ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌገበያ” የተሰኘ የሽያጭ አማራጭ ይፋ አደረገ

በኤደን ገብረእግዚአብሔር 

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹ ካሉበት ቦታ ሆነው የኩባንያውን አገልግሎቶች በቀላሉ ለመግዛት የሚያስችላቸውን አዲስ የሽያጭ አማራጭ መጀመሩን አስታወቀ። “ቴሌገበያ” የተሰኘው ይህ የሽያጭ አማራጭ፤ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎችን፣ የኢንተርኔት መጠቀሚያ ሞደሞችን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተርሚናሎችን እና ሌሎችንም የቴሌኮም አገልግሎቶችን ለመግዛት ያስችላቸዋል ተብሏል። 

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ አዲሱን የሽያጭ አማራጭ መጀመሩን ይፋ ያደረገው በአዲስ አበባ በተለምዶ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ቅርንጫፉ ዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 19፤ 2014 ባካሄደው መርሃ ግብር ላይ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌገበያ” ሲል የሰየመውን አዲሱን የሽያጭ አማራጭ የጀመረው አገልግሎቱን ለደንበኞች በስፋት ተደራሽ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል። 

በአሁኑ ወቅት ራሱ የሚያንቀሳቅሳቸው እና በአጋር ድርጅቶች በኩል አገልግሎት የሚሰጡ 731 የሽያጭ ማዕከላት እንዳሉት የገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም፤ የ“ቴሌገበያ” መጀመር ደንበኞች ወደ ሽያጭ ማዕከላቱ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ካሉበት ቦታ ሆነው የኩባንያውን ምርቶች እና አገልግሎቶች በቀላሉ ለመግዛት ያስችላቸዋል ተብሏል። የ“ቴሌገበያ” አገልግሎት በመጀመሪያ ምዕራፉ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የኩባንያው ደንበኞች ብቻ የቀረበ መሆኑን የገለጸው ኩባንያው፤ በሁለተኛው ምዕራፍ አገልግሎቱን ወደ ሌሎች የሃገሪቱ ከተሞች የማስፋት እቅድ እንዳለው አስታውቋል። 

የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች በ“ቴሌገበያ” ድረ ገጽ ላዘዙት የቴሌኮም ምርቶች እና አገልግሎቶች ክፍያ የሚፈጽሙት፤ “ቴሌብር” በተባለው የኩባንያው የዲጂታል ግብይት አገልግሎት አማካኝነት ይሆናል። በግንቦት 2013 የተጀመረውን የ“ቴሌብር” አገልግሎትን የሚጠቀሙ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ብዛት 17.6 ሚሊዮን መድረሳቸውን ኩባንያው ባለፈው ሳምንት ገልጾ ነበር። 

ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው መርሃ ግብሩ “አሻምቴሌ” የተሰኘ የደንበኞች ማበረታቻን አስተዋውቋል። “አሻምቴሌ”፤ የኩባንያው ደንበኞች የድምጽ ጥሪ፣ የኢንተርኔት እና የአጭር መልዕክት አገልግሎት በሚጠቀሙበት ጊዜ በሚሰበስቡት የነጥብ መጠን (point) መሰረት ሽልማቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። ይህን ማበረታቻ ለማግኘት የሚመዘገቡ ደንበኞች፤ በየሚያከማቹት ነጥብ የተለያዩ የስልክ ቀፎዎችን፣ ታብሌቶችን እና ላፕቶፖችን ለመግዛት የሚያስችላቸው እንደሆነ ኩባንያው ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)