በኤደን ገብረእግዚአብሔር
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚቀርበው ድጋፍ በመጠን፣ በፍትሃዊነት፣ በወቅታዊነት እና በተደራሽነት ረገድ “ከፍተኛ ጥያቄ” ማስነሳቱን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ። በአፋር ክልል በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች የሚደረግላቸው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ድጋፍም “በቂ እና ተመጣጣኝ” አለመሆኑን ተቋሙ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይህን ያስታወቀው፤ በአማራ እና አፋር ክልሎች ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ያለውን የእርዳታ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልሶ የማቋቋም ስራዎችን አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዚያ 11፣ 2014 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። እነዚህ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ በሁለቱ ክልሎች “ዳሰሳዊ ቁጥጥር” ማካሄዱን የገለጸው ተቋሙ፤ በቅኝቱ የደረሰባቸውን ግኝቶችም ይፋ አድርጓል።
ተቋሙ ዳሰሳዊ የቁጥጥር ቅኝቱን ያካሄደው አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና መስሪያ ቤት እና ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የተካተቱባቸው አራት ቡድኖችን ወደ ሁለቱ ክልሎች በማሰማራቱ መሆኑ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። ከእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ሶስቱ በአማራ ክልል ስር በሚገኙ ሰባት ዞኖች በመጓዝ ቅኝቱን ያካሄዱ ሲሆን ቀሪው ቡድን በአፋር ክልል ሃውሲ እና ፋንቲ ዞኖች በመገኘት ምልከታዎችን ማድረጉ ተገልጿል።
በአማራ እና አፋር ክልሎች ባሉ አካባቢዎች ከመጋቢት 14 እስከ ሚያዚያ 3 ባሉት ቀናት በተደረገው በዚሁ ቅኝት፤ በሁለቱም ክልሎች ሞት፣ የአካል መጉደል እና ቁሳዊ ውድመት መድረሱ በዳሰሳው መረጋገጡን ተቋሙ አስታውቋል። የዳሰሳዊ የቁጥጥር ግኝቱ ከዚህም በተጨማሪ በአማራ ክልል በጦርነቱ ሳቢያ በርካታ ህጻናት ወላጅ አልባ እንዲሆኑ እንደተገደዱ እንደዚሁም በእናቶች፣ ልጃገረዶች፣ ወንዶች እና አረጋውያን ላይ የመደፈር እና ጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን አመልክቷል።
በሁለቱም ክልሎች የትምህርት ፣ የጤና፣ የባንክ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የቴሌኮም እንዲሁም ሌሎች ተቋማቶች ላይ ውድመት መድረሱም በዳሰሳዊ የቁጥጥር ግኝቱ ላይ ተጠቅሷል። በሁለቱ ክልሎች የወደሙ ተቋማትን በማደራጀት እና የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ በማቋቋም ረገድ በተለያዩ አካላት ጥረቶች ቢደረጉም አሁን ከሚደረገው በላይ መሰራት እንዳለበት በግኝቱ ላይ ተመላክቷል።
በአማራ ክልል ብቻ በተለያየ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ቋሚ ድጋፍ የሚሹ 1.8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንዳሉ የጠቆመው ግኝቱ፤ ለእነዚህ እርዳታ ፈላጊዎች እየቀረበ የሚገኘው ድጋፍ ላይ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል። በህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የህጻናት ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰብለወርቅ ታሪኩ ፤ “የሚደረገው ድጋፍ ፍትሃዊነቱ፣ ወቅታዊነቱ፣ ተደራሽነቱ እና መጠኑ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥያቄን አስነስቷል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በመሰራጨት ላይ የሚገኘው የእርዳታ መጠን፤ በፌደራልም ሆነ በአማራ ክልል ደረጃ ተቀባይነት ያለውን መስፈርት የሚያሟላ እንዳልሆነ ወ/ሮ ሰብለወርቅ ገልጸዋል። አንድ ግለሰብ በህይወት ለመኖር በቀን ያስፈልገዋል ተብሎ የሚገመተው 2100 ኪሎ ካሎሪ እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ሆኖም በአብዛኛው ቦታ ላይ የሚሰራጨው እርዳታ 15 ኪሎ ስንዴ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። ለተፈናቃዮቹ በመስፈርቱ መሰረት ዘይት እና ጥራጥሬ ጭምር ሊሰጣቸው ይገባ እንደነበር አክለዋል።
መስፈርቱን የማያሟላው የእርዳታ መጠንም ቢሆን በወቅቱ እና በሚፈለገው ጊዜ “የሚዳረስ አይደለም” የሚል ቅሬታ እንደሚቀርብበት ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፍትሃዊነቱም ላይም ጥያቄ እንደሚነሳ የሚናገሩት ወ/ሮ ሰብለወርቅ፤ አንዳንድ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ላይ መካተት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይካተቱ መቅረታቸውን እና ማን እንደወሰደው ጭምር ሳይታወቅ ተከፋፍሏል እንደሚባል ከተረጂዎች ቅሬታ እንደሚቀርብ አብራርተዋል።
ዳይሬክተሯ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ አሁን የሚስተዋለውን ችግር “የበለጠ የሚያባብስ እና በጣም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል” ያሉትንም ጉዳይ አንስተዋል። ለተፈናቃዮች የሚደረገውን ድጋፍ የመመልከት እና ክትትል የማድረግ ኃላፊነት ያላባቸው የመንግስት ተቋማት የሰው ኃይል፣ የቢሮ ቁሳቁስ እና ሎጀስቲክ ያልተሟላላቸው መሆኑ ሊከናወን የሚገባውን የቁጥጥር ስራ አዳጋች ማድረጉን ዳይሬክተሩ አሳሳቢ ብለውታል።
የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንዱ በሕግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈጻሚው አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ጥራት፣ ቅልጥፍናና ግልጽነት ያለው መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ ነው። ተቋሙ የቀረቡለትን የአስተዳደር በደል አቤቱታዎች መሰረት በማድረግ ወይም በራስ ተነሳሽነት አሊያም በአስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ስልታዊ ምርመራ የማካሄድ ስልጣን እንዳለው በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)