በሃሚድ አወል
የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ያልሆነ ግለሰብ ያገኘውን መረጃ ከመስሪያ ቤቱ ኃላፊ ፍቃድ ውጭ ይፋ ካደረገ፤ በወንጀል ህግ እንዲጠየቅ የሚያደርግ የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። የአዋጅ ማሻሻያው፤ ከደህንነት መስሪያ ቤቱ የሚሰጥን መረጃ ጥቅም ላይ አለማዋል ቅጣት እንደሚያስከትልም ደንግጓል።
ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 11፤ 2014 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው ይህ የአዋጅ ረቂቅ፤ ከዘጠኝ ዓመት በፊት የወጣውን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ የሚያሻሽል ነው። በኢፈዲሪ የወንጀል ህግ መሰረት ተጠያቂ የሚያደርጉ ድንጋጌዎች የተካተቱበት አዲሱ አዋጅ፤ በነባሩ አዋጅ ላይ ያሉ ዘጠኝ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን አንድ አዲስ አንቀጽም እንዲጨመር አድርጓል።
የአዋጅ ረቂቁ ማሻሻያ ካደረገባቸው ድንጋጌዎች መካከል የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ስልጣን እና ተግባራት እንዲሁም አደረጃጀት የሚመለከቱት አንቀጾች ይገኙበታል። የደህንነት መስሪያ ቤቱን በዳይሬክተር ጄነራልነት የሚመሩትን ኃላፊ ስልጣን እና ተግባር የሚመለከተው አንቀጽም እንደዚሁ ማሻሻያ ተደርጎበታል።

የመስሪያ ቤቱን በጀት፣ የግዢ እና ንብረት አስተዳደር የሚመለከቱ አንቀጾች ላይ ተጨማሪ ንዑስ አንቀጾች የጨመረው የአዋጅ ረቂቁ፤ የተቋሙ ሰራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሰረት እንዲመራ የሚያደርግ አዲስ አንቀጽ እንዲካተት አድርጓል። በነባሩ አዋጅ ላይ “ተጠያቂነትን” እና “የመተባበር ግዴታን” በተመለከተ የተቀመጡ ሁለት አንቀጾች ላይም ተጨማሪ ንዑስ አንቀጾችን አክሏል።
በ2005 ዓ.ም የወጣው ነባሩ አዋጅ “ተጠያቂነትን” በተመለከተ በዘረዘረበት ክፍሉ ላይ፤ “ማንኛውም የአገልግሎቱ ሰራተኛ በአዋጅ [ለመስሪያ ቤቱ] የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ያለ አግባብ ከተገለገለ ወይም፤ አገልግሎቱ በሚያወጣው የሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን መመሪያ የተመለከቱ የሥነ ምግባርና የሙያ ኃላፊነቶቹን ከተላለፈ አግባብ ባለው ህግ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል” የሚል ድንጋጌ ሰፍሯል።
ነባሩ አዋጅ ከዚህ በተጨማሪም “የአገልግሎቱ ሰራተኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፤ በአገልግሎቱ ወይም በኃላፊው ወይም በሰራተኛው ስም፤ በቃል ወይም በድርጊት ለማታለልና ለማስመሰል የሞከረ ወይም፤ በማታለልና በማስመሰል የማንኛውም ዜጋ ወይም የተቋም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ወይም ዕለታዊ ተግባር ያወከ እንደሆነ፤ አግባብ ባላቸው የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች መሰረት ይቀጣል” ሲል ደንግጓል።

ዛሬ ለፓርላማ ባቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ እነዚህን ድንጋጌዎች ተከትሎ ሌላ ንዑስ አንቀጽ እንዲካተት ተደርጓል። አዲሱ ድንጋጌ “የአገልግሎቱ ሰራተኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፤ በስራው አጋጣሚ ወይም በስራ ስምሪቱ ያወቃቸውንና ያገኛቸውን ማናቸውንም መረጃ፣ ሰነድ ወይም ሪከርድ የተደረገ መረጃ ወይም ምንጭ ያለ ዳይሬክተር ጄነራሉ ፍቃድ የገለጸ እንደሆነ፤ አግባብ ባላቸው የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች መሰረት ይቀጣል” ሲል አስቀምጧል።
ይህ ተጨማሪ ድንጋጌ ማካተት ያስፈለገበትን ምክንያት በፓርላማ የመንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ የአዋጁን ማብራሪያ በመንተራስ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጻ አድርገዋል። ድንጋጌው ያስፈለገው “አገልግሎቱን ከደህንነት ስጋት ነጻ ለማድረግ” እንዲሁም “በስራ አጋጣሚ እና በስራ ስምሪት ከተቋሙ የስራ ግንኙነት ያላቸውን የአገልግሎቱ ሰራተኛ ያልሆኑ ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ” መሆኑን የፓርላማ የመንግስት ተጠሪው ተናግረዋል።
ከደህንነት መስሪያ ቤቱ “የመተባበር ግዴታን” አለመወጣትም በተመሳሳይ የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል በማሻሻያ የአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ከደህንነት መስሪያ ቤቱ ጋር “የመተባበር ግዴታን” በተመለከተ እስካሁን ሲሰራበት በቆየው አዋጅ ላይ ሶስት ጉዳዮች የሰፈሩ ሲሆን በማሻሻያው ረቂቅ ላይ አንድ ጉዳይ ተጨምሮበታል።

ተጨማሪው ድንጋጌ “ማንኛውም ሰው [ከደህንነት መስሪያ ቤቱ] የተሰጠውን መረጃ መጠቀምና ስራ ላይ ማዋል አለበት” የሚል ነው። ይህን ግዴታውን “ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት፤ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ያልተወጣ ማንኛውም ሰው አግባብ ባለው የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች መሰረት ይቀጣል” ሲል የአዋጅ ማሻሻያው አስፍሯል።
የእዚህ ተጨማሪ ድንጋጌ አስፈላጊነት በተዳሰሰበት የአዋጅ ማሻሻያ ማብራሪያ ላይ፤ “የመረጃ እና ደህንንት ስራዎች አፈጻጸም ላይ የመተባበር ተግዳሮቶች እንደሚታዩ” ተጠቅሷል። “ስራዎች የሚፈጸሙት በኃላፊዎች መልካም ፈቃደኝነት ወይም ባላቸው ቅርበት” መሆኑን ያመለከተው የአዋጅ ማብራሪያው፤ በየደረጃው ያሉ አካላት ይህን ግዴታቸውን ሳይወጡ ቢቀሩ ተጠያቂ የሚሆኑበት ድንጋጌ እንዲካተት ተደርጓል ብሏል።
የአዋጅ ማሻሻያው በህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲታይ፤ በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ተመርቷል። በዛሬው ስብሰባ ከተገኙ የፓርላማ አባላት ውስጥ ስምንቱ ቋሚ ኮሚቴው የአዋጅ ማሻሻያውን ሲመለከት ሊመረምራቸው ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች በማንሳት አስተያየት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)