ፖሊስ በሁለት የአሶሴትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ የጠየቀው ይግባኝ ውድቅ ተደረገበት

በሃሚድ አወል

የአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢ አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያ ቶማስ እንግዳ ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን ይግባኝ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ። ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ውድቅ ያደረገው “መርማሪ ፖሊስ ስራውን በትጋት እያከናወነ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ስላደረበት” መሆኑን ገልጿል። 

የፌደራል ፖሊስ ይግባኝ የጠየቀው፤ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መጋቢት 20 የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ነው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለቱ ጋዜጠኞች በ60 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ ከእስር ወጥተው ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር። ሆኖም ፖሊስ በውሳኔው ላይ ይግባኝ በመጠየቁ ጋዜጠኞቹ ከእስር ሳይፈቱ ቀርተዋል።  

ምርመራውን እያከናወነ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ “ቀሪ ስራዎች እያሉን ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና እንዲወጡ መወሰኑ አግባብ አይደለም” በሚል የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሻር ያመለከተው ትላንት ረቡዕ መጋቢት 21 ነው። ፖሊስ በዚሁ ማመልከቻው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቅድለትም ጠይቆ ነበር። 

የጋዜጠኞቹ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ለተጨማሪ የምርመራ ቀናት መጠየቂያ የሚያቀርባቸው ምክንያቶች ተመሳሳይ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያጸና ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 22 በጽህፈት ቤት በኩል በሰጠው ውሳኔ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቷል። “ተጠርጣሪዎቹ ከአራት ወራት በላይ በእስር ላይ ቆይተዋል ተብሎ ነው የሚታመነው” ያለው ፍርድ ቤቱ፤ ውሳኔውን የሰጠው “[በፖሊስ] ለተጨማሪ ጊዜ መጠየቂያ የሚቀርበው ምክንያት ተመሳሳይ ነው። ይህ መርማሪ ፖሊስ ስራውን በትጋት እያከናወነ መሆኑን አጠራጣሪ ያደርገዋል” በሚል ምክንያት ነው። 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ከሰጠ በኋላ ጉዳዩን ከውጭ ሆነው ሲከታተሉ የነበሩ የጋዜጠኞቹ የትዳር አጋሮች እና ቤተሰቦቻቸው ደስታቸውን በእንባ ጭምር ሲገልጹ ተስተውለዋል። በፍርድ ቤቱ በአካል ተገኝተው ሂደቱን የተከታተሉት ሁለቱ ጋዜጠኞች ከውሳኔው በኋላ እርስ በእርስ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በደስታ ስሜት ተውጠው ሲተቃቀፉ ታይተዋል።

አሚር አማን እና ቶማስ እንግዳ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከአራት ወራት ህዳር 19፤ 2014 ነበር። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት  “የአሸባሪውን ሸኔ ቡድንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ ነበር” በሚል ተጠርጥረው እንደሆነ ፖሊስ በወቅቱ ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)