እክል የሚፈጥሩ፣ ሰነድ የሚያሸሹ እና ምስክር የሚያባብሉ አይደሉም” ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ፤ ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹ ግብረአበሮች በተመለከተ ያቀረበውን ምክንያት ሳይቀበለው ቀርቷል። “ሌሎች ግብረአበሮችን ለመያዝ ተጠርጣሪዎችን በመያዣነት ማቆየት አይገባም” ብሏል ፍርድ ቤቱ። የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ምላሽ ያልሰጡት ባንኮች ትልልቅ ተቋማት በመሆናቸው፤ ተጠርጣሪዎቹ በእነርሱ ላይ “ጫና ሊፈጥሩ አይችሉም” ሲልም ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ ለመጠየቅ ያቀረባቸውን ሌሎች ሁለት ምክንያቶች ውድቅ አድርጓቸዋል።

ጋዜጠኞቹ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፈጸሙ በተባሉበት አካባቢ ያሉ “ቀሪ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል” የሚለውን የፖሊስ ምክንያት ግን በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝቷል። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ፤ ፖሊስ የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀናትን በማሳነስ 11 ቀናትን ብቻ ፈቅዷል። 

አሚር አማን እና ቶማስ እንግዳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ አዲሱ ሙሉነህ ጋር በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከ110 ቀናት በፊት ህዳር 19፤ 2014 ነበር። ሆኖም የፌደራል ፖሊስ ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቀው ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።  

ፖሊስ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው “የአሸባሪውን ሸኔ ቡድንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ ነበር” በሚል ጠርጥሯቸው እንደሆነ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ከሁለቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ለወራት ታስሮ የቆየው ጋዜጠኛ አዲሱ ባለፈው የካቲት ወር ላይ መለቀቁ ይታወሳል። 

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ያህል ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቆዩት አሚር እና ቶማስ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ነበር። የካቲት 15 በነበረው የመጀመሪያ የችሎት ውሏቸው፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለፖሊስ ዘጠኝ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል። 

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት የካቲት 25 ሲሆን በዚህ የችሎት ውሎም ፖሊስ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በፍርድ ቤት ተፈቅዶለታል። በዛሬው የችሎት ውሎ አሚር እና ቶማስ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል። ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በእነሱ መታሰር ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

“እንደ አንድ ጋዜጠኛ መስራት ያለብንን ሰርተናል” ያለው የአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢው አሚር አማን፤ የታሰረው በሙያው ምክንያት መሆኑን ለፍርድ ቤት ገልጿል። የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳ በበኩሉ “ከያዙን ጀምሮ ‘ከአሸባሪ ጋር ስትተባበሩ ነበር’ እያሉ ያለፍቃዳችን ፎቶ ሲያነሱን እና ቪዲዮ ሲቀርጹን ነበር” ሲል አቤቱታውን አቅርቧል። ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ባቀረቧቸው አቤቱታዎች ላይ አስተያየት ሳይሰጥ አልፎታል።

የዛሬውን የችሎት ውሎ ለመከታተል የስምንት ወር ነፍጡር የሆነችው የአሚር አማን የትዳር አጋርን ጨምሮ ሌሎች የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች ሰሜን ሆቴል አካባቢ በሚገኘው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ግቢ ቢገኙም፤ ችሎቱ በጽህፈት ቤት በሰየሙ ምክንያት ሳይታደሙ ቀርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)