የትራንስፖርት ማህበራት ወደ ንግድ ማህበርነት እንዲለወጡ የሚያስገድድ አዋጅ በፓርላማ ጸደቀ

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ማህበራት ወደ ንግድ ማህበርነት እንዲለወጡ የሚያስገድድ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። አዲሱ የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ ማህበራቱ ራሳቸውን በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ንግድ ድርጅትነት እንዲለውጡ እና የኦፕሬተርነት የብቃት ማረጋገጫ ስልጣን ካለው አካል እንዲወስዱ ያስገድዳል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ250 ገደማ የሚሆኑ የትራንስፖርት ማህበራት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። የትራንስፖርት ማህበራቱ የህዝብ ማመለሻ እና የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶችን በአባልነት የሚያቅፉ ናቸው። እነዚህ ማህበራት ህጋዊ ዕውቅና አግኝተው የተመዘገቡት ከ17 ዓመታት በፊት በወጣው የትራንስፖርት አዋጅ አማካኝነት ነበር። 

ይህንን ድንጋጌ የሚተካው እና ባለፈው ጥር ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፓርላማ የቀረበው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ፤ የትራንስፖርት ማህበራት በንግድ ተቋምነት እንዲደራጁ ግዴታ ጥሎባቸዋል። ማህበራቱ በአዋጅ የተጣለባቸውን ይህን ግዴታ፤ ድንጋጌው በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ዕለት ጀምሮ ባሉት ዘጠኝ ወራት መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።

የትራንስፖርት ማህበራቱ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ወደ ንግድ ማህበርነት ካልተለወጡ ምዝገባቸው እንደተሰረዘ ተቆጥሮ ህጋዊ ሰውነት እንደማይኖራቸው ዛሬ በፓርላማ በጸደቀው አዋጅ ላይ ሰፍሯል። የትራንስፖርት ማህበራቱ በአዋጁ መሰረት በአዲስ መልክ ሲደራጁ፤ ቀድሞ የነበራቸውን ንብረት በንግድ አግባብ ወደሚለወጡበት ማህበር ማስተላለፍ እንደሚችሉም በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።

ይህን አዋጅ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ የተገኙ 235 የፓርላማ አባላትን ድጋፍ በማግኘቱ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። ሶስት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ድምጽ ተዐቅቦን ያስተናግደው ይህ አዋጅ፤ ከትራንስፖርት ማህበራት  ተቃውሞዎች ቀርበውበት ነበር። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው መጋቢት ወር ባካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ላይም ይኸው ተቃውሞ ጎልቶ ተደምጧል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ማህበር ተወካዮች፤ በንግድ መደራጀት ንብረቶቹን የንግድ ድርጅቱ ስለሚያደርግ የተሸከርካሪ ባለንብረቶችን “ንብረት አልባ ያደርጋል” የሚል ስጋታቸውን በተደጋጋሚ አንጸባርቀዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዱ የነበሩት የተባበሩት ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተወልደብርሃን አለማየሁ፤ “የተሽከርካሪ ባለንብረቶችን በንግድ ማህበርነት ተደራጁ ብሎ ማስገደዱ አግባብ አይደለም” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር። ለአርባ አምስት ዓመታት ያህል በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የቆዩት ስራ አስኪያጁ፤ የትራንስፖርት ባለንብረቶች በማህበር መደራጀት የመረጡበትን ምክንያት ለውይይቱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል።

“በንግድ መደራጀት ድሮም አለ፤ ቢመርጣቸው ቀድሞውንም ለምን በእነዚህ አልተደራጀም? ማህበር ተገዶ አይደለም የገባው፤ ማህበር ስለሱ ሆኖ ስለሚከራከርለት ነው” ሲሉ አቶ ተወልደብርሃን አሁን በስራ ላይ ያለው አደረጃጀት የተመረጠበትን ምክንያት አብራርተዋል። በአዲሱ አዋጅ የተቀመጠው ድንጋጌ ተግባራዊ ከሆነ “የትራንስፖርት ዘርፉ ችግር ውስጥ ይገባል። ወደ ስራ ገብቶ ውጤታማ ይሆናል ብዬ አላስብም” ሲሉም ስራ አስኪያጁ በወቅቱ አቋማቸውን አሳውቀው ነበር።

የዩናይትድ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ወልደስላሴም በተመሳሳይ “መሬት ወርዶ ሲሰራ በጣም ያስቸግራል ብዬ ነው የማስበው” ሲሉ በውይይቱ ላይ ስጋታቸውን ገልጸው ነበር። የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በመጋቢቱ ውይይት ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ የትራንስፖርት ማህበራቱ በንግድ መደራጀት ለመንግስት ገቢ ከማስገኘት ባለፈ “አሁን አስተማማኝ ያልሆነውን የአሽከርካሪዎች ስራ secure  ያደርገዋል” ሲሉ ፋይዳውን አስረድተዋል።  

በተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ በመንገድ ትራንስፖርት አዋጁ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል | ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ተቃውሞችን ያስተናገደው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ከመጽደቁ በፊትም ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ተነስተውበት ነበር። እታፈራሁ ሞታ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ “የትራንስፖርት ማህበራቱ ቶሎ ወደ ስራ እንዲገቡ ስድስት ወር በቂ አይደለም ወይ?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል። 

በተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ለኮሚቴው በተመራው ረቂቅ አዋጅ ላይ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ስድስት ወር መሆኑን አስታውሰዋል። ሆኖም ቋሚ ኮሚቴው ከባለድርሻ አካላት ጋር ህዝባዊ የውይይት መድረክ ካከናወነ በኋላ የጊዜ ገደቡ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስረድተዋል።

“አሁን ያሉ ማህበራት ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው ማህበራቸውን ማፍረስ እንዲሁም በአዲስ የንግድ ማህበርነት ለመደራጀት ንግድ ፍቃድ ማውጣት አለባቸው” የሚሉት ሸዊት ይህን ለማድረግ ስድስት ወር በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም  “በነባሩ ማህበር ያሉ ንብረቶችን ኦዲት አስደርጎ አዲስ ለሚመሰረት የንግድ ድርጅት ማሻገር ጊዜ ይወስዳል” የሚል አስተያየት ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ውይይት መነሳቱን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የጊዜ ገደቡ እነዚህን አስተያየቶች “ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት” መስተካከሉን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)