በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በመጪው ሰኔ 11 እና 12፤ 2014 በሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ፓርቲውን በመሪነት እና በሊቀመንበርነት የሚመሩ አመራሮችን እንደሚመርጥ አስታወቀ። ፓርቲው በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የሰፈረውን “የአንድ ሰው፣ አንድ ድምጽ የምርጫ መርህን” ለጊዜው አስቀርቶ፤ የመሪዎቹን ምርጫ በቀጥታ በጠቅላላ ጉባኤ አማካኝነት ለማድረግ የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ ለጉባኤው አባላት እንደሚያቀርብም ተገልጿል።
ኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤውን የጠራው፤ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በሚደነግገው መሰረት በሶስት ዓመት አንዴ መደበኛ ጉባኤ ማከናወን ስለሚገባው መሆኑን ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 2፤ 2014 በዋና ጽህፈቱ ቤቱ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል። በመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ የኢዜማ መሪ፣ ምክትል መሪ፣ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ዋና ጸሐፊ እና የፓርቲው የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ እንደሚመረጡ ፓርቲው በዛሬው መግለጫው ይፋ አድርጓል።
በግንቦት 2011 የተመሰረተው ኢዜማን ላለፉት ሶስት ዓመታት በመሪነት እያገለገሉ የሚገኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሲሆኑ የምክትል መሪነት ስልጣን ያላቸው ደግሞ አቶ አንዷለም አራጌ ናቸው። በግንቦት 2011 በጸደቀው የኢዜማ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት፤ ፓርቲው በሀገር አቀፍ ምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን ከያዘ የፓርቲው መሪ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል።
ኢዜማ በምርጫ ወደ ስልጣን ካልመጣ የፓርቲው መሪ “ዋና” አሊያም “ዋና ያልሆነ” የፓርላማ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እንደሚሆን በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተቀምጧል። የፓርቲው መሪ ለቦታው መመረጥ የሚችለው ለሁለት ተከታታይ የፓርላማ ዘመን መሆኑን የሚጠቁመው መተዳደሪያ ደንቡ፤ ምርጫው የሚከናወነውም “በአንድ ሰው፣ አንድ ድምጽ የምርጫ መርህ” እንደሆነ አስፍሯል።
የፓርቲው መሪዎች በደንቡ መሰረት የሚመረጡ ከሆነ ድምጽ የሚሰጡት በየምርጫ ክልሉ የሚገኙ የኢዜማ አባላት በሙሉ እንደሚሆኑ በዛሬው መግለጫ ላይ ያነሱት የፓርቲው አስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስዩም መንገሻ፤ ሂደቱን ለማከናወን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለማከናወን የሚከተላቸውን አካሄዶች በሙሉ መከተል እንደሚጠይቅ በአጽንኦት አስረድተዋል። በሁሉም የምርጫ ክልሎች፤ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በሚያዝዘው እና በምርጫ ቦርድ አካሄድ መሰረት ሂደቱ ይካሄድ ቢባል የቀረው ጊዜ እንደማይበቃም ጠቁመዋል።
“በሀገራችን በአሁን ሰዓት ባሉት 358 አካባቢ የምርጫ ክልሎች አስመራጮች መቋቋም አለባቸው። የምርጫ ቅስቀሳው፣ ምረጡኝ የሚሉበት ስርዓት የሚስተናገደው በዚያ ነው። ስልጠናዎች ይካሄዳሉ፣ አስመራጮች፣ አስፈጻሚዎች ያስፈልጋሉ። በጣም በርካታ ስራ ነው የሚሰራው። ይሄንን ለማከናወን ደግሞ አሁን ያለን ጊዜ አይበቃንም። ምናልባት ስምንት ወር፣ ምናልባት 10 ወር፣ ምናልባት አንድ ዓመት ያስፈልጋል” ሲሉ ሂደቱ የሚጠይቀውን ጊዜ አብራርተዋል።፡
ከስምንት ወር እስከ አንድ ዓመት ድረስ ጊዜ ተወስዶ ሂደቱን የተከተለ የፓርቲ መሪዎች ምርጫ ቢካሄድ፤ በመተዳደሪያ ደንቡ የተቀመጠውን የሶስት ዓመት የጠቅላላ ጉባኤ የስልጣን ዘመን የሚጥስ መሆኑን የፓርቲው አስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተናግረዋል። በኢዜማ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡት የኢዜማ መሪ እና ምክትል መሪ የስልጣን ዘመን የሚቆየው በቀጣዩ ወር እስከሚካሄደው መደበኛ ጉባኤ ድረስ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ስዩም፤ ለዚህ ችግር ጊዜያዊ መፍትሔ የሚሰጥ የውሳኔ ሃሳብ ለጠቅላላ ጉባኤ ይቀርባል ብለዋል።
“ጠቅላላ ጉባኤው እንደምታውቁት የመጨረሻው የስልጣን አካል ነው። በማንኛውም ፓርቲ ውስጥ በእኛ ፓርቲ ጭምር የመጨረሻው የስልጣን አካል ስለሆነ፤ የተነሱትን ሃሳቦች ጠቅሰን ይሄን ጉዳይ እናቀርብለታለን። ጉባኤው በሚሰጠን አቅጣጫ መሰረት የመሪ ምርጫ ይደረጋል ማለት ነው” ሲሉ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ቀጣይ ሂደቶች ምን እንደሚመስሉ አስረድተዋል።
የፓርቲውን መሪ እና ምክትል መሪ አመራረጥን በሚመለከት በኢዜማ መተዳደሪያ ደንብ የተቀመጡ ድንጋጌዎች በደንብ ዘርዝር ተደርገው እንዲቀርቡ በምርጫ ቦርድ በኩል በቅርቡ በደብዳቤ መጠየቃቸውን አቶ ስዩም ጨምረው ገልጸዋል። ኢዜማ ዝርዝር የምርጫ ማስፈጸሚያውን በተመለከተ ከምርጫ ቦርድ ጋር ገና በንግግር ላይ መሆኑን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ትዕግስት ወርቅነህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዚህኛው ዙር “የአንድ ሰው፣ አንድ ድምጽ የምርጫ መርህ” የማይተገበር ከሆነ፤ ኢዜማ ያለ መሪ እንዳይቆይ ሲባል ጠቅላላ ጉባኤው በቀጥታ ድምጽ እንዲሰጥ ሊያደርግ የሚችል የውሳኔ ሃሳብ ሊቀርብ እንደሚችል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ጠቁመዋል። ጉዳዩ ከምርጫ ጋር ቦርድ ጋር በተያያዘ ገና በእንጥልጥል ላይ ስለሆነ የውሳኔ ሃሳቡን ሙሉ ይዘት “አሁን መናገር እንደማይችሉም” ጨምረው ገልጸዋል። በመጪው ሰኔ የሚሰበሰቡት የኢዜማ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት የፓርቲው መሪዎች ለዚህኛው ዙር ብቻ በቀጥታ እንዲመረጡ ከወሰኑ፤ ዕጩ አመራሮቹ ከጠቅላላ ጉባኤው መዳረሻ በፊት ለ19 ቀናት የምረጡኝ ቅስቀሳ የማድረጊያ ጊዜ ይሰጣቸዋል።
ፓርቲው መሪዎቹን ለመምረጥ አሁን ያጋጠመው ችግር በሊቀመንበር፣ በምክትል ሊቀመንበር፣ በጸሐፊ እና በፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ምርጫ ላይ የሚከሰት አለመሆኑን የኢዜማ ኃላፊዎች በዛሬው መግለጫቸው ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ለዚህም የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ በማስረጃነት ጠቅሰዋል። በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ለአራቱ የኃላፊነት ቦታዎች የሚመረጡ ግለሰቦች በጠቅላላ ጉባኤው በቀጥታ የሚመረጡ ናቸው።
የኢዜማን የዕለት ተዕለት ስራ በሙሉ ጊዜ የመምራት ኃላፊነት የተሰጠው ለፓርቲው ሊቀመንበር ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኃላፊነትን ተረክበው ፓርቲውን በመምራት ላይ የሚገኙት አቶ የሺዋስ አሰፋ ናቸው። ዶ/ር ጫኔ ከበደ ደግሞ የምክትል ሊቀመንበርነት ቦታውን ይዘው ቆይተዋል። ኢዜማን በአሁኑ ወቅት በዋና ጸሐፊነት በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ አበበ አካሉ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)