የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የአዋጅ ማሻሻያ ምን ይዟል?

ትላንት ሐሙስ ግንቦት 11፤ 2014 ለፓርላማ የቀረበው የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ የሚያሻሽለው የህግ ረቂቅ፤ በነባሩ አዋጅ ላይ ያሉ ዘጠኝ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን አንድ አዲስ አንቀጽም እንዲጨመር አድርጓል። በአዋጁ የተሻሻሉ እና የተጨመሩ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው።

⚫ የመረጃ ቋት ማቋቋም

➡ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከስራው ጋር በተያያዘ የመረጃ ማጠናቀሪያና ማከማቻ ቋት የማቋቋም እና የማስተዳደር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

➡ ይህን ስልጣን ለደህንነት መስሪያ ቤቱ የሚሰጠው ድንጋጌ የተካተተው፤ የመረጃዎች ሚስጥራዊነት ደረጃ ለመስጠት፤ መረጃዎች በሚስጥር የሚያዙበትን፣ የሚጠበቁበትን፣ ግልጽ ሊደረጉ የሚችሉበትን እንዲሁም ከሚስጥራዊ ደረጃ የሚወጡበትንና የሚወገዱበትን አሰራር ለመዘርጋት እና ከመረጃ እና ደህንነት ተቋማት የሚገኙ መረጃዎች ፍሰትና ስርጭት ማዕከላዊ እንዲሆን በማስፈለጉ መሆኑ በረቂቅ አዋጁ በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።

⚫ የግዢ ስርዓት እና የተቋሙ ገቢ

➡ በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ መሰረት ከመረጃ እና ደህንንት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውንና ለደህንነት ስጋት ምንጭ ይሆናሉ ተብሎ የሚታመንባቸው ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ግዢያቸው ከአንድ አቅራቢ በቀጥታ ወይም ውስን አቅራቢዎችን በማወዳደር ይፈጽማል። ይህ የሆነው የተቋሙ አቅም እና አሰራር ለሌሎች አካላት እንዳይጋለጥ እና ተገማች የሚሆንበትን ሁኔታ እንዳይፈጠር መሆኑ በአዋጅ ማብራሪያው ላይ ተገልጿል።

➡ የደህንነት ተቋሙ በመንግስት ከሚመደብለት ገንዘብ፤ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማስፈቀድ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃ የተለያዩ ንብረቶቹንና የስራ መሳሪያዎቹን በመሸጥ ከሚያገኘው ገቢ እና ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከሚገኘው ገቢ ከሚደርሰው 50 በመቶ ድርሻ በተጨማሪ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያገኘውን ገቢ መጠቀም እንደሚችል በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ተቀምጧል። የማሻሻያ ረቂቁ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ከየትኞቹ አገልግሎቶች ገቢ እንደሚያገኝ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም።

⚫ የተቋሙ ሰራተኞች

➡ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ሰራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሰረት እንደሚመራ ይደነግጋል። የሰራተኞቹ አስተዳደር በደንብ እንዲመራ የተወሰነው በተቋሙ ሰራተኞች የስራ ስምሪት እና የስራ ጠባይ ምክንያት ነው።

➡ የአገልግሎቱ ሰራተኞች ሊያገኙት በሚገባው የደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅም እና የህክምና አገልግሎት ሳቢያ በመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ማስተዳደር “የሚያስቸግር” መሆኑ ሌላው በምክንያትነት የቀረበ ጉዳይ ነው። ይህ የተለየ ደመወዝ እና ጥቅማጥቅም የደህንነት መስሪያ ቤቱን ብቃት ባለው የሰው ኃይል የማደራጀትና ያለውን ሰራተኛ የማቆየት እንዲሁም ሌላውን ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀል የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።

➡ የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁ የደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ወይም በቅስቀሳ ላይ እንዳይሳተፉም ገደብ ጥሏል። 

⚫ የተቋሙ አደረጃጀት

➡ በአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁ ድንጋጌ መሰረት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ ዳይሬክተር ጄነራል እና ምክትል ዳይሬክተር ጄነራሎች ይኖሩታል። በነባሩ አዋጅ ላይ የመረጃ፣ ደህንነት እና የድጋፍ ሰጪ አካላት እንደሚኖሩት የሚደነግጉት ንዑስ አንቀጾች በማሻሻያ ረቂቁ ተሰርዘዋል። የአዋጅ ማሻሻያው የምክትል ዳይሬክተር ጄነራሎችን ብዛት እና የስራ ኃላፊነትን አላስቀመጠም።

➡ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሁለት የፌደራል መስሪያ ቤቶችን የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት እንደተሰጠው በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ሰፍሯል። መስሪያ ቤቱ የሚያስተባብረው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎትን ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)