በሃሚድ አወል
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ መስከረም አበራ ላይ የ13 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 16 የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው፤ ፖሊስ በተጠርጣሪዋ ላይ እያካሄደው ያለው ምርመራ “ጅምር ስለሆነ እና ብዙ የሚሰሩ ስራዎች” የሚቀሩ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ገልጿል። ።
“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዮቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው ከሶስት ቀናት በፊት ቅዳሜ ግንቦት 13፤ 2014 ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበችው ደግሞ በትላንትናው ዕለት ነበር። በትላንትናው የችሎት ውሎ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን በጹሁፍ ባስገባው ማመልከቻ ጠይቋል።
መርማሪ ፖሊስ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀዱለት ፍርድ ቤቱን የጠየቀው፤ የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ የተጠርጣሪዋን ግብረ አበሮች ለመያዝ እና ከጋዜጠኛዋ የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን የምርመራ ውጤት ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ለመጠባበቅ በሚል እንደሆነ የጋዜጠኛዋ ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የጋዜጠኛዋ ጠበቆች፤ “ፖሊስ አከናውናቸዋለሁ ላላቸው ስራዎች መስከረምን በእስር ለማቆየት ህጋዊ ምክንያት አይደሉም” ሲሉ በትላንትናው የችሎት ውሎ መከራከራቸውን አቶ ሔኖክ አስረድተዋል።
ጠበቆቹ ከዚህም ባሻገር ደንበኛቸው ፈጽማዋለች በሚል በመርማሪ ፖሊስ ለቀረበው ገለጻ መከራከሪያቸውን ለፍርድ ቤቱ ማሰማታቸውንም አክለዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ በትላንቱ የችሎት ውሎ፤ ጋዜጠኛዋን የጠረጠራት ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስታውቆ ነበር።
ፖሊስ “ጋዜጠኛዋ የአማራ ክልል ከፌደራል መንግስቱ እንዲነጠል እና ፋኖ እና የፌደራል መንግስቱ እንዲጋጩ በመገናኛ ብዙሃን ስትቀስቅስ ነበር” ማለቱን አቶ ሔኖክ ገልጸዋል። የጋዜጠኛዋ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ደንበኛችው ወንጀል ፈጽማለች የተባለው በመገናኛ ብዙሃን መሆኑን ጠቅሰው ስለሆነም ጉዳዩ መታየት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ሊሆን እንደሚገባ ተከራክረዋል።
በመጋቢት 2013 ዓ.ም. የጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፤ “በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፤ በወንጀል ስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ህግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት” ሲል ይደነግጋል። ይህንን ድንጋጌ የጠቀሱት ጠበቆች፤ ደንበኛቸው በቀጥታ ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሚገባ በመግለጽ ከእስር እንድትለቀቅ ጠይቀዋል።
የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዛሬ ውሎው፤ “ጋዜጠኛዋ የተጠረጠረችው ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት በመሆኑ ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን ህግ ሳይሆን በመደበኛው ህግ ነው መታየት ያለበት” ሲል የጠበቆችን መከራከሪያ ውድቅ አድርጎታል። ፖሊስ ያቀረበውን ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን በተመለከተ ደግሞ “ምርመራው ጅምር ስለሆነ ብዙ የሚሰሩ ስራዎች ስላሉ ጊዜ መስጠቱን አምነንበታል” ሲል ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም መሰረት ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ፍርድ ቤቱ አንድ ቀን ብቻ በማሳነስ 13 የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የምርመራ ውጤት ለማድመጥም ለግንቦት 29፤ 2014 ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። ጋዜጠኛ መስከረም አበራ በትላንትናውም ሆነ በዛሬው የችሎት ውሎ በአካል ተገኝታ የፍርድ ቤት ሂደቱን ተከታትላለች።
ጋዜጠኛ መስከረም ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 13 ለስልጠና ከሄደችበት ከባህር ዳር ከተማ ስትመለስ በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጣቢያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ወደሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዷን ባለቤቷ አቶ ፍጹም ገብረ ሚካኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቤተሰቦቿ እና ጠበቆቿ ከእሁድ ጀምሮ ተጠርጣሪዋን መጎብኘት እንደተፈቀደላቸውም አክለዋል።
መስከረም አበራ “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘውን የራሷን የዩቲዩብ ቻናል ከማቋቋሟ በፊት፤ “አባይ ሚዲያ” እና “የኔታ ቲዩብ” በተባሉት የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ በወቅታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየቶቿን ስታቀርብ ቆይታለች። በታሪክ የመጀመሪያ እንዲሁም በስርዓተ ፆታ ጥናት የሁለተኛ ዲግሪ ያላት መስከረም፤ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ከመግባቷ በፊት በሐዋሳ መምህራን ኮሌጅ እና በዲላ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ እና ስነ ዜጋ አስተምራለች።
መስከረም የመምህርነት ስራዋን ሙሉ በሙሉ በመተው ወደ ጋዜጠኝነቱ ፊቷን ከማዞሯ በፊት፤ “ስለ ስልጣኔ” እና “የዘውግ ፖለቲካ ስረ መሠረቶች” የተሰኙ ሁለት መጽሐፍትንም ለንባብ አብቅታለች። የ37 ዓመቷ መስከረም ለእስር የተዳረገችው፤ የሰባት ወር እድሜ ያለው ህጻን ልጇን በቤት ትታ መሆኑን የሚያነሱት ቤተሰቦቿ ከእስር ተለቅቃ ጉዳይዋን በውጭ እንድትከታተል ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)