በሃሚድ አወል
የአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢ አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያ ቶማስ እንግዳ እያንዳንዳቸው በ60 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቅቀው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ በፍርድ ቤት ተወሰነላቸው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 20 ውሳኔውን ያስተላለፈው “ምርመራው ካለበት አልተንቀሳቀሰም” በሚል ነው።
ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው፤ የፌደራል ፖሊስ በሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ እያደረገው ላለው ምርመራ በፈቀደው 11 ተጨማሪ ቀናት የተከናወኑ ተግባራትን ለማድመጥ ነበር። ፖሊስ በተፈቀዱለት ቀናት የሁለቱን ተጠርጣሪዎች እና የአንድ ምስክርን ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤት አስረድቷል።
በጽህፈት ቤት በኩል በተከናወነው የዛሬ የችሎት ውሎ ፖሊስን ወክለው የተገኙት መርማሪ፤ “የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ያስፈልገናል” በሚልም ተጨማሪ 14 ቀናት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ጋዜጠኞቹ የተጠረጠሩበትን ወንጀል “ልዩ ባህሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት” ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ሲፈቅድ መቆየቱን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፤ ሆኖም የምርመራው ሂደት ከዚህ በፊት ከነበረበት ለውጥ አለማሳየቱን በመግለጽ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ አድርጓል።
ይህን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ በጋዜጠኞች ጠበቃ በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ መቀበል፤ ተጠርጣሪዎቹ እያንዳንዳቸው የ60 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም ጋዜጠኞቹ ከአገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳም አስተላልፎባቸዋል።
ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደውን የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ፤ የጋዜጠኞቹ የትዳር አጋሮችን ጨምሮ አምስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው በጽህፈት ቤት በአካል ተገኝተው ተከታትለዋል። ጋዜጠኞቹ በዋስትና እንዲወጡ በፍርድ ቤት ከተወሰነ በኋላ የጋዜጠኛ አሚር ባለቤት ደስታዋን በእንባ ስትገልጽ ታይታለች።
አሚር አማን እና ቶማስ እንግዳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ አዲሱ ሙሉነህ ጋር በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከአራት ወራት በፊት ህዳር 19፤ 2014 ነበር። የፌደራል ፖሊስ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት “የአሸባሪውን ሸኔ ቡድንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ ነበር” በሚል ተጠርጥረው እንደሆነ አስታውቆ ነበር።
በእስር ላይ ከነበሩት ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው አዲሱ ሙሉነህ ባለፈው የካቲት ወር ላይ ከእስር የተለቀቀ ሲሆን በዚያው ወር አጋማሽም የአሚር እና ቶማስ ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ተወስዷል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ያህል ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቆዩት አሚር እና ቶማስ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ነበር።
የሁለቱን ጋዜጠኞች ጉዳይ የሚመለከተው ፍርድ ቤት ከዛሬ በፊት በነበሩት ሶስት ቀጠሮዎች ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜያት በመፍቀዱ ምክንያት ተጠርጣሪዎቹ በእስር እንዲቆዩ ሆነዋል። የጋዜጠኞቹን እስር አስመልክቶ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲ.ፔ.ጄን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ባወጧቸው መግለጫዎች፤ አሚር እና ቶማስ እንዲፈቱ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ዛሬ ከተካሄደው የጋዜጠኞቹ የፍርድ ቤት ውሎ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሁለት የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጋዜጠኛ አሚር አማን “በአስቸኳይ” ከእስር እንዲፈታ ጥሪ አቅርበው ነበር። ጥሪውን ያቀረቡት አባላት የካሊፎርኒያ ተወካይ የሆኑት አዳም ሺፍ እና የፔንስልቬንያዋ ተወካይ ሜሪ ጌይ ስካሎን ናቸው።
የአሜሪካው ብሔራዊ ፕሬስ ክለብ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት ሰኞ መጋቢት 5፤ 2014 ባወጣው መግለጫ አሚር አማንን ጨምሮ “ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ክስ ሳይመሰረትባቸው ታስረዋል’’ ያላቸው ሶስት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት “በአስቸኳይ” እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። በፕሬስ ክለቡ ፕሬዚዳንት ጄን ጀድሰን እና የተቋሙ የጋዜጠኝነት ኢንስቲትዩትን በሚመሩት ጊል ክላይን ስም በወጣው በዚህ መግለጫ የቶማስ እንግዳ እና የተራራ ኔትዎርክ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ ጉዳይም ተነስቷል።
አሚር አማን በዘጋቢነት የሚሰራበት አሶሴትድ ፕሬስም በዚህ ወር መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ፤ ጋዜጠኛ አሚር “በአስቸኳይ እንዲፈታ” ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረቡ አይዘነጋም። የዜና ተቋሙ ዋና አዘጋጅ ጁሊ ፔስ “አሚር ምንም አይነት ክስ ሳይመሰረትበት በግፍ ታስሯል” ማለታቸው በመግለጫው ተጠቅሶ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)