የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከኃላፊነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ለቀቁ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ አቶ ተወልደ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን አረጋግጠዋል።
እኚሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ዋና ስራ አስፈጻሚው በገዛ ፍቃዳቸው ከስራ መልቀቃቸውን ዛሬ ከሰዓት ለመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ከተሰራጨ ኢሜይል እንዳወቁ ጨምረው ገልጸዋል። አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንግድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት በጥር 2003 ዓ.ም ነበር። አቶ ተወልደ ለ11 ዓመታት በዋና ስራ አስፈጻሚነት የመሩትን ተቋም የተቀላቀሉት ከ37 ዓመታት በፊት በ1977 ዓ.ም ነው።
በአየር መንገዱ በትራንስፖርት ወኪልነት ስራ የጀመሩት አቶ ተወልደ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከእንግሊዙ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በበቢዝነስ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። አቶ ተወልደ በ2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መቀበላቸው ይታወሳል። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)