ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከእስር ተፈታ

ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከአራት ወራት ገደማ እስር በኋላ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 28፤ 2014 ከእስር ተፈታ። ጋዜጠኛው ከእስር የተፈታው፤ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ50 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ከእስር እንዲፈታ በትላንትናው ዕለት ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው። 

የታምራት ቤተሰቦች በትላንትናው ዕለት በፍርድ ቤት የተወሰነውን የዋስትና ገንዘብ ክፍያ ቢፈጽሙም፤ የመፈቻ ትዕዛዙ በዳኞች ባለመፈረሙ ጋዜጠኛው ትላንት ማክሰኞ ከእስር ቤት ሳይወጣ መቅረቱን ወዳጆቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መሟላት የሚገባው የፍቺ ሂደት በዛሬው ዕለት ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ጋዜጠኛ ታምራት ዛሬ ምሳ ሰዓት አካባቢ በፊንፊኔ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ ከሚገኘው ዳለቲ ማረሚያ ቤት ከእስር መለቀቁ ወዳጆቹ ገልጸዋል።

ጋዜጠኛው ከተፈታ በኋላ በቀጥታ ወደ ቤቱ የሄደ ሲሆን፤ ከቤተሰቡ ጋር ተገናኝቷል። “ቤተሰብ ጋር ያለው ደስታ የተለየ ነው። እናቱ በጣም ደስተኛ ሆናለች። ሁሉም በለቅሶ ነው ደስታውን የገለጸው” ሲል አንድ የታምራት የቅርብ ወዳጅ በቤተሰቡ ዘንድ ያለውን ስሜት አጋርቷል።    

“ተራራ ኔትወርክ” የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ የሆነው ታምራት ነገራ፤ በፖሊስ ከመኖሪያ ቤቱ ከተወሰደ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋለው ታህሳስ 1፤ 2014 ነበር። ጋዜጠኛ ታምራት ከእስር እንዲፈታ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲ.ፒ.ጄን ጨምሮ ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። (በሃሚድ አወል- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)