የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር መስመርን የሚገነባው የቱርክ ኩባንያ የሰራተኞቹን ውል አቋረጠ

በሃሚድ አወል

የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ (ወልዲያ) የባቡር መስመር ፕሮጀክትን ግንባታ የሚያከናውነው “ያፒ መርከዚ” የተሰኘው የቱርክ ኩባንያ የሰራተኞቹን ውል አቋረጠ። ኩባንያው ውሉን ማቋረጡን ያስታወቀው ከአስር ቀናት ገደማ በፊት ለሰራተኞቹ በጻፈው ደብዳቤ ነው። 

በ“ያፒ መርከዚ” የኢትዮጵያ ቅንርጫፍ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ሰርካን ኮርክማዝ ተፈርሞ በወጣው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው በዚሁ ደብዳቤ ላይ፤ የሰራተኞቹ ውል የተቋረጠው ከመጋቢት 22፤ 2014 ጀምሮ እንደሆነ ተገልጿል። ኩባንያው የሰራተኞቹን ውል ያቋረጠው የባቡር መስመር ፕሮጀክቱ ባለቤት ከሆነው ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር የገባው ውል በመቋረጡ ሳቢያ መሆኑን በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።

የቱርኩ ኩባንያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ያለው ውል የተቋረጠው ከሁለት ወር ገደማ በፊት ከጥር 25፤ 2014 ጀምሮ መሆኑን በደብዳቤው ገልጿል። በኢትዮጵያ የባቡር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን የመገንባት እና የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት ዓላማ አንግቦ የተቋቋመው ኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፤ የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክትን ለ“ያፒ መርከዚ” የሰጠው በ2006 ዓ.ም ነበር። 

ፕሮጀክቱን የተረከበው የቱርኩ ኩባንያ የባቡር መስመር ግንባታውን በ1.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በሶስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውሎ ገብቶ ነበር። ይሁን እንጂ የባቡር መስመር ግንባታው አምስት ዓመታት ዘግይቶም ቢሆን መጠናቀቅ አልቻለም። ፕሮጀክቱ ለዓመታት ከመጓተቱ በተጨማሪም በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ላለፉት ሰባት ወራት ያህል ተቋርጦ መቆየቱን የኩባንያው ሰራተኞች ይናገራሉ።  

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የኩባንያው ሰራተኛ፤ የፕሮጀክቱ ስራ ሙሉ ለመሉ የቆመው የወልዲያ ከተማ በትግራይ አማጽያን ከተያዘች ከአንድ ወር በኋላ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው ወልዲያ ከተማ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የወደቀችው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

የወልዲያ ከተማ የባቡር መስመሩ መዳረሻ ከሆነችው የሃራ ገበያ 25 ኪሎ ሜትሮች ገደማ ርቀት ላይ ትገኛለች። ከኮምቦልቻ እስከ ሃራ ገበያ ያለውና በሁለተኛው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ ግንባታው ሲከናወን የቆየው የባቡር መስመር የሚሸፍነው ርቀት 122 ኪሎ ሜትር ነው። የመጀመሪያው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ አካል የሆነው ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ ያለው የባቡር መስመር 270 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው። 

ለሰባት ዓመታት በባቡር ፕሮጀክቱ ያገለገለው ሰራተኛ፤ ኩባንያው የግንባታ ስራውን ማቆም ብቻ ሳይሆን ለሰራተኞቹ የአራት ወራት ደመወዝ ሳይከፍል ቆይቷል ሲል ይከስሳል። ኩባንያው ከሁለት ሳምንት በፊት የሰራተኞቹን የአራት ወራት ውዝፍ የደመወዝ ክፍያ ከፍሎ ማጠናቀቁንም ያስረዳል።

“ደመወዝ ሲለቀቅልን ፕሮጀክቱ እንደገና ስራ ይጀምራል የሚል ሀሳብ ነበር ያለን” የሚለው በኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ የሆነው የኩባንያው ሰራተኛ፤ ሆኖም ከአምስት ቀናት ቆይታ በኋላ ውላቸው መቋረጡን የሚገልጽ ደብዳቤ በኩባንያው ቢሮዎች እና የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተለጥፎ ማንበቡን ይገልጻል። “ለሁሉም የያፒ መርከዚ ሰራተኞች” እንዲደርስ የተጻፈው ደብዳቤ፤ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በገባው ውል መሰረት ለ“ያፒ መርከዚ ክፍያ ባለመፈጸሙ” እና “በመሰረታዊ የውል ጥሰት ምክንያት” ውሉ መቋረጡን አመልክቷል። 

የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልከሪም አማን፤ በቱርኩ ኩባንያ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሶስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሰራተኞች ውል መቋረጡን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በደረሰው ውድመት ምክንያት ኮንትራክተሩ ከመንግስት ጋር ድርድር እያደረገ ነው። ጉዳዩ መቋጫ የሚያገኝበት ጊዜ አይታወቅም። ስለዚህ ‘ዝም ብዬ ደመወዝ ከምከፍል’ ብሎ ነው [የሰራተኞቹን ውል] ያቋረጠው” ሲሉ ኩባንያው ውል ያቋረጠበትን ምክንያት አብራርተዋል። 

አቶ አብዱልከሪም በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በባቡር መስመሩ ላይ እና ግንባታውን በሚያከናውነው ድርጅት ላይ የደረሰው ውድመት እየተጠና መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኝ አንድ የፕሮጀክቱ ሰራተኛ የቱርኩ ኩባንያ ያጋጠመውን ጉዳት ሲያስረዳ፤ “ከፍተኛ ስርቆትም ውድመትም ነው የደረሰበት። ከሌሎች ካምፓኒዎች በተለየ ሁኔታ ውድመት የደረሰበት የእኛ ካምፖኒ ነው” ብሏል።   

“ያፒ መርከዚ” በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ሰራተኞቹ ቢመሰክሩም፤ ተቀጣሪዎቹን ከስራ ያሰናበተበት መንገድ ላይ ግን ቅሬታቸውን ከማቅረብ ወደ ኋላ አላሉም። የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር መስመር የሰራተኞች ማህበር ተወካይ የሆነ አንድ ግለሰብ፤ “ድርጅቱ ሰራተኞቹን አሰናብቷል። ሰራተኞቹን ያሰናበተበት አግባብ ደግሞ ሰራተኞቹን ያስደሰተ አይደለም” ሲል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው የሰራተኞች ማህበሩ ተወካይ፤ ሰራተኞቹን ቅር ያሰኘው ኩባንያው ውላቸውን ላቋረጠባቸው ሰራተኞች የካሳ ክፍያ አለመክፈሉ ነው ባይ ነው። ኩባንያው በበኩሉ በአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት ውላቸው ለተቋረጠባቸው ሰራተኞች የስራ ስንብት፣ የማስጠንቀቂያ እና የዓመት እረፍት ክፍያ መፈጸሙን ገልጿል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሰራተኞችም ኩባንያው ያላቸውን ክፍያዎች መፈጸሙን አረጋግጠዋል።  

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት በ“ያፒ መርከዚ” ኩባንያ የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት በአካል በመገኘት ጥያቄዎች ብናቀርብም የሚመለከተውን አካል ማግኘት ሳንችል ቀርተናል። የፕሮጀክቱ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በስልክ ያቀረብናቸውን ጥያቄዎችም ምላሽ አላገኘነም።

ግንባታው 94 በመቶ ከደረሰ በኋላ መቆሙ የተነገረው የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት፤ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠለት ወቅት ለሀገሪቱ ልማት ቁልፍ አስተዋጽኦ ከሚያበረከቱ መሰረተ ልማቶች አንዱ እንደሚሆን ተተንብዮለት ነበር።  የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ ይፋ ባደረጋቸው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዶችም፤ የባቡር መስመሮች ግንባታ ከቀዳሚ የመሰረተ ልማት ግቦች ተርታ መቀመጣቸው ይታወሳል። 

በሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት፤ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 2,741 ኪ.ሜ ርዝመት ያላቸው የባቡር መስመሮች ዝርጋታ ለማከናወን ታቅዶ ነበር። በአምስት ኮሪደሮች እና በስድስት መስመሮች ሊገነቡ ታቅደው ከነበሩት ከእነዚህ የባቡር ፕሮጀክቶች ውስጥ ማሳካት የተቻለው 22 በመቶውን ብቻ መሆኑን ባለፈው ዓመት ይፋ የተደረገው የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ያመለክታል።     

እንደ የልማት ዕቅድ ሰነዱ ገለጻ፤ ያለፉት አስር ዓመታት የባቡር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም “ዝቅተኛ” የሆነው በፋይናንስ እጥረት፣ በእውቀትና ልምድ እጥረት እንዲሁም በውጭ ሀገር እውቀት እና ቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው ምክንያት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት፤ አሁን በሀገሪቱ ያለውን የባቡር መስመር ሽፋን ከ902 ኪሎ ሜትር ወደ 4,199 ኪሎ ሜትር ለማሳደግ ዕቅድ መያዙም በልማት እቅዱ ላይ ተጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)