የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ የክልሉን ምክር ቤት አባላት ቁጥር ወደ 171 ሊያሳድግ ነው

በሃሚድ አወል

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከአራት ወራት በፊት የተመሰረተውን የክልሉን ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ52 ወደ 171 ሊያሳድግ ነው። የምክር ቤት አባላቱን ብዛት የሚያሳድገው የአዋጅ ረቂቅ፤ ዛሬ ሐሙስ በተጀመረው እና እስከ ነገ አርብ መጋቢት 23 በሚቆየው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። 

የአዋጅ ረቂቁ ወደ ክልሉ ምክር ቤት የተላለፈው፤ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ሰኞ መጋቢት 12፤ 2014 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ውይይት ካደረገበት በኋላ ነው። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ላይ ሲመሰረት የክልሉ ምክር ቤት አባላት ቁጥር 52 ነበር። 

እነዚህ 52 ተወካዮች በነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን፤ አዲሱ ክልል ሲመሰረት በቀጥታ የክልሉ ምክር ቤት መስራች አባላት ሆነዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ህገ መንግስት በመሸጋገሪያ ድንጋጌው ላይ “ህገ መንግስቱ ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት በህጉ መሰረት በክልል ምክር ቤት የተወከሉ አባላት፤ ለዚህ ክልል ምክር ቤት እንደተወከሉ ይቆጠራል” ሲል ቀደም ሲል ተመርጠው የደቡብ ክልል ምክር ቤትን የተቀላቀሉ ተወካዮች የአዲሱ ክልል ምክር ቤት አባላት እንደሚሆኑ አስፍሯል። 

ሃምሳ ሁለቱ የአዲሱ ምክር ቤት አባላት፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ከመሰረቱት የካፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ሸካ እና ኮንታ ዞኖች የተውጣጡ ናቸው። ከእነዚህ የምክር ቤት አባላት ውስጥ ሃያዎቹ የካፋ ዞንን የወከሉ ናቸው። የዳውሮ ዞን በዘጠኝ አባላት በመወከል በተወካይ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ሲቀመጥ፤ ምዕራብ ኦሞ እና የቤንች ሸኮ ዞኖች እያንዳንዳቸው ሰባት ተወካዮች በአዲሱ ክልል ምክር ቤት ውስጥ አሏቸው። የሸካ ዞን ስድስት፤ የኮንታ ዞን ደግሞ ሶስት የክልል ምክር ቤት ተወካዮች አሏቸው። 

ክልሉን የመሰረቱት የምክር ቤት አባላት ቁጥር “አሁን ካለን የህዝብ ብዛት አንጻር ያንሳል” የሚሉት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፤ የክልሉ ምክር ቤት በሚያካሄደው መደበኛ ጉባኤ ቁጥሩ ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርግበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 22 በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ፤ የክልሉን ምክር ቤት ተወካዮች ቁጥር ለመወሰን የቀረበን ረቂቅ አዋጅ ተወያይቶ ማጽደቅ የሚል አጀንዳ ተካትቷል።  

የአዋጅ ረቂቁ የክልሉን ምክር ቤት አባላት ቁጥር ወደ 171 እንደሚያሳድግ የክልሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ተናግረዋል። በአዋጁ መሰረት፤ በክልሉ ያሉ መደበኛ ምርጫ ክልሎች እያንዳንዳቸው በምክር ቤት ውስጥ 10 መቀመጫ ይኖራቸዋል ያሉት ምንጮቹ፤ ልዩ የምርጫ ክልሎች ደግሞ እያንዳንዳቸው ሶስት መቀመጫዎች እንደሚይዙ አስረድተዋል።

በሚሻሻለው የክልሉ ምክር ቤት አባላት ቁጥር መሰረት የካፋ ዞን 66 ተወካዮች የሚኖሩት ሲሆን፤ የዳውሮ ዞን 30፣ ቤንች ሸኮ 23፣ ምዕራብ ኦሞ 22፣ ሸካ 20 እንዲሁም ኮንታ 10 ተወካዮች እንደሚኖራቸው ምንጮች ጠቁመዋል። የክልሉ ምንጮች ይህን ቢሉም የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ግን “እስካሁን የተወሰነ ነገር የለውም” ሲሉ መረጃውን አስተባብለዋል። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 15 መደበኛ እና ሰባት ልዩ በድምሩ 22 ምርጫ ክልሎች አሉት። በነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ምርጫ ክልሎች እያንዳንዳቸው ሶስት፤ ልዩ ምርጫ ክልሎች ደግሞ አንድ ውክልና ነበራቸው። አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 20 መቀመጫዎች አሉት።

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ፤ ምርጫን የሚመለከቱ የክልል ህጎች በህገ መንግስቱ እና በምርጫ አዋጁ ከተቀመጡ የምርጫ ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋል። ክልሎች የምክር ቤቶቻቸውን አባላት ቁጥር ለመቀየር የሚሰጡት ውሳኔ፤ ለአጠቃላይ ምርጫ ከሚደረገው የእጩዎች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ስድስት ወር አስቀድሞ መደረግ እንዳለበትም ያስቀምጣል። 

ከስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር በአንድ ላይ በህዝብ ውሳኔ የተመሰረተው አዲሱ ክልል፤ የምክር ቤት አባላቱን ቁጥር የሚወስነውን አዋጅ ካጸደቀ በኋላ፤ ቀሪ የምክር ቤት አባላት እንዲሟሉለት ለቦርዱ ጥያቄ እንደሚያቀርብ አቶ ወንድሙ ገልጸዋል። “[አዋጁን] ምክር ቤቱ ካጸደቀው፤ ከጉባኤው ማግስት ቀጥታ ነው ለምርጫ ቦርድ የምናቀርበው። ምክር ቤቱ አዋጁን ካልተቀበለው እና አሳማኝ የሆኑ ነገሮች ከተነሱ [አዋጁን] እንደገና የምናይበት አግባብ ይኖራል” ሲሉ አፈ ጉባኤው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

“[አዋጁን] ምክር ቤቱ ካጸደቀው፤ ከጉባኤው ማግስት ቀጥታ ነው ለምርጫ ቦርድ የምናቀርበው። ምክር ቤቱ አዋጁን ካልተቀበለው እና አሳማኝ የሆኑ ነገሮች ከተነሱ [አዋጁን] እንደገና የምናይበት አግባብ ይኖራል”

አቶ ወንድሙ ኩርታ – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

አንድ የክልሉ የመንግስት ኃላፊ፤ አጠቃላይ ምርጫ በመጠናቀቁ ቀሪ የክልሉ ምክር ቤት አባላት የሚመረጡት በማሟያ ምርጫ ወቅት እንደሚሆን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በምርጫ አዋጁ መሰረት በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች “በተለያየ ምክንያት የተጓደሉባቸው አባላት እንዲሟሉላቸው ለቦርዱ ጥያቄ ሲያቀርቡ” የማሟያ ምርጫ ሊደረግ ይችላል። ቦርዱ ጥያቄው በደረሰው ስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የማሟያ ምርጫ እንደሚያካሂድም በአዋጁ ላይ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)