የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለሰባት ዓመታት በዋና ስራ አስፈጻሚነት ያገለገሉት አቶ ግርማ ዋቄ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕን በቦርድ ሊቀመንበርነት እንዲመሩ ተሾሙ። አቶ ግርማን በአዲሱ የኃላፊነት ቦታ ላይ በቅርቡ የመደባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አቶ ግርማ “ከፍተኛ ልምድ ያላቸው፣ ስኬታማ እና ከበሬታ ያላቸው የቢዝነስ መሪ” መሆናቸውን የገለጸው አየር መንገዱ፤ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪውም በቅጡ የሚታወቁ ግለሰብ መሆናቸውን አመልክቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመሩባቸው ዓመታት፤ ተቋሙ ላስመዘገበው ፈጣን እና ትርፋማ እድገት መሰረት የጣሉ መሆናቸውን ለዚህ ገለጻው በማሳየነት ጠቅሷል።
“የአቶ ግርማ የውሳኔ አሰጣጥ ክህሎት የተፈተነ እና በሚገባ የተረጋገጠ ነው” ያለው አየር መንገዱ፤ “የእርሳቸው ልምድ፣ የስራ ባህል እና ትጋት ሲቀናጅ፤ ቦርዱን በሊቀመንበርነት ለመምራትም ሆነ አየር መንገዱን ወደ ቀጣይ ደረጃ ለማሻገር ብቁ ያደርጋቸዋል” ሲል የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ ወደ ተቋሙ መመለስ የሚኖረውን ጠቀሜታ አስገንዝቧል።
ከታህሳስ 2007 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩ የቆዩት የቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው። አቶ አባዱላ የሊቀመንበርነት ቦታውን የተረከቡት ከቀድሞው የብአዴን ሊቀመንበር እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አዲሱ ለገሰ እንደነበር ይታወሳል።
አየር መንገዱ በዛሬ መግለጫው የዋና ስራ አስፈጻሚው ተወልደ ገብረማርያምን ከስራ መልቀቅ አረጋግጧል። አቶ ተወልደ ላለፉት ስድስት ወራት በአሜሪካ በህክምና ላይ መቆየታቸውን የገለጸው አየር መንገዱ፤ በግል የጤና ሁኔታዎች ላይ ማተኮር ስለሚገባቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚነት መቀጠል አለመቻላቸውን አስረድቷል።
ይህን ተመርኩዞም አቶ ተወልደ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አስተዳደር ቦርድ በጡረታ ለመሰናበት ጥያቄ ማቅረባቸውን አመልክቷል። ቦርዱ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 14፤ 2014 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ አቶ ተወልደ ያቀረቡትን የቅድመ ጡረታ ጥያቄን እንደተቀበለ አየር መንገዱ አስታውቋል። የአየር መንገዱ ቦርድ የአቶ ተወልደን ተተኪ በቅርቡ እንደሚያስታውቅም ጨምሮ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)