የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሙስና ተጋላጭ ከሆኑ ተቋማት ቀዳሚው ነው ተባለ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሙስና ተጋላጭ ከሆኑ የመንግስት ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሙ መሆኑን የፌደራል የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት ባከናወነው ጥናት ይህንኑ ማረጋገጡንም ገልጿል።

የፌደራል የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፤ ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚቀርብበትን የሙስና ተጋላጭነት ችግር በተመለከተ ጥናት ያደረገው በ2013 ዓ.ም ነው። የእዚህ ጥናት ግኝት ዛሬ አርብ መጋቢት 23፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው ውይይት ላይ ቀርቧል።

ቋሚ ኮሚቴው ውይይቱን የጠራው፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የንብረት አስተዳደር እና አፈጻጸም የኦዲት ሪፖርትን መነሻ በማድረግ ነው። ለውይይቱ መነሻ የሆነው የመንግስት ተቋሙን የኦዲት ሪፖርት ያዘጋጀው፤ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ነው። 

ከ2010 እስከ 2012 ባለው የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የንብረት አስተዳደርን ምን ይመስል እንደነበር የፈተሸው የኦዲት ሪፖርቱ፤ ተቋሙ የንብረት አያያዝ እና የሰራተኛ አመዳደብ እንከኖች ያሉበት መሆኑ አመልክቷል። መስሪያ ቤቱ የኦዲት ሪፖርቱን ያሰናዳው አራት የአገልግሎቱን ግምጃ ቤቶች በናሙናነት በመውሰድ ነው።

በኦዲት ሪፖርቱ ምልከታ ከተደረገባቸው ውስጥ በአዲስ አበባ ጎፋ አካባቢ የሚገኘው የአገልግሎቱ ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት ይገኝበታል። በዚሁ ግምጃ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ 7.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ዕቃዎች ለ15 ዓመታት በመጋዘን ታሽገው እንደሚገኙ በኦዲት ግኝቱ ተደርሶበታል። በተመሳሳይ በዚሁ ግምጃ ቤት 59 ሚሊዮን ብር ገደማ ዋጋ ያላቸው ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ የማይውሉ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች መኖራቸው በሪፖርቱ ተረጋግጧል። 

በኦዲት ሪፖርቱ በናሙናነት የተወሰዱት ሌሎች የመስሪያ ቤቱ ግምጃ ቤቶች በኮተቤ የተሽከርካሪ ጥገና እና አስተዳደር፣ በምዕራብ እና ደቡብ አዲስ አበባ ዲስትሪክቶች ስር የሚገኙ ናቸው። በናሙናነት በተወሰዱት በመስሪያ ቤቱ ስር ባሉ ሁሉም ግምጃ ቤቶች፤ ከንብረት አያያዝ ባለፈ ንብረቶች መዘረፋቸውን በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል። 

በዛሬው የፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በአስረጂነት የተገኙት የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፤ ግምጃ ቤቶቹ በተቋሙ የጥበቃ ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ እና በካሜራዎች ጥበቃ የሚደረግላቸው እንደሆኑ አስረድተዋል።  “እነዚህ ባሉበት ነው ንብረት እየጠፋ ያለው። [ከተቋሙ] ጋር የተያያዘ የተዘረጋ ሲስተም ያለ ይመስለኛል። ስለዚህ የተቋሙ ውስጥ ይፈተሽ” ሲሉ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

የፌደራል ምክትል ዋና ኦዲተሯ፤ ከንብረት አያያዝ እና ዝርፊያ ጋር በተያያዘ ሁለት ማሳያዎችን አንስተዋል። በ2010 ዓ.ም. ከተቋሙ የለቀቀ አንድ ሰራተኛ፤ ሲገለገልበት ነበረውን “ቪ 8” መኪና እስካሁን አለመመለሱን እና አንድ ሌላ ተሽከርካሪም በተመሳሳይ ያለበት እንደማይታወቅ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል። 

“የተቋሙ ሰራተኞች ከሚሰሩት ስራ ጋር የተመጣጣነ አቅም የላቸውም” የሚሉት ምክትል ዋና ኦዲተሯ “ተቋሙ በአግባቡ እየተመራ ነው ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያያት ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት አሰራሩን ማሻሻል እና ማረም እንደሚገባውም አሳስበዋል። 

በፌደራል የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና ስጋት ጥናት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች በላቀ የሙስና ተጋላጭነት ያለበት መሆኑን መስሪያ ቤታቸው ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት “ሌብነት የሚበዛበት [ተቋም] ነው” የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ “በየቅንርጫፉ ያሉ ጥገና የሚያደርጉ ወይም መብራት የሚያስገቡ ሠራተኞች፤ እቃ እንደሌለ እያደረጉ ከህብረተሰቡ ጉቦ ይቀበላሉ” ሲሉ በተቋሙ አለ ያሉትን ችግር ለመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስረድተዋል። 

በመስሪያ ቤታቸው ጥናት የተሳተፉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም፤ “መብራት ኃይል ነው ለአገልግሎት ታማኝ ያልሆነው” የሚል አስተያየት እንደሰጡ አክለዋል። “የተቋሙ አመራር ኃላፊነቱን ወስዶ ተግባራዊ ከማድረግ እና ትኩረት ሰጥቶ እርምጃ ከመውሰድ አንጻር ዳተኛ ነው” የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ በዚህም ምክንያት በተቋሙ “ስፋት ያለው የሙስና ችግር አለ” ሲሉ ይከስሳሉ።  

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የሚመሩትን መስሪያ ቤት በተመለከተ በሁለቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የቀረበውን ትችት እና ውንጀላ ተከላክለዋል። መስሪያ ቤታቸው “ሌብነት የሚበዛበት ነው” መባሉን ያስተባበሉት አቶ ሽፈራው፤ “ብዙ ህዝብ ስለምናገለግል ብዙ ቅሬታ ሊቀርብ ይችላል። አብዛኛው ሰራተኛ ‘ሌባ ነው’ የሚለውን ድምዳሜ [ግን] አንቀበልም፤ ስህተት ስለሆነ” ብለዋል። 

ትችቶች የበረቱበት መንግስታዊው ተቋም ጥፋት በፈጸሙ ሰራተኞቹ ላይ እርምጃ አይወስድም በሚል ለቀረበው ነቀፌታም ዋና ስራ አስፈጻሚው ምላሽ ሰጥተዋል። መስሪያ ቤታቸው በ2013 ዓ.ም በ900 ገደማ ሰራተኞች ላይ “የተጠያቂነት እርምጃ” መውሰዱን በምሳሌነት የጠቀሱት አቶ ሽፈራው፤ “ዳተኛ አይደለንም፤ ይኼ አይገልጸንም። ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ችግሮችን ለማስተካከል በስርዓት እየሄድን ነው” ሲሉ ተሟግተዋል።

እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የፍትህ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊ፤ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት    ከተከሰቱ ችግሮች ጋር በተያያዘ በህግ የሚጠየቁ አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። በሚኒስቴሩ የፌደራል ህጎች ተፈጻሚነት መከታተያ ዳይሬክተር ትብለጽ ቡሽራ “ለጠፉ ነገሮች የአስተዳደራዊ፣ የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት ይኖራል” ሲሉ ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል። 

የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ውይይቱን ከመቋጨታቸው በፊት ለሶስት የመንግስት ተቋማት የቤት ስራ ሰጥተዋል። የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ፤ ለሙስና እና ብልሹ አሰራር አጋላጭ ጉዳዮች ካሉ በሁለት ወር ውስጥ አጣርቶ ለቋሚ ኮቴው ሪፖርት እንዲያቀርብ ሰብሳቢው ጠይቀዋል።

የፍትህ ሚኒስቴርም በተመሳሳይ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ፤ የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ጉዳዮች ካሉ አጣርቶ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያቀርብ እና ክስ እንዲመሰርት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። “በህዝብ ሀብት እና ንብረት ላይ ውድመት ያደረሱ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ” የመወሰድ ኃላፊነት ደግሞ በገንዘብ ሚኒስቴር ላይ መጣሉን አቶ ክርስቲያን ታደለ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)