በሃሚድ አወል
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሚሰጥ የአበል ክፍያ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ቅሬታ ዛሬ ረቡዕ በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ። ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሆስፒታሉ ሰራተኞች፤ ለሁለት ዓመታት ያህል የኮሮና ቫይረስን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በ2012 ዓ.ም ሊከፈላቸው ከሚገባው ክፍያ 34 በመቶ ያህሉ እንዳልተከፈላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከፊት ለተሰለፉ የጤና ዘርፍ ሰራተኞች የተጨማሪ አበል ክፍያ እንዲደረግላቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት በመመሪያ ወስኖ ነበር። ግንቦት 14፤ 2012 የጸደቀው መመሪያ በሁሉም የፌደራል ጤና ተቋማት እና የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ተግባራዊ ይሆናል መባሉ ይታወሳል።
የጥቁር አንበሳ ሰራተኞች ከዚህ ክፍያ በተጨማሪ የሶስት ወር የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተፈጸመልንም ሲሉ ያማራርሉ። በሆስፒታሉ ያለው የህክምና ቁሳቁሶች እጥረትም በተመሳሳይ ለሆስፒታሉ ሰራተኞች የቅሬታ ምንጭ መሆኑንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ሰራተኞቹ ዛሬ ረፋዱን ከሆስፒታሉ ቅጽር ግቢ በመውጣት ቅሬታቸውን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ማሰማት ቢችሉም በጸጥታ ኃይሎች ወደ ግቢ እንዲመለሱ ተደርገዋል።
ከ60 እስከ 70 ገደማ የሚሆኑት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ከተመለሱ በኋላ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር በአዳራሽ ተነጋግረዋል፡፡
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አንዷለም ደነቀ “የኮቪድ ክፍያን በተመለከተ በኮሌጁ አንድ ሳንቲም የለም። መክፈል አንችልም። እሱን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። ቅሬታው መቅረብ ያለበት ለእኔ ሳይሆን ለሚመለከተው [አካል] ነው” ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቅሬታቸውን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር፣ ለትምህርት ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ማቲዮስ ኤርሳሞ በበኩላቸው፤ የጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከፊት ለተሰለፉ የጤና ዘርፍ ሰራተኞች በ2014 ምንም አይነት በጀት አለመያዙን ገልጸዋል። ክፍያውን ለመፈጸም “በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በኩል ገንዘብ ሚኒስቴርን እንጠይቃለን” ያሉት ዶ/ር ማቲዮስ፤ “ሆኖም በጀቱ ይፈቀዳል ብዬ ቃል አልገባም” ሲሉ ለቅሬታ አቅራቢዎቹ ነግረዋቸዋል።
የህክምና ቁሳቁስ እጥረትን በተመለከተ ችግሩ የተከሰተው “በበጀት እጥረት” መሆኑን የጠቆሙት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ “ህመምተኞች [የህክምና ቁሳቁስ] እኛ ሲጎድለን ከውጭ መግዛት አለባቸው። አሁን ልዋሻችሁ አልፈልግም፤ ወደፊትም ይገዛሉ። [በሆስፒታሉ] እያለ ግን ግዙ ከተባለ ችግር ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አንዷለም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያነሱትን የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተም ምላሽ ሰጥተዋል። የትርፍ ሰዓት ክፍያው እንደማይቀር የተናገሩት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ “ሀገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ትግስት ያስፈልጋል” ሲሉ የጤና ባለሙያዎቹ ለተወሰነ ጊዜ ያህል በትግስት እንዲጠብቁ ጠይቀዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ከክፍያ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ዘንድ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወካዮችን መርጠው ጉዳዩን እንዲከታተሉ ምክራቸውን ለግሰዋል። በዚህም መሰረት ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ አራት የቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወካዮች ወደ ሆስፒታሉ ስራ አስፈጻሚ ቢሮ አቅንተዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ቅሬታ አቅራቢዎች፤ የዩኒቨርሲቲው እና የሆስፒታሉ አመራሮች ባሉት መሰረት ችግሩ ይፈታል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ “ጥያቄዎቻችን መልስ ካላገኙ ፈቃድ ጠይቀን ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)