አቶ ዮሃንስ ቧያለው ከውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተርነት ኃላፊነታቸው ተነሱ

– ዶ/ር ደሳለኝ አምባው ኢንስቲትዩቱን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተሹመዋል

በሃሚድ አወል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩትን ለአንድ ዓመት ከስምንት ወር በኃላፊነት የመሩትን አቶ ዮሃንስ ቧያለውን ከኃላፊነታቸው አነሱ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአቶ ዮሃንስ ምትክ በአማራ ክልል በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሰሩትን ዶ/ር ደሳለኝ አምባውን በዋና ዳይሬክተርነት መሾማቸውን የተቋሙ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ ገልጸዋል።

አቶ ዮሃንስ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ከትላንት ሐሙስ ሚያዚያ 20፤ 2014 ጀምሮ መሆኑን እኚሁ የተቋሙ ምንጭ ተናግረዋል። ተሰናባቹ ዋና ዳይሬክተር እስከ ትላንት ድረስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ቅጽር ግቢ በሚገኘው ጊዜያዊ ቢሯቸው በስራ ገበታቸው ላይ እንደነበሩም አክለዋል። 

በ1988 ዓ.ም የተቋቋመው እና በየጊዜው በሚደረጉ የመዋቅር ለውጦች ምክንያት በተለያዩ ስያሜዎች ሲጠራ የቆየው የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሆን የተደረገው ከነሐሴ 2012 ጀምሮ ነው። “የስትራቴጂ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት” የተሰኘ ስያሜውን አሁን ወደያዘው መጠሪያው ባለፈው መስከረም ወር የቀየረው ተቋሙ፤ አዲስ የተሰጠውን ህንጻ በማደስ ላይ በመሆኑ አቶ ዮሃንስ ቧያለውን ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎች ስራቸውን ሲያከናውኑ የቆዩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ በተሰጧቸው ቢሮዎች ነበር። 

አቶ ዮሃንስ ኢንስቲትዩቱን በዋና ዳይሬክተርነት እንደሚሩ በነሐሴ 2012 ዓ.ም ሲሾሙ፤ ተቋሙ የሚጠራው “የስትራቴጂ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት” በሚለው ስያሜው ነበር። የስትራቴጂ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት “ስትራቴጂያዊ በሆኑ የሰላም እና ደህንነት፣ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ፣ ውቅረ መንግሥት እና ሀገር ግንባታ ጉዳዮች ጥናት፣ ምርምር እና ትንተና በማከናወን አማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማማከር እና ምክረ ሃሳብ ማቅረብ እንዲሁም ስልጠናዎችን የመስጠት” ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነበር።

ባለፈው መስከረም ወር የጸደቀው የፌደራል አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ፤ የስትራቴጂ ጉዳዮች ኢንስቲትዩትን እና የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትን እንዲዋሃዱ በማድረግ የአሁኑ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም አድርጓል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር የነበረው የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት፤ የኢትዮጵያን አዳዲስ ዲፕሎማቶች አሰልጥኖ በአጥጋቢ ሁኔታ ላጠናቀቁ የድህረ-ምረቃ ዲፕሎማ ሲሰጥ የቆየው ተቋም ነው። 

አቶ ዮሃንስ ቧያለው ተቋሙ በአዲስ መልክ ሲዋቀር “ትልቅ አስተዋጽኦ” ማበርከታቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ኢንስቲትዩቱ “እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም” የሚሉት የተቋሙ ሰራተኛ፤ “አሁን ለሀገሪቱ የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ትላልቅ የምርምር ስራዎችን እየሰራን ነው። ለእነዚህ ስራዎች ደግሞ የእርሳቸው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው” ሲሉ የአቶ ዮሃንስን አስተዋጽኦ አብራርተዋል።

ተቋሙን በአዲስ መልክ በማደራጀት ረገድ ከአቶ ዩሃንስ ጋር አብረው የሰሩት፤ የቀድሞው የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር እና የአሁኑ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር በከር ሻሌ የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደነበራቸው እኚሁ ሰራተኛ አክለዋል። የቀድሞው የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር በከር የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር ሆነው የሰሩት ለአንድ ዓመት ያህል ነው። 

የቀድሞው የአማራ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዮሃንስ ቧያለው፤ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩትን በሰው ኃይል በማደራጀትም ስማቸው በበጎ ይነሳል። ተሰናባቹ ዋና ዳይሬክተር በስራ ዘመናቸው 30 ገደማ ተመራማሪዎችን ወደ ተቋሙ ማምጣታቸውን የኢንስቲትዩቱ ሰራተኛ ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። ከእነዚህ ተመራማሪዎች መካከል 20 ገደማ የሚሆኑት የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው መሆኑን የተቋሙ ሰራተኛ በጥሩ ጎን አንስተዋል። 

የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩትን የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት ዶ/ር ደሳለኝ አምባውም፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፌደራሊዝም እና አስተዳደር ጥናት ከአንድ ዓመት በፊት በየካቲት 2013 የዶክትሬት ዲግሪ ያገኙ ናቸው። ዶ/ር ደሳለኝ በአማራ ክልል ከዞን አስተዳደር ጀምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለዓመታት አገልግለዋል።  

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የሰሩት አዲሱ ተሿሚ፤ ከዚያ አስቀድሞ የክልሉ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት መርተዋል። በ2003 ወደ ፌደራል የስልጣን እርከን ከፍ ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ለአምስት ዓመታት ገደማ በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታነት ተሹመው ሰርተዋል። ከ2008 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል፤ በቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስቴር በተመሳሳይ የስልጣን እርከን ሲሰሩ ቆይተዋል። 

እንደ ዶ/ር ደሳለኝ ሁሉ አቶ ዮሃንስ ቧያለውም በፌደራል ተቋም ተመድበው ከመስራታቸው በፊት በአማራ ክልል በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል። በክልሉ ገዢ ፓርቲ ውስጥም በቁልፍ የስልጣን ቦታዎች ሰርተዋል። የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ ለረጅም ዓመታት ሲጠቀምበት የቆየውን የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የተሰኘው ስያሜውን በመስከረም 2011 ወደ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሲለውጥ፤ አቶ ዮሃንስ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ። 

በአዴፓ ውስጥ የምክትል ሊቀመንበርነት ስልጣን የነበራቸው አቶ ዮሃንስ፤ ፓርቲው ራሱን አክስሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን የአሁኑን ብልጽግና ፓርቲ እስከመሰረተበት ህዳር 2012 ድረስ በኃላፊነታቸው ቆይተዋል። ከብልጽግና ፓርቲ ምስረታ በኋላ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤትን ለአራት ወራት መርተዋል። 

አቶ ዮሃንስ ቧያለው በፌደራል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣን የተሰጣቸው በየካቲት 2012 ነበር። የቀድሞ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት አቶ ዮሃንስ፤ ሹመቱን “አልቀበልም” ማለታቸው በወቅቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም። አቶ ዮሃንስ ሹመቱን ላለመቀበል በዋና ምክንያትነት ያቀረቡት በወቅቱ የነበረው የአካዳሚውን ስያሜ ነው። 

“በዚያ ተቋም መስራት ቢኖርብኝ እንኳን አሁን ባለው ብራንድ መስራት የምችልበት ሁኔታ ስላልሆነ የቀረበውን ሹመት ለመቀበል ያስቸግረኛል። አሁን ባለው ስያሜ እና ብራንድን ለማገልገል ዝግጁ አለመሆኔን ለቦርዱ ሰብሳቢ ገልጫለሁ” ሲሉ አቶ ዮሃንስ በወቅቱ ምክንያታቸውን ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል። የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ፤ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ስያሜውን ወደ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ መቀየሩ ይታወሳል። 

አቶ ዮሃንስ ቧያለው በኢህአዴግ የስልጣን ጊዜ ጭምር አባል ከሆኑበት ፓርቲ የተቃረኑ ሃሳቦችን በማራመድ ይታወቃሉ። በዚህ አካሄዳቸው ምክንያት ይዘውት ከነበረው ስልጣን እንዲነሱ በተደረጉበት ወቅት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ማገልገል ጀምረው ነበር። አቶ ዮሃንስ በሰላም እና ደህንነት ጥናት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከዚሁ ዩኒቨርስቲ ነው።  

እስካለፈው መጋቢት ወር ድረስ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ዮሃንስ፤ ገዢውን ፓርቲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በተመለከተ በየጊዜው የሰጧቸው አስተያየቶች ሲያነጋግሩ ቆይተዋል። ብልጽግና ፓርቲ ባለፈው መጋቢት ወር ካካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላም፤ አባል የሆኑበት ፓርቲ ላይ ጠንካራ ትችቶችን በመገናኛ ብዙሃን ሲያቀርቡ ተደምጠዋል።  

አቶ ዮሃንስ ከአንድ ሳምንት በፊት ከአንድ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ብልጽግና ባሰብነው መልኩ እየሄደ ነው ማለት አይቻልም” ሲሉ ፓርቲያቸውን ወቅሰዋል። “ብልጽግናን የፈጠርነው የብሔር ድርጅቶች ለማክሰም እንጂ የብሔር ድርጅቶች እንዲጎለብቱ እና የአንድ ክልል ሰዎች እንዲሰባሰቡ አይደለም። መክሰሙ ትክክል ነበር ግን ችግሩ አሁንም ከብሔር አጥር መውጣት አልተቻለም” ሲሉም ፓርቲያቸው አጋጥሞታል ያሉትን ችግር በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው አስረድተው ነበር። 

ተሰናባቹ ሹመኛ በቃለ ምልልሶች ካነሷቸው ትችቶች እና ወቀሳዎች ባለፈ፤ አባል በሆኑበት የአማራ ክልል ምክር ቤትም የሰሜኑን ጦርነት እና ከክልሉ ውጭ ያሉ የአማራ ተወላጆችን የተመለከቱ ጠንክር ያሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። አቶ ዮሃንስ ባለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር የክልሉ ምክር ቤት “ህዝባችንን ለዳግም ጥቃት እንዳያጋልጠው” ሲሉ አሳስበው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)