ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ያየሰው ሽመልስ በጸጥታ ኃይሎች ተያዙ

በተስፋለም ወልደየስ

የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጄንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ እና “ኢትዮ ፎረም” የተሰኘው የዩ ቲዮብ መገናኛ ብዙኃን አዘጋጅ የነበረው ያየሰው ሽመልስ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 18፤ 2014 በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው መወሰዳቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ። ሁለቱም ጋዜጠኞች በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ወደሚገኝበት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል ተብሏል። 

ተመስገን ደሳለኝ የሲቪል ልብስ በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች የተያዘው በአዲስ አበባ አድዋ ድልድይ አካባቢ ወደሚገኘው ቢሮው እየገባ በነበረበት ወቅት እንደሆነ በአካባቢው የነበሩ እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ጋዜጠኛ ተመስገን ሊይዙት የመጡትን የጸጥታ ኃይሎች “መጥሪያ ይዛችኋል?” እያለ ሲጠይቃቸው እንደነበር መስማታቸውን የጠቀሱት እማኞቹ፤ የፍርድ ቤት መጥሪያውን ካላሳዩት አብሯቸው እንደማይሄድ መናገሩንም አክለዋል።

የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ በስተመጨረሻ ጠመንጃ ያነገቱ የጸጥታ ኃይሎች በተሳፈሩበት መኪና ተጭኖ መወሰዱን ባልደረቦቹ ገልጸዋል። ተመስገን ከዚህ ቀደም ታስሮ ወደነበረበት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሄዱት ቤተሰቦቹ፤ በመኪና ተጭኖ ለፍተሻ ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲወሰድ ተመልክተናል ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ በለበሱ አራት ፖሊሶች እና ሁለት የሲቪል ልብስ ያደረጉ ግለሰቦች በተመስገን መኖሪያ ቤት ካደረጉት ብርበራ በኋላ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መውሰዳቸውን ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። አንድ ሰዓት ከአርባ ደቂቃ ገደማ በፈጀው በዚሁ ብርበራ የቆዩ የ“ፍትሕ” መጽሔቶች፣ ሃርድ ዲስኮች፣ ፍላሽ ዲስኮች፣ ኒከን ካሜራ፣ የተበላሸ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ተመስገን ሃሳቡን ያሰፈረባቸው በርካታ ወረቀቶች በጸጥታ ኃይሎች መወሰዱን ታሪኩ ዘርዝሯል።

ተመስገን ደሳለኝ ከብርበራው መጠናቀቅ በኋላ በፖሊሶች ታጅቦ በመኪና መወሰዱንም ታናሽ ወንድሙ ጠቁሟል። የጋዜጠኛው ቤተሰቦች ማምሻውን አልባሳት እና ምግብ ይዘው ቀድሞ ወደታሰረበት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ለመስጠት ሲሞክሩ “እዚህ የለም” መባላቸውንም ጨምሮ ገልጿል። 

እንደ ተመስገን ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች የተያዘው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስም፤ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን መስማታቸውን ጠበቃው አቶ ታደለ ገብረመድህን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ጋዜጠኛ ያየሰው በጸጥታ ኃይሎች የተያዘው ዛሬ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ በአዲስ አበባ የካ አባዶ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ እንደነበር ጠበቃው ገልጸዋል።

በአካባቢ የነበሩ የዓይን እማኞችን የጠቀሱት ጠበቃው፤ ያየሰው መጀመሪያ ወደ የካ አባዶ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰደ በኋላ ለትንሽ ጊዜ በዚያው ቆይቷል። ጋዜጠኛው ከቆይታ በኋላ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን የሰሙት አቶ ታደለ፤ ከሰዓቱን ወደዚያው ቢያቀኑም በአካል ሳያገኙት ቀርተዋል። እርሳቸው በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በነበሩበት ወቅት በያየሰው መኖሪያ ቤት የጸጥታ ኃይሎች ብርበራ ሲያደርጉ እንደነበር እና ደንበኛቸውም በቦታው ላይ እንደነበር መስማታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)