በገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት መካከል የሚታዩ መፋጠጦች ሀገራዊ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ኢዜማ አስጠነቀቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፤ በመንግስት አካላት መካከል የሚታዩ መፋጠጦች እንዲረግቡ ካልተደረጉ አጠቃላይ ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ ሲል አስጠነቀቀ። ፓርቲው በሀገርና በህዝብ ላይ እየደረሰ ነው ላለው “እያንዳንዱ መከራ”፤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ “ተቀዳሚ ተጠያቂ” እንደሚሆን አሳስቧል።

ኢዜማ ይህን ያለው ዛሬ ሐሙስ ሚያዚያ 6፤ 2014 በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው ባለ 10 መግለጫ ነው። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ “አገራዊ ፓርቲ ነኝ” ቢልም፤ በባለስልጣናቱ መካከል ከሰሞኑ የተስተዋለው “ንትርክ” በተግባር “የብሔር ፓርቲ” መሆኑን በአደባባይ ማስመከሩን ገልጿል። 

“ክልሎችን ለመምራት በመንበሩ የተቀመጡ የብልጽግና አመራሮች ተናብበው እና ተቀናጅተው፤ ሀገራችን ከገጠማት ዘርፈ ብዙ ፈተና ለማውጣት በጋራ በመስራት ከህዝቡ አንድ እርምጃ ቀድመው የመፍትሔ ሃሳብ ማቅረብ ሲገባቸው፤ መሽቶ በነጋ ቁጥር እርስ በእርስ እየተናከሱ፣ አለፍ ሲልም ለጸብ እየተጋበዙ፣ ከኑሮ ውድነቱ በላይ ራሳቸው አመራሮቹ ለሀገር ስጋት ሆነዋል” ሲል ኢዜማ በዛሬ መግለጫው አትቷል። 

በገዢው ፓርቲ ውስጥ የሚፈጠርን የስልጣን ሽኩቻ ለማሸነፍ “ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት ከችግሩ የማምለጫ ስልት ተደርጎ በተደጋጋሚ ተወስዷል” ሲል ኢዜማ ከስሷል። ይህን አካሄድ “እጅግ አሳዛኝ እና አሳፋሪ እውነታ” ሲል የተቸው ተቃዋሚ ፓርቲው፤ “የመንደራቸው አውራ ለመሆን የሚታትሩ የብልጽግና አመራሮች ከዚህ አስነዋሪ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

ኢዜማ በአዲስ አበባ ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው በዚሁ መግለጫ የተገኙት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ “በእኛ እምነት ካልቻሉ፤ ስልጣናቸውን አስረክበው፣ በር ዘግተው ነው እንደሌላው ፓርቲ ተደባደቡም ተጨቃጨቁም ማድረግ ያለባቸው። ህዝብ ትከሻ ላይ የራስን ስሜት መገንፈል አይቻልም። አስቦ መናገር፣ አስቦ መተግበር እና በኃላፊነት መንቀሳቀስ [ያስፈልጋል]። ይኼ ትዕቢት የዓመታት አይደለም፤ የወራት እድሜ የለውም። በጣም ብዙ ትዕቢተኛ ሲተነፍስ ያየንበት ሀገር ስለሆነ ትዕቢት የማያዋጣ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ተናግረን ማለፍ እንፈልጋለን” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ አሁን የሚታየው መገፋፋት በሁለት ኃይሎች መካከል የሚካሄድ መሆኑ ኢዜማ ጠቁሟል። ፓርቲው የመጀመሪያዎቹን ኃይሎች “በማያልቅ እና በማይጠረቃ የዘውግ ፖለቲካ ፍላጎት ሀገርን በቋሚነት መበዝበዝ የሚፈልጉ” ሲል የጠራቸው ሲሆን፤ በሌላ ወገን የተሰለፉትን ደግሞ በደረሰባቸው በደል የቆሰሉ እና እልህ የተጋቡ ዜጎች” መሆናቸውን ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል። የእነዚህ ኃይሎች “ጽንፍ ለጽንፍ ሆነው መጓተታቸው ከዕለት ወደ ዕለት ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል” ሲልም አጽንኦት ሰጥቷል። 

ይህን የመሰለ መንገድ መከተል “ከመጠፋፋት በዘለለ ወደ መፍትሔ በጭራሽ የማያደርስ መሆኑን” የገለጸው ኢዜማ፤ “ብልጽግና [ፓርቲ] እንደ ቀደመው ጊዜ ያሻኛን ባሰኘኝ ሰዓት እፈጽማለሁ ብሎ በሚሄድበት አጓጉል መንገድ በሚፈጠር ችግር በሀገርና በህዝብ ላይ ለሚደርሰው ለእያንዳንዱ መከራ ተቀዳሚ ተጠያቂ እንደሚሆን ለማሳወቅ እንወዳለን” ብሏል። 

“እንደ ሀገር የተደቀኑብንን ችግሮች ጥልቀት እና ግዝፈት በግብታዊነት እና በእልኸኝነት የሚፈቱ ስላልሆኑ፤ በመነጋገር መግባባት ላይ መድረስ ብቸኛው አማራጫችን መሆኑን በማመን ሁሉም አካላት ሀገርን አስቀድመው በሰከነ መንገድ ሊነጋገሩ ይገባል”

– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)

“ኃላፊነት የጎደለው የገዢው ፓርቲ የመከፋፈል አካሄድ በዚሁ እስከቀጠለ [ድረስ] አስከፊው መከራችን ቀንበሩን እየጨመረ መሄዱ የማይታበል ሃቅ በመሆኑ በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ ተቀራርቦ ሊሰራ ይገባል” ሲል ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል። “እንደ ሀገር የተደቀኑብንን ችግሮች ጥልቀት እና ግዝፈት በግብታዊነት እና በእልኸኝነት የሚፈቱ ስላልሆኑ፤ በመነጋገር መግባባት ላይ መድረስ ብቸኛው አማራጫችን መሆኑን በማመን ሁሉም አካላት ሀገርን አስቀድመው በሰከነ መንገድ ሊነጋገሩ ይገባል” ሲልም ለችግሩ በውይይት መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስቧል። 

በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ባሉ የጸጥታ ችግሮች እና ሀገሪቱ የተደቀነባትን አደጋ በተመለከተ መፍትሔ ለማፈላለግ፤ ኢዜማ ተጨባጭ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ውይይት ከሚመለከታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር የማካሄድ ውጥን እንዳለውም አስታውቋል። ኢዜማ በዛሬው መግለጫው ከጸጥታ እና ተያያዥ ጉዳዮች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለውን የኑሮ ውድነት፣ የከተማ መሬት ወረራ እና የቤቶች ልማት ችግር ጉዳዮችን በስፋት ዳስሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)