በሃሚድ አወል
በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ ከተካተቱ አራት ድርጅቶች ውስጥ የሶስቱ ክስ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 8፤ 2014 በችሎት ተነበበ። ክሳቸው የተነበበላቸው ትራንስ ኢትዮጵያ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር እና ሱር ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግ.ማህበር ናቸው።
በትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) ስር የሚተዳደሩ ሶስቱ ድርጅቶች፤ ከሌሎች 59 ተከሳሾች ጋር በጋራ ክስ የተመሰረተባቸው ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር ነበር። ከሶስቱ ድርጅቶች ውጭ ያሉት እና በቁጥጥር ስር የዋሉት 21 ተጠርጣሪዎች፤ በፍርድ ቤት ክስ ከተመሰረተባቸው ከአንድ ወር ገደማ በኋላ የቀረቡባቸው ሁለት ክሶች በችሎት ተነብቦላቸዋል።
የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን እና ምክትላቸው ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር (ሞንጆሪኖን) ጨምሮ 42 ተጠርጣሪዎችን የሚመለከተው የመጀመሪያው ክስ፤ “በኃይል፣ በዛቻ፤ በአድማ እና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ኢ-ህገመንግስታዊ ምርጫ በማካሄድ በሕገ መንግስት የተቋቋመን የክልል መንግስትን ለውጠዋል” የሚል ነው። ዛሬ ክሳቸው የተነበበላቸው ሶስቱን ድርጅቶች ጨምሮ 52 ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበው ሁለተኛው ክስ ደግሞ፤ የፌደራል መንግስትን በኃይል ለመለወጥ በማሰብ “በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት አድርሰዋል” በሚል የሚወነጅል ነው።
ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት፤ በህብረት እና ወንጀል ለማድረግ በማደም እንዲሁም በሽብር ድርጊት ተካፋይ መሆናቸው በክሱ ዝርዝር ላይ ሰፍሯል። በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት 21 ተከሳሾች ውስጥ ስድስቱ ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ክሳቸው በመንግስት እንዲቋረጥ በመደረጉ፤ ጉዳያቸውን ችሎት ፊት በመቅረብ እየተከታተሉ ያሉት 16 ግለሰቦች ናቸው።
ሶስቱ የንግድ ድርጅቶች “የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ‘የፌደራል መንግስት በጥገኛ ኃይል ቁጥጥር ስር ስለዋለ በማንኛውም መንገድ መመከት እና ከስልጣን ማውረድ ይኖርብናል’ በማለት የወሰነውን ውሳኔ ተቀብለው ተንቀሳቅሰዋል” የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ድርጅቶቹ ላይ የቀረበው የወንጀል ዝርዝር እንደሚያስረዳው፤ ድርጅቶቹ ለትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ የሰው ኃይል፣ መሳሪያ፣ አስፈላጊ ነዳጅ፣ ትጥቅ እና ስንቅ በማጓጓዝ እና በማከማቸት በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፈዋል።
ትራንስ ኢትዮጵያ የተባለው አንደኛው ተከሳሽ ድርጅት፤ 211 ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎቹን በመጠቀም የገንዘብ ግምቱ 177.9 ሚሊዮን ብር የሆነ 9.7 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ወደተለያዩ ስፍራዎች በማጓጓዝ ለወታደራዊ ጥቃት እንዲውል ማድረጉ ዛሬ በተነበበው ክስ ላይ ሰፍሯል። ትራንስ ኢትዮጵያ ነዳጅ ከማጓጓዝ ባለፈ 559 ሚሊዮን ብር በመመደብ በትግራይ ክልል ሰቲት ሑመራ፣ ሽሬ እንዳስላሴ፣ አቢ አዲ እና መሖኒ ከተሞች የነዳጅ ማከፋፈያ እና ዴፖዎች ሊያስገነባ እንደነበር በክሱ ተመላክቷል።
በመቀሌ ከተማ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ያለው መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ላይ የቀረበው ክስ ደግሞ “በመቀሌ የነዳጅ ዲፖ የተቀመጠ ነዳጅ በመዝረፍ [የትግራይ] ወታደራዊ ኮማንድ ለሚያደርሰው ጥቃት አገልግሎት እንዲውል” አድርጓል የሚል ነው። ድርጅቱ ነዳጁ ለወታደራዊ አገልግሎት እንዲውል፣ መቀሌ የሚገኝ ይዞታውን ነዳጅ ተቆፍሮ እንዲቀበርበት በመፍቀድ፣ የገንዘብ ግምቱ 258 ሚሊዮን የሆነ 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ በመዝረፍ ለጥቃት አገልግሎት እንዲውል ማድረጉ በክሱ ላይ ተብራርቷል።
ሌላኛው ተከሳሽ ሱር ኮንስትራክሽን ለትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ አገልግሎት የሚውሉ ምሽጎችን በመቆፈር፣ ተምቤን የሚገኝ የድርጅቱን ካምፕ የህወሓት አመራሮች እንዲያርፉበት በማድርግ ተከስሷል። ከዚህ ባለፈም የድርጅቱን ተሽከርካሪዎች ከባድ መሳሪያዎች፣ ምግብ፣ ትጥቅ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች እንዲሁም የህወሓት አመራሮችን እንዲያመላልሱ መፍቀዱ በክስ ንባቡ ወቅት ተደምጧል።
ድርጅቶቹ በተከሰሱበት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ጥፋተኛ ከተባሉ፤ ከ100 ሺህ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ቅጣት ይጠብቃቸዋል። በአዋጁ መሰረት ከተደነገገው ቅጣት በተጨማሪ፤ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ ጠያቂነት ወይም በራሱ ተነሳሽነት ድርጅቶቹ እንዲፈርሱ ወይም ንብረታቸው እንዲወርስ ሊወስን ይችላል።
በሶስቱ የንግድ ድርጅቶች ላይ የተከፈተው ክስ፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ዳኛ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 8፤ 2014 በንባብ ሲቀርብ፤ የድርጅቶቹ ሁለት ጠበቆች በአካል ሂደቱን ተከታትለዋል። ከጠበቆቹ መካከል አንደኛው የሆኑት አቶ ወንደወሰን በፍቃዱ፤ በመዝገቡ ውስጥ ለተካተቱ ሌሎች ደንበኞቻቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ለሶስቱም ድርጅቶች እንደሚያገለግል ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
ጠበቃው ከዚህ በፊት ባቀረቡት መቃወሚያ ላይ በመመርኮዝ ዐቃቤ ህግ ምላሽ መስጠት ይችል እንደውም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱ ይህን ጥያቄ በመቀበል፤ ዐቃቤ ህግ ከዚህ በፊት በቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ተመርኩዞ ምላሽ እንዲሰጥ ውሳኔ ቢያስተላልፍም፤ ጠበቆች ሀሳባቸውን በመቀየራቸው ችሎቱ ሌላ ትዕዛዝ ለማስተላለፍ ተገድዷል።
“ቀደም ሲል ያቀረብኩት መቃወሚያ ይያዝልኝ” የሚል ሀሳብ አቅርበው የነበሩት አቶ ወንድወሰን፤ ከሌላኛው ጠበቃ ታደለ ገብረመድህን ጋር ከመከሩ በኋላ አዲስ መቃወሚያ እንደሚያቀርቡ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። በዚህም ችሎቱ የክስ መቃወሚያቸውን ለማቅረብ ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ጠበቃ ታደለ በበኩላቸው የድርጅቶቹ ዋና መስሪያ ቤት ወደ መቀሌ መዘዋወሩን ለችሎቱ ገልጸው፤ ሰነዶችን ለማስመጣት እና የድርጅቶቹን ኃላፊዎች ለማነጋገር ጊዜ እንደሚፈጅ በመጥቀስ ችሎቱ አንድ ወር ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ችሎቱም የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል የክስ መቃወሚያቸውን ለሰኔ 13፤ 2014 እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)