ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን የህወሓት ኃይሎች ከአፋር ክልል መውጣት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ተናገሩ

በሃሚድ አወል

ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን የህወሓት ኃይሎች ከአፋር ክልል መውጣት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ገለጹ። ቃል አቃባዩ፤ በአፋር ክልል ያለው ህዝብ ወደ ትግራይ ክልል በሚጓዘው የሰብዓዊ እርዳታ ላይ ቅሬታዎችን እያሰማ መሆኑንም ተናግረዋል።   

ለትግራይ ክልል የሚደርሰው የሰብዓዊ እርዳታ ክልሉን በሚጎራበተው የአፋር ክልል እንደሚያልፍ ያስታወሱት ቃል አቃባዩ፤ ይህ በህዝቡ ላይ ቅሬታ አሳድሯል ብለዋል። ዲና ሙፍቲ ይህን የተናገሩት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 15፤ 2014 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ላይ ነው። 

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ወደ መቐለ ሲጓዙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች በአፋር ክልል ስላጋጠማቸው እክል የተጠየቁት ዲና፤ “ ‘አሸባሪው ኃይል በእኛ በኩል የሚሄደውን ምግብ እየተመገበ፤ እኛን እየወጋ ነው’ [የሚል] በህዝቡ በኩል ስሜት አለ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“ይኼን በምንነጋገርበት ሰዓት በTPLF [ህወሓት] የተያዙ የተወሰኑ የአፋር ወረዳዎች አሉ” የሚሉት ቃል አቃባዩ፤ “ ‘እንዴት በእኛ መንገድ በእኛ መሬት (territory) አልፎ እነዚህን ይመግባል’ በሚል የተወሰኑ የአፋር ዜጎች ይኼንን የሚቃወሙበት ሁኔታ አለ” ሲሉ በክልሉ አለ ያሉትን የቅሬታ መንስኤ አብራርተዋል። ለዚህ መፍትሔ የሚሆነውም የህወሓት ኃይሎች የአፋርን  ክልልን ለቅቆ መውጣት መሆኑንም ቃል አቃባዩ አስታውቀዋል።  

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ፤ በአፋር ክልል እርዳታ በማጓጓዝ ረገድ ችግር እንደነበር ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። ልዩ ልዑኩ ትላንት ረቡዕ ለዜና ወኪሉ በሰጡት ቃል፤ ባለፈው ሳምንት ወደ አፋር ክልል እርዳታን ለማድረስ የተደረገው ሙከራ “በሁሉም በኩል ካለው ጥልቅ ቅያሜ እና አለማመን የተነሳ በአካባቢው አካላት ታግዷል” ብለዋል።  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዛሬ ሳምንት ሐሙስ መጋቢት 8፤ 2014 ባወጣው መግለጫ፤ በአብአላ ወደ ትግራይ የሚወስደው የሰብአዊ እርዳታ መስመር የተዘጋው “በአፋር በድጋሚ በተቀሰቀሰው ጥቃት” መሆኑን አስታውቆ ነበር። መስሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው፤ ባለፈው ሳምንት ብቻ 20 ምግብ የጫኑ ተሸከርካሪዎች እንዲሁም ሶስት የነዳጅ ማጓጓዣ መኪኖች ከአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ወደ መቐለ መንቀሳቀሳቸውን ጠቅሷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (UNOCHA) በተመሳሳይ ቀን ባወጣው ሪፖርቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን መግለጫ ተቃርኗል። በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ የሰብአዊ ሁኔታ የዳሰሰው የጽህፈት ቤቱ ሪፖርት፤ በመንገድ መተላለፊያ እጦት ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ በሚፈለገው መጠን እና ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል እየደረሰ አለመሆኑን አስታውቋል።

በትግራይ ክልል ካለፈው የመኸር እርሻ የቀረው የምግብ ክምችት ማለቁን የጠቀሰው የጽህፈት ቤቱ ሪፖርት፤ ሰብአዊ እርዳታ በሰዓቱ ባለመድረሱ የምግብ ዋስትና እጦቱ በሚቀጥሉት ወራት ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ትንበያውን አስቀምጧል። በክልሉ ከሚያስፈልገው ምርጥ ዘር አሁን በክልሉ ያለው ስምንት በመቶ ገደማ መሆኑን የጠቆመው ጽሀፍት ቤቱ፤ ይህ በግጭት የተጎዱትን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት እና ኑሮ በእጅጉ ይጎዳል ሲል ተጽዕኖውን አብራርቷል፡፡

እንደ ተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከሆነ፤ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ምንም አይነት ማዳበሪያ እና አግሮ ኬሚካሎችን የመሳሰሉ የግብርና ግብዓቶች ወደ ትግራይ ክልል አልገቡም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)