የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ ጠየቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ ለፓርላማ ጥያቄ አቀረበ። ምክር ቤቱ ጥያቄውን ያቀረበው ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ሚያዚያ 18፤ 2014 በተወካዮች ምክር ቤት በተደረገ ውይይት ላይ ነው።

የማክሰኞው ውይይት የተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለጋራ ምክር ቤቱ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ነው። አፈ ጉባኤው ውይይቱን የጠሩት ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በቀረበ ጥያቄ ነው። የጋራ ምክር ቤቱ ገዢው ፓርቲን ጨምሮ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈ ነው። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የካቲት 22፤ 2014 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ማብራሪያ እንዲሰጡ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ምክር ቤቱ ይህን ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና ለአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤  የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለጊዜው ቆሞ በአጠቃላይ አካሄዱ ላይ በድጋሚ ውይይት እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።

የተወካዮች ምክር ቤት ለዚህ ደብዳቤ ይፋዊ ምላሽ ባይሰጥም፤ የፓርላማው አፈ ጉባኤ ስለ ምክክር ሂደቱ ማብራሪያ እንዲሰጡ የቀረበው ጥያቄ ግን ሁለት ወራት ዘግይቶም ቢሆን ተቀባይነት አግኝቷል። እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ በቆየው በትላንት በስቲያው ውይይት የተገኙት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የኮሚሽነሮቹን የአሰያየም ሂደት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በውይይቱ ላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እና ምክትል ሰብሳቢዋ ሂሩት ገብረስላሴ ተገኝተዋል። በተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ በተካሄደ በዚሁ ውይይት ላይ የገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ የጋራ ምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኘተው ጥያቄ እና አስተያየታቸውን ሀሳባቸውን አቅርበዋል።  

በውይይቱ ላይ የተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ፤ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ “ነፍጥ አንግበው እየታገሉ ያሉ” ቡድኖች እንዲሳተፉ መጠየቃቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በምክክሩ ይሳተፉ ዘንድ በቅድሚያ እነዚህ ቡድኖች በሂደቱ ላይ አመኔታ ሊኖራቸው እንደሚገባ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አስገንዝበዋል።

ታጣቂ ቡድኖቹ ነፍጥ አንስተው ከመንግስት ጋር ውጊያ የገጠሙት “የውይይት ዕድሉም ስላልነበረ ይፈጠራል ብለውም ስላላሰቡ ነው” የሚሉት ዶ/ር ራሄል፤ ሂደቱን ገለልተኛ በማድረግ እነዚህን ቡድኖች ወደ ምክክሩ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። “ነጻ እና ከምንም አይነት የፖለቲካ ጥገኝነት ገለልተኛ መሆኑን እነሱም ጭምር ማየት አለባቸው። አይተው ወደ ጠረጴዛ መምጣት አለባቸው” ሲሉ የሂደቱን ገለልተኛነት የጦር መሳሪያ ለታጠቁ ኃይሎች ጭምር መታየት እንዳለበት አሳስበዋል።  

“በተግባር ለኦነግ ሸኔም፣ ለህወሓትም እንደገና ደግሞ በየቦታው ግጭት ለሚፈጥሩ ይኼ አማራጭ መኖሩን እና አስተማማኝ እና የሚያምኑት አይነት መሆኑን ማሳየት አለብን። መተማመን [ላይ] ሲደረስ፤ እነሱ እራሳቸው እኮ ፈልገው እንዲመጡ ያደርጋቸዋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ‘የሚለው አለው’ ተብሎ የተዘረጋው መንገድ ቢረጋገጥ፤ ያለጥርጥር ሁሉም ፈቅዶ ይመጣል። የጋራ ምክር ቤቱ ጥያቄ [የታጠቁ አካላት] ፈቅደው የሚመጡበትን መንገድ እንድናመቻች ነው” ሲሉ ዶ/ር ራሄል የሂደቱ ተዓማኒ መሆን የሚኖረውን ፋይዳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

በውይይቱ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤው አቶ ታገሰ ጫፎ “ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ አካታች ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ exclude አይደረገም” ማለታቸውን የተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ሄኖክ ስዩም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አፈ ጉባኤው፤ “[ሀገራዊ ምክክሩ] አካታች ነው ማለት ሁሉም ቡድን እና ግለሰብ ይሳተፋል ማለት ነው። ዳር ሆኖ የሚመለከት የለም” ማለታቸውን ዶ/ር ሄኖክ ጨምረው ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ባለፈው ታህሳስ ወር በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀበት ወቅት፤ በምክክሩ የሚሳተፉ አካላት ጉዳይ የፓርላማ አባላትን ማከራከሩ ይታወሳል። ገዢው ብልጽግና ፓርቲን እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወክለው የተመረጡ የፓርላማ አባላት፤ በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት “በምክክሩ መካተት የለበትም” ሲሉ ጠንካራ አቋማቸውን አንጸባርቀው ነበር። 

ከሁለት ወር በፊት ታህሳስ 20፤ 2014 በጸደቀው የሀገራዊ ምክከር ኮሚሽን ማቋቋያ አዋጅ ላይ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ አካላት ማንነት በተመለከተ በግልጽ የሰፈረ ነገር የለም። አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ለፓርላማ በቀረበ የማብራሪያ ሰነድ ላይ ግን የተሳታፊዎቹ ማንነት በአዋጁ ላይ እንዲካተት ያልተደረገበት ምክንያት ተብራርቷል። 

“የምክክር ሂደቱን ተሳታፊዎች በተመለከተ፣ በየትኛው ደረጃ፣ በምን አይነት አካሄድ እና መስፈርት ተሳታፊዎች እንደሚመለመሉ የአሰራር ስርዓቱ በአዋጅ በዝርዝር ከሚቀመጥ ይልቅ፤ ለኮሚሽኑ ቢተው የተሻለ ነው የሚል አቋም ተወስዷል። ገለልተኛ እና ብቁ የሆኑ ኮሚሽነሮች ይህን አሰራር ቢዘረጉ እና ዝርዝር ጉዳዮችን በመመሪያ ቢወስኑ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ ስራ ለመስራት ይችላሉ ተብሎ ታምኗል”

– የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የማብራሪያ ሰነድ

“የምክክር ሂደቱን ተሳታፊዎች በተመለከተ፣ በየትኛው ደረጃ፣ በምን አይነት አካሄድ እና መስፈርት ተሳታፊዎች እንደሚመለመሉ የአሰራር ስርዓቱ በአዋጅ በዝርዝር ከሚቀመጥ ይልቅ፤ ለኮሚሽኑ ቢተው የተሻለ ነው የሚል አቋም ተወስዷል። ገለልተኛ እና ብቁ የሆኑ ኮሚሽነሮች ይህን አሰራር ቢዘረጉ እና ዝርዝር ጉዳዮችን በመመሪያ ቢወስኑ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ ስራ ለመስራት ይችላሉ ተብሎ ታምኗል” ሲል የማብራሪያ ሰነዱ ምክንያቱን አትቷል። 

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ኮሚሽኑ “በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን ግልጽ በሆኑ መሥፈርቶች እና የአሠራር ሥርዓት መሠረት ይለያል። በምክክሮች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል። ይህን የተመለከተ ዝርዝር መመሪያም ያወጣል” ሲል ደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)