በሰሜኑ ጦርነት በአማራ ክልል የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራው ግብረ ኃይል፤ አብዛኛውን ምርመራውን ማጠናቀቁን አስታወቀ

በሃሚድ አወል

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ በአማራ ክልል የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንዲያጣራ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል፤ ሲያከናውን የቆየውን ምርመራ ከሞላ ጎደል ማጠናቀቁን አስታወቀ። ግብረ ኃይሉ በእስካሁኑ ምርመራው በጦርነቱ የተሳተፉ ወገኖች፤ ከዳኝነት ውጪ ሰዎች መግደላቸውን፣ ከባድ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን እንዲሁም የአስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃት መፈጸማቸውን ማረጋገጡን ገልጿል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይሉ እንዲቋቋም ያደረጉት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት ጋር በጥምር ያደረጉትን የምርመራ ውጤት ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በዚሁ የምርመራ ሪፖርታቸው፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት የተሳተፉ ሁሉም አካላት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አስታውቀው ነበር። 

በግጭቱ ተሳታፊ አካላት በተለያየ መጠን ተፈጽመዋል ከተባሉት ጥሰቶች ውስጥ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ይገኙበታል። ሁለቱ ተቋማት ተፈጽመዋል ላሏቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፤ የፌደራሉ መንግስት ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ምርመራ እንዲያከናውን ምክረ ሃሳብ አቅርበው ነበር።

ምክረ ሃሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ የተቋቋመው ግብረ ኃይል በይፋ ወደ ስራ መግባቱን ያስታወቀው ከአራት ወራት በፊት ህዳር 20፤ 2014 ሲሆን፤ የምርመራ ቡድኖቹን ወደ አማራ እና ክልል የላከው ደግሞ ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ነው። የምርመራ ቡድኖቹን ያወቀረው፤ በግብረ ኃይሉ ስር የምርመራ ጉዳዮችን እንዲከታተል እና አጥፊዎችን የማስቀጣት ሂደቶችን እንዲያከናወን የተቋቋመው ኮሚቴ ነው። 

የፍትህ ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልል ፍትህ ቢሮዎችን በአባልነት ያቀፈው ይህ ኮሚቴ፤ ከእነዚሁ የመንግስት ተቋማት የተውጣጡ 158 ገደማ አባላት ያሉበትን የምርመራ ቡድኖችን በማወቀር ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ልኳል። ወደ አማራ ክልል የተሰማራው የምርመራ ቡድን በሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ እንዲሁም በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች ያደረጋቸውን የወንጀል ማጣራት ስራዎች ማጠናቀቁን የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ ካሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የምርመራ ቡድኑ በጦርነቱ ሳቢያ ተፈጸሙ ያላቸውን ሶስት “ከባድ ወንጀሎችን” መለየቱንም የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል። የምርመራ ቡድኑ የለየው የመጀመሪያ ወንጀል “በግጭቱ ተሳታፊነት የሌላቸው ንጹሃን ላይ ከዳኝነት ውጪ የተፈጸመ ግድያ” (extra-judicial killing) መሆኑን ዶ/ር ታደሰ አስረድተዋል። ቡድኑ በምርመራው የለየው ሌላኛው የወንጀል አይነት ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ነው። 

ምርመራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃቶችም በከባድ ወንጀልነት መመዝገባቸውን የግብረ ኃይሉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አስታውቀዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ስር ከተመሰረቱ አራት ኮሚቴዎች ውስጥ አንደኛው የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የማጣራት ኃላፊነት የተጣለበት ነው። ይህን ኮሚቴ በበላይነት የሚመራው በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።     

በአማራ ክልል የተሰማራው የምርመራ ቡድን በማጣራት ስራው ተፈጽመዋል ካላቸው “ከባድ ወንጀሎች” በተጨማሪ፤ ስቅየት (torture)፣ የግለሰብ ንብረት ውድመት እና ዘረፋ እንዲሁም በመንግስት ንብረት እና መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳቶች መድረሳቸውን በምርመራው ለይቷል ተብሏል።  

እንደ ዶ/ር ታደሰ ገለጻ፤ የምርመራ ቡድኑ በተሰማራባቸው አካባቢዎች መረጃዎችን ለማሰባሰብ ሁለት መንገዶች ተጠቅሟል። “በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመረጃ ምንጭ ምስክር ነው” የሚሉት ዶ/ር ታደሰ፤ በጦርነት ውስጥ የነበሩ አካባቢዎች ወደ መልሶ ግንባታ ከመግባታቸው በፊት የደረሱ ውድመቶችን የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዮዎችም ለመረጃ ምንጭነት ማገልገላቸውን ገልጸዋል።

“ግጭቱ በተራዘመ ቁጥር አዳዲስ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ እነዚያም መመርመር አለባቸው” የሚሉት የጽህፈት ቤት ኃላፊው፤ በትግራይ እና አፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎች የቀጠለው ውጊያ ምርመራውን እንዳዘገየው ተናግረዋል። “አዲዲስ ሁኔታዎች [ምርመራውን] affect አድርገውታል። አሁን ምርመራውን መጨረስ የሚቻልበት ሰዓት ነበር ነገር ግን አፋር ክልል ያለው ግጭት አዲስ ክስተቶችን ይዞ መጥቷል። ይህ የምርመራ ስራውን ወደ ኋላ ጎትቶታል” ብለዋል። 

“ቀጣዩ ሂደት የሚሆነው አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ ነው” የሚሉት ዶ/ር ታደሰ፤ “[ምርመራው] የትኛውን አካባቢ ሸፈነ? ምን ያህል ጊዜ ወሰደ? እነዚህ አብይ ግኝቶች አሉ ተብሎ ሪፖርት ይቀርባል። በዚያ ሪፖርት ላይ ተመስርቶ፤ ወደ ክስ የሚያመራ ጠንካራ ማስረጃ የቀረበባቸው ላይ፤ የክስ ስራውን ዐቃቤ ህግ ይሰራል” ሲሉ ከምርመራው መጠናቀቅ በኋላ የሚኖረውን ሂደት አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)