በኢትዮጵያ በማዕድን ፍለጋ እና ልማት ላይ ተሰማርተው የነበሩ 55 ኩባንያዎች ፈቃድ ተቋረጠ

በኢትዮጵያ በወርቅ፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እና ልማት ተሰማርተው የነበሩ 55 ኩባንያዎች ፈቃድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት እንዲቋረጥ መደረጉን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ተስፋ በጣለባቸው በሁለቱ ዘርፎች ፈቃድ ያላቸው ሁለት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።   

የኩባንያዎቹ ፈቃድ መቋረጥ ይፋ የተደረገው፤ የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ የመስሪያ ቤታቸውን ያለፉትን ዘጠኝ ወራት የስራ ክንውን ሪፖርት ዛሬ ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ነው። አቶ ታከለ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በሪፖርቱ በተጠቀሰው ጊዜ ብቻ 52 የወርቅ እና የሌሎች ማዕድናት ፈቃድ ተቋርጧል። ለተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እና ልማት የተሰጡ ሶስት ፈቃዶችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲቋረጡ መደረጉንም አክለዋል።

ፎቶ፦ የማዕድን ሚኒስቴር

ፈቃዳቸው ከተቋረጠባቸው ኩባንያዎች መካከል በሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ እና ልማት ፈቃድ የነበረው የብሪታንያ ኩባንያ እንደሚገኝበት በሚኒስቴሩ ሪፖርቱ ተጠቅሷል። “ኒውኤጅ” የተባለው ይኸው ኩባንያ ፈቃዱን ያጣው “ግዴታውን መወጣት ባለመቻሉ” መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር በሪፖርቱ አስታውቋል። 

ኩባንያው “ለበርካታ ጊዜያት ማራዘሚያ ቢሰጠውም መስራት ሳይችል የስምምነት ጊዜው በመጠናቀቁ ስምምነቱ እንዲቋረጥ ተደርጓል” ሲል ሚኒስቴሩ ከእርምጃው ጀርባ ያለውን ምክንያት አብራርቷል። “ኒውኤጅ” የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በኦጋዴን አካባቢ የነዳጅ እና ጋዝ ክምችት ማግኘቱን አስታውቆ ነበር። ክምችቱ የተገኘበት ቦታ፤ ካሉብ እና ሂላላ ከተባሉት የነዳጅ ማውጪያ ስፍራዎች አቅራቢያ መሆኑንም በወቅቱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። 

እንደ ብሪታንያው ኩባንያው ሁሉ፤ “ጂፒቢ” የተባለው የሩሲያ ኩባንያም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፍቃዱ መቋረጡ በማዕድን ሚኒስቴር ሪፖርት ተመላክቷል። በራሱ ፈቃድ ስምምነቱን ማቋረጡ የተነገረለት “ጂፒቢ”፤ እርምጃውን የወሰደው “የፋይናንስ ውስንነት ስላጋጠመው” እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል። 

“ጂፒቢ ግሎባል ሪሶርስስ” የተባለው የሩሲያ ኩባንያ በአፋር ሸለቆ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ለመፈለግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት የተፈራረመው ከስምንት አመታት በፊት ነበር። በኢትዮጵያ አራት የተፈጥሮ ጋዝ እና ነዳጅ ፍለጋ ፈቃድ ያሉት “ፖሊጂሲኤል” የተባለው የቻይና ኩባንያ ጉዳይም በማዕድን ሚኒስቴር የዘጠኝ ወር የስራ ክንውን ሪፖርት ተነስቷል። 

ከፍለጋ ፍቃዶቹ በተጨማሪ አንድ የተፈጥሮ ጋዝ ልማት እና ምርት ፈቃድ ያለው “ፖሊጂሲኤል”፤ “ፈቃድ ወስዶ በሰራባቸው ዘጠኝ ዓመታት የሚጠበቅበትን ስራ ያላከናወነ መሆኑ በግምገማ ታውቋል” ሲል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት አትቷል። “በዚህም በሃገር ደረጃ የተያዘውና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት የተፈጥሮ ጋዝ ልማት በተያዘለት ጊዜ ዕውን አንዳይሆን አድርጓል” ሲል ሪፖርቱ ተችቷል።

አቶ ታከለ ኩባንያውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ፖሊጂሲኤል “መንግሥት እና ሕዝብ ከፍተኛ ተስፋ የጣለበትን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት በተያዘለት ጊዜ እውን እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥሯል” ብለዋል። ኩባንያው “እስከ በጀት አመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ያለበትን የፋይናንስ እና የቴክኒክ አቅም ውስንነት ካላሟላ ሥምምነቱ የሚቋረጥ ስለመሆኑ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ” እንደተሰጠውም ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።

ፎቶ፦ የማዕድን ሚኒስቴር

የማዕድን ሚኒስቴር የፈቃድ ማቋረጥ እና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የመስጠት እርምጃ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 439 ሚሊዮን ዶላር ያገኝችበትን የወርቅ ምርት ዘርፍን ይጨምራል። “ከፊ ሚኒራልስ” የተባለው የብሪታኒያ ኩባንያ በምስራቅ ወለጋ “ቱሉ ካፒ” በተባለው አካባቢ የወርቅ ምርት ፈቃድ ከተሰጠው ስምንት አመታት እንደተቆጠረ ለተወካዮች ምክር ቤት የገለጹት አቶ ታከለ፤ ሆኖም ኩባንያው “ውል በገባው መሰረት የምርት ሥራ አላከናወነም” ብለዋል። 

ኩባንያው “በገባው የውል ስምምነት መሰረት በተለያዩ ጊዜያት ስራውን እንዲያከናውን ክትትል እና ድጋፍ ሲደረግለት” እንደቆየ የጠቀሱት የማዕድን ሚኒስትሩ፤ እንዲያም ቢሆን “የሚጠበቀው ውጤት ሊመዘገብ አልተቻለም” ሲሉ ሂደቱን ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት አብራርተዋል። ይህንን ተንተርሶም መስሪያ ቤታቸው ለኩባንያው “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” መስጠቱንም አስረድተዋል። ማስጠንቀቂያው፤ የብሪታንያው ኩባንያው ከየካቲት እስከ ሐምሌ 2014 ባሉት ጊዜያት “ለስራው የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ማረጋገጫ” እንዲያቀርብ የሚያዝዝ መሆኑን አክለዋል። 

ካርታ፦ ከፊ ሚኒራልስ ኢትዮጵያ

የማዕድን ሚኒስትሩ የስራ አፈጻጸማቸውን ከዘረዘሯቸው ከእነዚህ ኩባንያዎች በተጨማሪ “የተወካዮች ምክር ቤት ክትትል እና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ያሏቸውን ሶስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሁኔታ በሪፖርታቸው አንስተዋል። ሶስቱ ኩባንያዎች በአፋር ክልል በሚገኘው ዳሎል አካባቢ የፖታሽ ማዕድን ለማልማት ፈቃድ የተሰጣቸው ናቸው። 

“ሚራክል”፣ “ያራ ዳሎል” እና “ሰርከም ሚኒራልስ” የተባሉት እነኚህ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፤ በመሰረተ ልማት እና የጸጥታ ችግር ምክንያት ስራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ አለመሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር ሪፖርት አመልክቷል። ኩባንያዎቹ ከእነዚህ ተግዳሮቶች ተላቅቀው ስራቸውን እንዲያከናወኑ “ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ ድጋፍ ይፈልጋሉ” ሲሉ አቶ ታከለ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)