የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በቅርቡ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞችን በአፋጣኝ እንዲፈቱ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) ጥሪ አቀረበ። ባለስልጣናቱ የፕሬስ አባላትን ከማዋከብ እንዲታቀቡም ተቋሙ ጠይቋል።
መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገው ሲፒጄ ትላንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ከግንቦት 11፤ 2014 ጀምሮ በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ 11 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞችን መታሰራቸውን አስታውቋል። ጋዜጠኞቹ እና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞቹ የታሰሩት የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት “ህግ ማስከበር” ብለው በሚጠሩት እርምጃ መሆኑንም ተቋሙ ጠቅሷል።

እርምጃው ከተወሰደባቸው መካከል “አሻራ ሚዲያ” የተባለው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን እንደሚገኝበት በሲፒጄ መግለጫ ተመላክቷል። የአማራ ክልል ፖሊስ በባህር ዳር ከተማ የሚገኘውን የ“አሻራ ሚዲያ” ቢሮ በበረበሩበት ዕለት አምስት ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የድርጅቱ ዳይሬክተር ኤልያስ ደባሱ ለሲፒጄ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ግንቦት 11፤ 2014 በተካሄደው ብርበራ ወቅት በፖሊስ የተያዙት ጋሻዬ ንጉሴ፣ ጌትነት ያለው እና ሐብታሙ መለሰ የተባሉ ጋዜጠኞች እንዲሁም ዳንኤል መስፍን እና ቀለሙ ገላጋይ የተባሉ የካሜራ ባለሙያዎች እና የቪዲዮ ኤዲተሮች መሆናቸው ሲፒጄ በመግለጫው አስፍሯል። ብሌን ተጫነ የተባለች የ“አሻራ ሚዲያ” ባልደረባ፤ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች በማግስቱ በንፋስ መውጫ ከተማ ወደሚገኝ እስር ቤት ከተወሰዱ በኋላ ከቤተሰባቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ ለሲፒጄ ገልጻለች።
የአማራ ክልል ፖሊስ በተመሳሳይ ቀን በዚያው በባህር ዳር የሚገኘውን “ንስር ኢንተርናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” በተባለ የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን ላይ ብርበራ ካካሄደ በኋላ ሶስት የድርጅቱን ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሲፒጄ በትላንቱ መግለጫው አመልክቷል። ሌላ አራተኛ የተቋሙ ባልደረባ በማግስቱ ግንቦት 12 ቀን በቁጥጥር ሥር እንደዋለም ዓለም አቀፉ ተቋም አስታውቋል።

ከታሰሩት የንስር መገናኛ ብዙኃን ባልደረቦች ውስጥ ሁለቱ በባህር ዳር ከተማ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ከባህር ዳር 185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በንፋስ መውጫ ከተማ ባሉ እስር ቤቶች እንደሚገኙ የሲፒጄ መግለጫ ጠቁሟል። የአማራ ክልል ፖሊስ በ“አሻራ” እና በ“ንስር” የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን ላይ ብርበራ ባደረገበት ዕለት ላፕቶፖች፣ ኮምፒውተሮች፣ ሚሞሪ ካርዶች፣ ሃርድ ዲስኮች እና ሌሎችም ቁሳቁሶችን መውሰዱን የየድርጅቱ ኃላፊዎች ለሲፒጄ ገልጸዋል።
በባህር ዳር ከተማ የተካሄደውን የጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች እስር ተከትሎ በአዲስ አበባም በተከታታይ ቀናት ሁለት የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሲፒጄ በመግለጫው ጠቅሷል። “ገበያኑ” የተሰኘው የመገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ሰሎሞን ሹምዬ ባለፈው ሳምንት አርብ ግንቦት 12 በፖሊስ የተያዘ ሲሆን በማግስቱ ደግሞ “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው መገናኛ ብዙኃን መስራች እና አርታኢ መስከረም አበራ በቁጥጥር ስር መዋሏን ሲፒጄ አስታውቋል።
ሰለሞን ሹምዬ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚገኝ ቤተሰቦቹ እና ጠበቃው ማረጋገጣቸውን ሲፒጄ በመግለጫው አስፍሯል። ሰለሞን በታሰረ በማግስቱ ግንቦት 13፤ 2014 ፍርድ ቤት ቀርቧል።
ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ስትመለስ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንቦት 13 በቁጥጥር ስር የዋለችው መስከረም አበራ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ እንደምትገኝ ባለቤቷ እና ጠበቃዋ መናገራቸውን ሲፒጄ ጠቅሷል። መስከረም ግንቦት 15 ቀን ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን ለግንቦት 29 ተቀጥራለች።
በሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ አንጌላ ኩዊንታል የአስራ አንዱ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች እስር “መንግስት ለፕሬስ ነጻነት እና ዜጎች ከብዙ ነጻ የሚዲያ ምንጮች ላላቸው መረጃ የማግኘት መብት ክብር እንደሌለው በድጋሚ ያሳየ ነው” ሲሉ ነቅፈዋል። “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሁሉንም ያለ ክስ በአፋጣኝ ሊፈቱ ይገባል” ያሉት አስተባባሪዋ፤ ጋዜጠኞች በዘፈቀደ የመታሰር፣ የመጨቆን እና የሳንሱር ስጋት ሳይኖርባቸው መዘገባቸውን እንዲያረጋግጡም ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)