በኤደን ገብረእግዚአብሔር
የአማራ ክልል እና የፌደራል መንግስት የዋግ ላስታን አንገብጋቢ ችግር በልዩ ትኩረት መፍትሄ ካልሰጡት ከ1977ቱ የረሃብ ጊዜ የማይተናነስ “ፍጅት” እንደሚከሰት የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፓርቲ አስጠነቀቀ። የአካባቢውን ህዝብ ለመታደግ እና ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ይቻል ዘንድ የአማራ ክልል መንግስት የእርዳታ አቅርቦትና የመልሶ ማቋቋም ስራ በፍጥነት እንዲከያናወን ፓርቲው ጥያቄ አቀርቧል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፓርቲ (ሸንጎ) ይህን ያስታወቀው ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 13፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። ክልላዊው ፓርቲ በአራት ገጽ ባዘጋጀው በዛሬ መግለጫው፤ በሸንጎው አመራሮች እና አባላት ላይ ተፈጽመዋል ካላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እስከ አገውና ቅማንት ህዝብ የመደራጀት ጥያቄዎች ድረስ ያሉ ጉዳዮችን ዳስሷል።
ፓርቲው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ላይ ሲያራምድ የቆየውን አቋም እንዲሁም በፌደራል መንግስት በኩል ተግባራዊ የተደረገውን የተኩስ አቁም እና ወደፊት ይደረጋል በሚባለው ድርድር ያለውን አመለካከት በመግለጫው አንጸባርቋል። በጦርነቱ ምክንያት በአገው ማህበረሰቦች ላይ ደርሷል ያለውን “የከፋ ችግር” በተመለከተም ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል።
እንደ ፓርቲው ገለጻ ከሆነ፤ በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን፣ በላስታ ላሊበላ እንዲሁም በትግራይ ክልል ድንበር በሚገኙ የዋግ አካባቢዎች የሚኖሩ የአገው ማህበረሰቦች፤ “ለረዥም ጊዜ መውጫ፤ መግቢያ አጥተው” በከፍተኛ ችግር ውስጥ ቆይተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች “ጦርነቱ ከተወው አሳዛኝ የሞት እና የአካል መጉደል በተጨማሪ እጅግ በከፋ ችግር ውስጥ ይገኛሉ” ሲል ፓርቲው አክሏል።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና፣ የትምህርት እና የመሰረተ ልማት ተቋማት በጦርነቱ ሳቢያ መውደማቸውን የጠቀሰው የፓርቲው መግለጫ፤ በዚህ ምክንያትም የአካባቢው ነዋሪዎች ውሃ፣ መብራትና ስልክ የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለወራቶች ሳያገኙ መቅረታቸውን አትቷል። የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ቢሆን “በበቂ ሁኔታ የእለት ደራሽ እና የማቋቋሚያ እርዳታ እያገኙ አይደለም” የሚለው ፓርቲው፤ ከችግሩ ስፋት እና ግዝፈት አንጻር የተሰጣቸው ትኩረት አናሳ መሆኑን አመልክቷል።
“[የአገው ማህበረሰቦች] በአሰቃቂ የእልቂት ጫፍ ላይ ደርሰዋል። በርካቶች ከቀያቸው ለመሰደድ ተገድደዋል። ቀሪውም በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ በአስከፊ ሁለንተናዊ ችግር ውስጥ ይገኛል” ሲል የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፓርቲ በመግለጫው አስፍሯል። ፓርቲው በአካባቢው አለ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ከ1977ቱ የረሃብ ጊዜ ጋር አነጻጽሮታል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርቅ የተከሰተበትን የ1977ቱን ወቅት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው “በጣም በብዙ ሺህ ህዝብ በረሃብ ያለቀበት ነበር” ሲሉ ይገልጹታል። በወቅቱ ልክ እንደ አሁኑ ጊዜ ጦርነት እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ አላምረው፤ “በእርዳታ ማጣት ምክንያት ሰዎች በየመንገዱ እየሞቱ የሚቀሩበት ጊዜ ነበር” ሲሉ የሁኔታውን አስከፊነት ያስታውሳሉ።
“አሁንም ተመሳሳይ ሁኔታ እያንዣበበት ነው ያለው። ሰዎች ሰውነታቸው ከስጋቸው ተላቆ፣ አጽማቸው ወጥቶ እየታዩ ነው ያሉት። በጣም የሚያሰቅቅ ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ አቶ አላምረው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል። እርሳቸው የሚመሩት ፓርቲ በዛሬው መግለጫው፤ በዋግ ላስታ አካባቢ ያለው “አንገብጋቢ ችግር” በልዩ ትኩረት መፍትሄ ካልተሰጠው ከ1977ቱ የረሃብ ጊዜ የማይተናነስ “ፍጅት ሊከሰት ይችላል” ሲል አስጠንቅቋል።
አሁን በአካባቢው በሚስተዋለው ችግር “የአገው ህዝብ የለማኝነት መገለጫና ተምሳሌት ነው የሆነው” የሚሉት አቶ አላምረው፤ ይህ የተከሰተው የአካባቢው ህዝብ “ለዘመናት በደረሰበት አደህይቶ የመግዛት ፖሊሲ ነው” ሲሉ ጉዳዩ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የሚሻገር መሆኑን ጠቁመዋል። በሰቆጣ ከተማ ብቻ ከአካባቢው ካሉ ወረዳዎች የተፈናቀሉ 52 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንዳሉ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ የክልሉ መንግስትም ሆነ ሌሎች አካላት ለተፈናቃዮቹ በቂ ትኩረት አልሰጧቸውም ሲሉ ተችተዋል።
የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፓርቲ፤ በብዙ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በድርድር እንዲቋጭ እንደሚሻ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከጥንስሱ ጀምሮ እንዲቆም ደጋግሞ መጠየቁን የገለጸው ሸንጎው፤ ሆኖም ጥሪው ሰሚ አጥቶ “ሰፊ ጥፋት ያስከተለ ጦርነት” መካሄዱን በዛሬ መግለጫው ጠቅሷል።
የፌደራል መንግስት ጦሩን ከትግራይ አውጥቶ የተናጠል ተኩስ አቁም ሲያውጅ ሸንጎው ደግፎ እንደነበርም ፓርቲው በመግለጫው አስታውሷል። ዘግይቶም ቢሆን ገዢው የብልጽግና ፓርቲ “ጦርነቱን ለማቆም ከህወሓት ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነኝ” ማለቱን የአገው ብሔራዊ ሸንጎ በበጎ እንደሚመለከተው በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። የገዢውን ፓርቲ ውሳኔ “የሰላምን ዋጋ በሚገባ የተገነዘበ እና ጦርነቱ ቢቀጥል የሚያስከትለውን ተጨማሪ አስከፊ ጥፋት ለመግታት የተወሰደ” ሲልም ሸንጎው አሞካሽቶታል።
እንደ ገዢው ፓርቲ ሁሉ ህወሓትም “ችግሩን ሰጥቶ በመቀበል መርህ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ለመላው ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን በቶሎ እንዲያሳውቅ” የጠየቀው የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፤ ሁለቱ ወገኖች “በፍጥነት ድርድር እንዲጀመሩም” አሳስቧል። ሸንጎው ከዚህ በተጨማሪም የፌደራል መንግስት ለሁሉም አማጽያን ተመሳሳይ ጥሪ አድርጎ አለመግባባቶችን በንግግርና በድርድር እንዲፈታ በዛሬው መግለጫው ጥያቄ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)