ኢትዮ ቴሌኮም የ“ቴሌብር” አገልግሎቱን ለመጠቀም እንዲችሉ ከ20 ተቋማት ጋር ስምምነት ሊያደርግ ነው

በኤደን ገብረእግዚአብሔር 

ኢትዮ ቴሌኮም ከ20 ተቋማት ጋር “ቴሌብር” በተባለው የዲጂታል ግብይት አገልግሎቱ አማካኝነት ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ። ከድርጅቱ ጋር በቅርቡ ስምምነት ከሚፈጽሙት ተቋማት ውስጥ ስምንቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መሆናቸው ተገልጿል።  

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቱ ይህንን የገለጸው፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጥምረት የጀመረውን የበረራ ትኬት ግዢ አገልግሎት ባበሰረበት ወቅት ነው። ሁለቱ መንግስታዊ ተቋማት በጥምረት የጀመሩትን አገልግሎት ይፋ ያደረጉት፤ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 12፣ 2014 በተካሄደ መርሃ ግብር ላይ ነው። 

አዲሱ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት አገልግሎት፤ የአየር መንገዱ ደንበኞች “ቴሌብር” የተባለውን የሞባይል መተግበሪያ (አፕልኬሽን) በመጠቀም አሊያም ለአገልግሎቱ የተመደበውን የስልክ ቁጥር በመጠቀም የሀገር ውስጥ ጉዞ ትኬቶችን መግዛት የሚያስችላቸው ነው። ከየካቲት 7፤ 2014 ጀምሮ በሙከራ ደረጃ ሲከናወን በቆየው በዚህ አገልግሎት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የሀገር ውስጥ የበረራ ትኬቶችን መሸጥ እንደቻለ በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል።

ኢትዮ ቴሌኮም እና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንኑ አገልግሎት በተሟላ መልኩ ለደንበኞች መስጠት የሚያስችላቸውን ስምምነት በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተፈራርመዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት የተቋሙ ዋና የንግድ ኦፊሰር አቶ ለማ ያዴቻ ናቸው። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩም በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።  

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ከፊርማ ስነ ስርዓቱ አስቀድመው ባደረጉት ንግግር የሚመሩት ተቋም “የዲጂታል ለውጥ ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ” መሆኑን ገልጸዋል። የዲጂታል ግብይት አገልግሎትን ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ኩባንያዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰል ጥምረቶችን ለመፍጠር በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ከ49 ተቋማት ጋር የ“ቴሌብር” የክፍያ አገልግሎትን የመጠቀም ስምምነት ፈጽሞ አገልግሎቱን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የ“ቴሌብር”ን አገልግሎት እየተጠቀሙ ከሚገኙ ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ አንድነት ፓርክ፣ የአርባ ምንጭ፣ የባህር ዳር እና የሀረር ከተሞች የውሃ አገልግሎት መስሪያ ቤቶች እንደሚገኙበት ድርጅቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።   

ኢትዮ ቴሌኮም በተመሳሳይ መልኩ ከ20 በላይ ከሚሆኑ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅርቡ ስምምነት ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆኑን ገልጿል። ከድርጅቱ ጋር በቅርቡ ስምምነት እንደሚፈራረሙ ከሚጠበቁ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የገቢዎች፣ የንግድና ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል። 

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ፣ የግብርና፣ የማዕድን እና የሰላም ሚኒስቴሮችም በቅርቡ የቴሌ ብር አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ ከተባሉ ተቋማት ዝርዝር ውስጥ ተካተተዋል። በየዕለቱ በርካታ ዜጎችን የሚያስተናግዱት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣ የኢሜግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን እና የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በቅርቡ ስምምነት ይፈጽማሉ ተብሏል። 

ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት “ቴሌብር” የተባለውን አገልግሎቱን የሚጠቀሙ 17.6 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት አስታውቋል። ድርጅቱ አገልግሎቱን ከጀመረበት ከግንቦት 2013 ጀምሮ ከ12.58 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ የገንዘብ ዝውውር ወይም ግብይት እንዳከናወነም ገልጿል። መንግስታዊው ድርጅት ከስምንት ዓለም አቀፍ የሃዋላ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ባለው ስምምነትም ከ34 ሀገራት ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ዝውውር መፈጸሙን አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)