ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ

በሃሚድ አወል

ለአራት ወራት ገደማ በእስር ላይ የቆየው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 27 ዋስትናውን የፈቀደው፤ ጋዜጠኛው በጠበቃው በኩል ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ከመረመረ በኋላ ነው።

የጋዜጠኛው ጠበቃ ገመቹ ጉተማ የደንበኛቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ከ25 ቀናት በፊት መጋቢት 2፤ 2014 ነበር። የዋስትና ጥያቄው የቀረበለት ፍርድ ቤቱ ባለፉት አራት ተከታታይ ቀጠሮዎች በጋዜጠኛ ታምራት የዋስትና ይገባኛል ጥያቄ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ ቆይቷል።

ፍርድ ቤቱ መጋቢት 8፤ 2014 በነበረው የመጀመሪያ ቀጠሮ፤ የጋዜጠኛውን የዋስትና ጥያቄ በመቃወም የኦሮሚያ አቃቤ ህግ በጹሁፍ ያቀረበውን ማመልከቻ በመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መጋቢት 13፤ 2014 ከዋለው ችሎት ጀምሮ በነበሩት ሶስት ተከታታይ ቀጠሮዎች፤ የዋስትና ጥያቄውን በተመለከተ “ምርመራውን አለማጠናቀቁን” በመግለጽ ለውሳኔ ቀጠሮ ሲሰጥ ቆይቷል። 

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማዕከላዊ የወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው፤ የክልሉ ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛው የዋስትና ጥያቄ ላይ ያቀረበውን ተቃውሞ ወድቅ በማድረግ፤ ተጠርጣሪው የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና አስይዞ ከእስር እንዲፈታ ውሳኔ አሳልፏል። የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የታምራት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቆ የነበረው በሶስት ምክንያቶች ነበር።

የክልሉ ዐቃቤ ህግ የዋስትና ጥያቄውን የተቃወመበት የመጀመሪያው ምክንያት፤ ጋዜጠኛው “TPLF [ህወሓት] እና ኦነግ ሸኔ በመንግስት ላይ በከፈቱት ጦርነት ተሳትፎ እያደረገ በመሆኑ” ከእስር ሊፈታ አይገባም በሚል ነው። የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ሁለተኛ ምክንያት፤ ጋዜጠኛ ታምራት “የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከመሰረቱ መፍረስ አለበት” በማለት ጉዳዩን ለመፈጸም ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር ሲተባበር ነበር የሚል ነው። 

የአቃቤ ህግ ሶስተኛው መቃወሚያ ታምራት ነገራ የተጠረጠረበት ወንጀል “ከባድ” መሆኑ ነው። “[ተጠርጣሪው] የተጠረጠረበት ወንጀል ከባድ በመሆኑ እና ሕግ መንግስታዊ ስርዓትን ለማፍረስ ሲንቀሳቀስ የነበረ በመሆኑ በዋስትና ከወጣ ስለማይመለስ” ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ እንዲያደርገው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። 

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ታምራት የዋስትና ጥያቄ ላይ ተቃውሞውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጹሁፍ አቅርቦ ቢሟገተም፤ በስር ፍርድ ቤት እንዲፈጽም የታዘዘውን ጉዳይ ግን በቀነ ገደቡ መሰረት ሳያሳካ ቀርቷል። የጋዜጠኛውን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ ሲመለከተ የቆየው የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ የክልሉ ዐቃቤ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ትዕዛዝ ከሰጠ 27 ቀናት ቢያልፉም ጋዜጠኛው እስካሁን ድረስ ክስም ሳይመሰረትበት፣ የዋስትና መብቱም ሳይከበር ለአራት ወራት ገደማ በእስር ላይ ቆይቷል።

“ተራራ ኔትዎርክ” የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ፤ ከቤቱ ተወስዶ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ታምራት ታህሳስ 1፤ 2014 ነበር። ጋዜጠኛው ያለፉትን ሶስት ገደማ ወራት የሚሆነውን ጊዜ ያሳለፈው፤ በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ስር በሚገኘው የገላን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያ ነው።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በታምራት ላይ ሲያከናውን የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን ለገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት መግለጹን ተከትሎ፤ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በተጠርጣሪው ላይ ክስ እስኪመሰረት ድረስ ጋዜጠኛው በፊንፊኔ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ ወደ ሚገኘው ዳለቲ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወር በችሎት መታዘዙ ይታወሳል።

በዛሬው ችሎት ጋዜጠኛ ታምራት በአካል ያልተገኘ ሲሆን፤ እርሱን ወክለው በስፍራው የተገኙት ጠበቃው አቶ ገመቹ ጉተማ ናቸው። የዛሬውን የችሎት ውሎ በቦታው ተገኝተው የተከታተሉት የጋዜጠኛው አክስት፤ ፍርድ ቤቱ ለታምራት የ50 ሺህ ብር ዋስትና መፈቀዱን ሲሰሙ በደስታ ሲያለቅሱ ታይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)