በሃሚድ አወል
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በየጫካው ያሉ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው የተሃድሶ ስልጠና በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ከተወካዮቻቸው ጋር ውይይት ሊያደርግ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የክልሉ መንግስት የተሃድሶ ስልጠና ሃሳቡን ያቀረበው፤ ከጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ታጣቂዎች ጋር ትላንት ቅዳሜ መጋቢት 10፤ 2014 በይፋ ዕርቅ መፈጸሙን ተከትሎ ነው።
በጉሙዝ ባህል መሰረት እንደተከናወነ የተነገረለት የዕርቅ ስነ ስርዓት የተካሄደው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ካማሺ ዞን፤ ካማሺ ከተማ በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና በካማሺ ወንዝ ዳርቻ ነው። በዕርቅ ስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ እና የጉህዴን ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ ተገኝተዋል።
በካማሺ ከተማ የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው እና ለአራት ሰዓታት በዘለቀው በዚሁ የዕርቅ ስነ ስርዓት ላይ የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ብጅጋ ጻፊዮ እና የታጣቂዎቹ ተወካይ አቶ ጫፌ አንደኛ ንግግር አድርገዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት እና በጉህዴን አመራሮች መካከል ዕርቅ መውረድ ተከትሎ፤ በጫካ የነበሩ አማጽያን ከእነ ትጥቃቸው ወደ ካማሺ ከተማ ሲገቡ መመልከታቸውን አንድ የከተማይቱ ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የታጣቂዎቹን ወደ ከተማ መግባት የካማሺ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ቦካ አቦሴም አረጋግጠዋል። ታጣቂዎቹ ለጊዜው የካማሺ ዞን ባዘጋጀላቸው ማረፊያ እንደሚቆዩ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢናገሩም፤ በየትኛው የከተማው አካባቢ እንደሚቆዩ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በካማሺ ዞን ለሚስተዋለው የጸጥታ ችግር በክልሉ መንግስት ተጠያቂ የሚደረጉትን ታጣቂዎች ከክልሉ መንግስት ጋር ለማስታረቅ፤ በካማሺ ዞን በተደራጁ ሽማግሌዎች አማካኝነት ጥረት መደረግ የጀመረው ከአንድ ወር ገደማ በፊት ነበር። የሀገር ሽማግሌዎቹ ካለፈው ጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ ካማሺ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በማቅናት ታጣቂዎቹን ሲያናግሩ ቆይተዋል።
ታጣቂዎቹ ከመንግስት ጋር እርቅ ከመፈጸማቸው በፊት እንዲሟሉላቸው የሚፈልጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በሽግማሌዎቹ በኩል ለመንግስት አቅርበዋል። ታጣቂዎቹ ካቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንደኛው “የታሰሩ ጉህዴን አመራሮች ይፈቱ” የሚል እንደነበር የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚፈጸሙ ጥቃቶች በክልሉ ባለስልጣናት ተጠያቂ የሚደረገው ጉህዴን፤ በህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ተደራጅቶ በክልሉ ሲንቀሳቀስ የቆየ ነው። ንቅናቄው በክልሉ በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ለመወዳደር ጭምር ዝግጅት ሲያደርግ ነበር። ምርጫው ከመካሄዱ አምስት ወራት በፊት ግን ጉህዴን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የነበረውን ህጋዊ ዕውቅና አጥቷል።
ጉህዴንን ጨምሮ 28 ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ የተሰረዙት፤ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት “መስፈርቶችን አላሟላም” በሚል ነው። ይህን ተከትሎ የተወሰኑ የጉህዴን አመራሮች እና አባላት ነፍጥ አንግበው ለመታገል መወሰናቸውን በማስታወቃቸው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንቅናቄውን ከፍተኛ አመራሮችን እና በርካታ አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።
የሀገር ሽማግሌዎች በክልሉ መንግስት እና በጉህዴን ታጣቂዎች መካከል ዕርቅ ለማውረድ እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ ግን በርካታ የንቅናቄው ታጣቂዎች ከእስር መፈታታቸው ተነግሯል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳም “ከፌደራል መንግስት ጋር በመነጋገር የታሰሩ የጉህዴን አመራሮች የካቲት 17 እንዲፈቱ ተደርገዋል” ሲሉ ዕርቁን ለማሳካት በክልሉ መንግስት በኩል የተወሰደውን እርምጃ ያስረዳሉ።
ከ20 ቀናት ገደማ በፊት ከእስር የተፈቱት የጉህዴን ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ፤ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው አመራሮች መለቀቃቸውን በመጥቀስ የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን ገለጻ ያረጋግጣሉ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከጉህዴን አመራሮች በተጨማሪ፤ 400 ገደማ የፓርቲው አባላትም ከእስር መፈታታቸውን አቶ ግራኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የጉህዴን ታጣቂዎች ከክልሉ መንግስት ጋር ዕርቅ ለማውረድ ያቀረቡት ሌላኛው ቅደመ ሁኔታ፤ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እና ለሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ነው። አካባቢው ሰላም ከሆነ የክልሉ መንግስት ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና በየትኛውም ቦታ እርዳታ ማቅረብ እንደሚችል ለታጣቂዎቹ እንደተገለጸላቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
ታጣቂዎቹ ካቀረቡት ዋና ዋና ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በካማሺ እና መተከል ዞን ያሉት የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲሁም የሌሎች ክልል ልዩ ኃይሎች አካባቢዎቹን ለቅቀው እንዲወጡ የሚለው ይገኝበታል። ይህን ቅድመ ሁኔታ በተመለከተ አቶ ጌታሁን ሲናገሩ “የተጠቀሱት የጸጥታ ኃይሎች እንዲወጡ በቅድሚያ ሰላም መምጣት እንዳለበት ከብዙ ውይይት በኋላ ተስማምተናል” ብለዋል።
የጉህዴን ሊቀመንበር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ውይይት አላደረግንም ባይ ናቸው። ሆኖም ከዕርቁ በኋላ በጉዳዩ ላይ ወይይት እንደሚደረግበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከዕርቁ በኋላ የሚኖረውን ሂደት በተመለከተ ከ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፤ “ታጥቀው በየጫካው ያሉ ታጣቂዎች፤ ትጥቃቸውን ፈትተው የተሃድሶ ስልጠና የሚያገኙበት ሁኔታ ላይ መምከር ከዕርቁ በኋላ የሚኖረው አንዱ ዋነኛ ጉዳይ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ግራኝ ጉደታም በተመሳሳይ “ከዕርቁ በኋላ ከክልሉ መንግስት ጋር የሚደረግ ውይይት አለ። [ታጣቂዎቹ] ትጥቅ መቼ እንደሚፈቱ የሚወሰነው በውይይት ነው እስከዛ ግን [ታጥቀው] ይቆያሉ” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከጉህዴን ታጣቂዎች ጋር ዕርቅ በማውረድ ተመሳሳይ ስምምነት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከአስር ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና የታጣቂ ቡድኑ ተወካይ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ በፈረሙት ስምምነት፤ የቡድኑ አባላት በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንዲገቡ ተስማምተው ነበር። ከስምምነቱ በኋላ ተሃድሶ ለወሰዱ የቡድኑ አባላትም ሹመት እስከመስጠት ተደርሶ ነበር።
ነገር ግን ስምምነቱም ሆነ የተሃድሶ ስልጠናው በክልሉ የሚከሰተውን ጥቃት እና የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ አላስቻለም። ከስምምነቱ በኋላ የጸጥታ ኃይል አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በታጣቂዎች በተሰነዘሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት የካቲት 23 በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት፤ አንድ የሻለቃ አመራርን ጨምሮ 20 ገደማ የጸጥታ ኃይል አባላት መሞታቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)