ሩሲያ “ለሀገሪቱ ተሰልፈን መዋጋት እንፈልጋለን” ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ ኤምባሲዋ እንዳይመጡ አሳሰበች

በሃሚድ አወል

በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ፤ “ለሩሲያ ተሰልፈን መዋጋት እንፈልጋለን” የሚሉ ኢትዮጵያውያን ወደ ቅጽር ግቢው እንዳይመጡ ማሳሰቢያ ሰጠ። የኤምባሲው ቃል አቃባይ ማሪያ ቸርኑኪና ሩሲያ ኢትዮጵያውያንን “ለውትድርና እየመለመለች ነው” መባሉን “ሀሰት ነው” ሲሉ አስተባብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በጉዳዩ ላይ እስካሁን “የተጨበጠ ነገር” እንደሌለው አስታውቋል።

ሩሲያ ከጎረቤቷ ዩክሬን ጋር ለገባችበት ጦርነት “ወታደር እየመለመለች ነው” መባሉን የሰሙ ኢትዮጵያውያን ትላንት እና ዛሬ በአዲስ አበባ ቀበና አካባቢ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ለምዝገባ መሰለፋቸው አነጋጋሪ ሆኗል። እስከ ቀትር ድረስ ብቻ በቆየው የትላንቱ ሰልፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መመዝገባቸው የተነገረ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም 250 ገደማ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ መልኩ ከኤምባሲው ደጃፍ ለምዝገባ ሲጠባበቁ ታይተዋል።

በቦታው የነበሩ አብዛኛዎቹ ተመዝገቢዎች የቀድሞ ወታደሮች መሆናቸውን በስፍራው ለነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያኑ አመልካቾች በኤምባሲው በር ላይ መሰለፍ የጀመሩት ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ መሆኑን በስፍራው የነበሩ ሰዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ለ20 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ አየር ኃይል ያገለገሉ አንድ ጡረተኛ ወደ ኤምባሲው የመጡት፤ እየተካሄደ ባለው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ላይ ከሩሲያ ጎን ተሰልፎ ለመዋጋት እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እኚሁ የቀድሞ አየር ኃይል አባል፤ ጦርነቱ ሲያበቃ ወደ ሌሎች አውሮፓ ሀገራት የመጓዝ ሀሳብ እንዳላቸውም ተናግረዋል። “ጦርነት መቼም ዝንተ ዓለም አይቀጥልም፤ ካለቀ በኋላ ወደ ሌላ ሀገር ሄደህ እድልህን መሞከር ነው” ሲሉም ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ወደ ሀገር ቤት የመመለስ እቅድ እንደሌላቸው ጠቁመዋል። 

የሜትር ታክሲ (ራይድ) በማሽከርከር የሚተዳደር አንድ የቀድሞ ወታደር በበኩሉ ወደ ሩሲያ ኤምባሲ ለመመዝገብ የመጣው ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ሽሽት እንደሆነ ይናገራል። “እዚህ በጣም ብዙ ነገር ያስጠላኛል። አሁን ያለው ወቅታዊ  ፖለቲካ ምቹ አይደለም። ውጤት የሌለው ጦርነት እዚህ ከማካሄድ፤ እዚያ ሄደህ ውጤት ያለው ማድረግ ይሻላል” ሲል አቋሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። 

የ34 ዓመቱ የቀድሞ ወታደር ከዚህ ምክንያቱ በተጨማሪም፤ ሩሲያ በዓለም አቀፍ መድረክ በቅርብ ጊዜ ለኢትዮጵያ ያደረገችውን ውለታ ለመመለስ “የወታደር ምልመላው” ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ይናገራል። “ይህችን ሀገር ከአሜሪካ ሴራ የታደገቻት ሩሲያ ናት። እሷ ለእኛ ውለታ ውላለች፤ እኛም መዋል አለብን። የእኛ መንግስት አይደለም ተመላሽ፤ ካለው ወታደርም መስጠት አለበት” ብሏል። 

ጡረተኛው የአየር ኃይል አባሉም ሆነ ጎልማሳው ወታደር፤ እንደ ሌሎች አመልካቾች ሁሉ የስራ ማስረጃዎቻቸውን የያዙ ሰነዶችን በፖስታ ይዘው፤ ተራቸው እስኪደርስ ድረስ በሩሲያ ኤምባሲ ደጃፍ ለሰዓታት በትዕግስት በሰልፍ ሲጠባበቁ ቆይተዋል። አብዛኞቹ አመልካቾች ከውትድርና የተሰናበቱበት የምስክር ወረቀት እና ከውትድርና አገልግሎት ጋር የተያያዙ ሌሎች ሰነዶችን እንዲሁም የነዋሪነት መታወቂያዎችን ይዘው እንደነበር የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። 

ተሰልፈው ተራቸውን የሚጠብቁ ግለሰቦች ወደ ሩሲያ ኤምባሲው ቅጽር ግቢ ከመግባታቸው በፊት ሰነዶቻቸውን በሚታይ መልኩ እንዲያዘጋጁ በኤምባሲው በሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ማሳሰቢያ ሲሰጣቸውም ዘጋቢው ታዝቧል። ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቃላቸውን የሰጡ አመልካቾች፤ ወደ ኤምባሲው ቅጽር ግቢ ከገቡ በኋላ በኤምባሲው ሰራተኞች እንደተመዘገቡ እና ሰነዶቻቸው ኮፒ ተደርገው እንደተመለሱላቸው ገልጸዋል።   

በዚህ መልክ ሲካሄድ የቆየው ምዝገባ፤ በአንድ ሩሲያዊ የኤምባሲው ባልደረባ አማካኝነት ከቀኑ አምስት ሰዓት ገደማ ከተላለፈ ማሳሰቢያ በኋላ እንዲቋረጥ ተደርጓል። ስማቸውን እና የስራ ድርሻቸውን ያልገለጹት እኚህ የኤምባሲ ባልደረባ፤ በቦታው ለተገኙት ኢትዮጵያውያን በአስተርጓሚ ባስተላለፉት መልዕክት “የሩሲያ መንግስት በቂ ጦር አለው። የተመዘገባችሁት ዝርዝራችሁ እኛ ጋር ስላለ አስፈላጊ ከሆነ እንጠራችኋለን” ብለዋል። 

ሩሲያዊው የኤምባሲ ሰራተኛ አጭር ማሳሰቢያቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት፤ ወደ ኤምባሲው ቅጽር ግቢ ገብተው መመዝገብ ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን አመልካቾች የሰነዶቻቸውን ፎቶ ኮፒ ሰጥተው መሄድ እንደሚችሉ ጠቁመዋቸዋል። ይህንን ጥቆማ ተከትሎም በርከት ያሉ አመልካቾች ከውትድርና የተሰናበቱበትን የምስክር ወረቀት እና የቀበሌ መታወቂያ ፎቶ ኮፒ ለኤምባሲው የጥበቃ ሰራተኞች ሰጥተው ሲሄዱ ተስተውለዋል። 

ምዝገባውን ሲያስተባብሩ እና የግለሰቦችን ሰነዶች ሲቀበሉ የነበሩት የኤምባሲው የጥበቃ ሰራተኞች ጋዜጠኞች እና መንገደኞች ፎቶ እንዳያነሱ እና ቪዲዮ እንዳይቀርጹ ክልከላ ሲያደርጉ ነበር። ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ገደማ በስፍራው የተገኙ የአንድ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያ የካሜራ ባለሙያ እና ሪፖርተርም የዚሁ ክልከላ ሰለባ ሆነዋል። 

የቴሌቪዥን ጣቢያው የካሜራ ባለሙያ ለቀረጻ በሚዘጋጅበት ወቅት በኤምባሲው የጥበቃ ሰራተኞች ተይዞ ወደ ኤምባሲው በር ሲወሰድ በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። የሚሰራበት የመገናኛ ብዙሃን ተቋም እና የራሱም ስም እንዳይጠቀስ የጠየቀው የካሜራ ባለሙያ፤ የኤምባሲው የጥበቃ ሰራተኞች ይዘው ያቆዩት የካሜራው ሜሞሪ ካርድ ባዶ መሆኑን እስኪያረጋግጡ እና በመታወቂያው ላይ ያሉ መረጃዎቹን ጽፈው እስኪያጠናቅቁ ድረስ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። የጥበቃ ሰራተኞቹ ምዝገባውን የተመለከተ ዜና እንዳያስተላልፍ እንዳስጠነቀቁትም ገልጿል።  

በትላትናው እና በዛሬው ዕለት በሩሲያ ኤምባሲ ደጃፍ የተስተዋለውን የአመልካቾች ምዝገባ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የኤምባሲው ቃል አቃባይ ማሪያ ቸርኑኪና፤ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ኤምባሲው የመጡት በውትድርና ለመ’መልመል ሳይሆን፤ “ድጋፋቸውን ለመግለጽ እና በሚችሉት መንገድ ለመርዳት ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

ወታደራዊ ምልመላ ከሌለ፤ የኤምባሲው ሰራተኞች ሰነዶችን ሲቀበሉ እና ምዝገባ ሲያካሄዱ የነበሩት ለምን እንደሆነ የተጠየቁት ቃል አቃባዩዋ፤ “የህዝቡን ፍላጎት ችላ ማለት አልፈለግንም” ብለዋል። “ወደ ኤምባሲው ቅጽር ግቢ ሲገቡ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አመልካቾች የውትድርና አገልግሎት የምስክር ወረቀት ይዘው ነበር። ይህ ለምን ሆነ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ማሪያ ቸርኑኪና፤ “ለምን እነዚህን ሰነዶች እንዳመጡ አላውቅም። ምናልባት የመቀጠር ተስፋ እና ፍላጎት ስላላቸው ይሆናል” ሲሉ መልሰዋል። 

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትን አቋም በተመለከተ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባዩ ዲና ሙፍቲ “ተቀንጭቦ ከሚወራው ውጭ የተጨበጠ ነገር አልያዝኩም” ብለዋል። “ምንድን ነው ያለው? የሚለውን ከእነሱም ማጣራት ይጠይቃል፤ ምን እንደሆነ እየተከታተልነው ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ዲና፤ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ጉዳዩን በተመለከተ የሩሲያ ኤምባሲን በይፋ አለማናገሩን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)