ምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጸጥታ ሁኔታን የሚገመግም የመረጃ ማሰባሰብ ሊያካሂድ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን የጸጥታ ሁኔታ የሚገመግም የመረጃ ማሰባሰብ ሂደት ሊጀምር ነው። ቦርዱ ለዚህ የመረጃ ማሰባሰብ የሚረዳውን እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቧቸው ቅሬታዎች ላይ የሚደረግ ምርመራን የተመለከተ ስብሰባ በዚህ ሳምንት እንደሚያካሄድ ገልጿል።

ምርጫ ቦርድ የሚያካሄደው ይህ የጸጥታ መረጃ ማሰባሰብ፤ በክልሉ ምርጫ ባልተደረገባቸው ቦታዎች ምርጫ ለማከናወን አስቻይ ሁኔታዎች መኖር አለመኖራቸውን የሚያመላክት ነው ተብሏል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት፤ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በክልሉ ጠቅላላ ምርጫ የተካሄደው በከፊል ነው። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአጠቃላይ ካሉት 22 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በአስራ ሰባቱ በሰኔ 2013 ምርጫ አልተካሄደም። በዚህም ምክንያት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ካሉት 99 መቀመጫዎች ውስጥ ስልሳ አምስቱ ምርጫ ሳይደረግባቸው ቀርቷል። 

ምርጫ ከተካሄደባቸው 34 መቀመጫዎች ውስጥ በስድስት ያህሉ በድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ በመወሰኑም፤ የክልሉ ምክር ቤት የስድስተኛው ዙር ምርጫ ተመራጮችን ማስተናገድ እንዳይችል ሆኗል። አሁን ክልሉን እያስተዳደረ የሚገኘው መንግስት የተሰየመው ከሰባት ዓመት በፊት በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ በተመረጡ የክልል ምክር ቤት አባላት ነው። 

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ባለፈው ታህሳስ ወር የክልሉን ቀሪ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ሲያደርግ ቢቆይም ባለፈው ጥቅምት ወር በመላው ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት ሂደቱን ለማቋረጥ መገደዱን አስታውቆ ነበር። ለስድስት ወራት ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሶስት ወራት ቆይታ በኋላ መነሳቱን ተከትሎ፤ ቦርዱ ባለፈው መጋቢት ወር የክልሉ ምርጫ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚወዳደሩ ፓርቲዎች፣ የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት እና የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ የሚከታተለው የኮማንድ ፖስት ተወካዮች በተገኙበት በዚህ ውይይት፤ ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት ማብራሪያ አቅርቦ ነበር። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ ግምገማ ቀርቦም ውይይት እንደተካሄደበት ቦርዱ ገልጿል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምርጫ ቦርድ ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ባገኘችው መረጃ መሰረት፤ “በየጊዜው የሚቀያየረውን የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ” የሚገመግም ተመሳሳይ ውይይት በዚያው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በዚህ ሳምንት ይካሄዳል። በዚህ ውይይት ላይ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በተመለከተ፤ ምርጫ ቦርድ የሚያካሄደውን ምርመራ የተመለከተ ጉዳይ ይነሳል ተብሎም ይጠበቃል።  

ቦርዱ ውይይቱን ለማካሄድ ለፓለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እና ለሌሎችም ተሳታፊዎች በደብዳቤ ይፋዊ ጥሪ አድርጓል። ምርጫ ቦርድ ይህን ውይይት ተከትሎ የጸጥታ ችግር አለባቸው በተባሉ የክልሉ ወረዳዎች ላይ መረጃዎችን የማሰባሰብ ሂደት እንደሚጀምርም ተነግሯል። በውይይቱ እና በመረጃ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ የተገኙ ውጤቶች ላይ ተመስርቶም ቦርዱ ምርጫውን በተመለከተ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች አስታውቀዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው እና ግጭቶች ከሚከሰቱባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ዋነኛው ነው። በክልሉ በመተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ ዞኖች በተደጋጋሚ ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በየጊዜው ሲፈናቀሉ ተስተውለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)