በሃሚድ አወል
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ላይ የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ያየሰው የተጠረጠረው “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” መሆኑን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
የጋዜጠኛውን ጉዳይ የያዙት ሁለት መርማሪዎች፤ “ተጠርጣሪው ሆን ብሎ ሁከት እና ብጥብጥ ለማነሳሳት ገንዘብ ተከፍሎት ሃይማኖት ከሃይማኖት እንዲጋጭ፣ በተለያዩ ዩቲዩብ ሚዲያ ንግግር በማድረግና በፌደራል መንግስት ላይ ህዝቡ እንዲያምጽ፣ ሆን ብሎ ሀገር እንዲረበሽ ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ በማሳጣት፣ ሁከት እንዲፈጠር፣ ሀገር እንዳይረጋጋ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነበር” ሲሉ ለችሎቱ የተጠረጠረበትን ወንጀል ዝርዝር አስረድተዋል።
የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ታደለ ገብረመድህን በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ በጽሁፍ ያቀረበው እና መርማሪዎቹም ለችሎቱ ያስረዱት የወንጀል ዝርዝር “ግልጽነት የሚጎድለው ነው፤ መልስ ለመስጠት በሚያስችል መልኩም አልቀረበም” ሲሉ ተከራክረዋል። ጠበቃው አክለውም መርማሪ ፖሊስ “ተጠርጣሪው መቼ፣ ምን ብሎ በመናገር ህዝብን ከመንግስት ጋር ለማጋጨት እንደሞከረ በግልጽ መቀመጥ አለበት” ብለዋል፡፡
መርማሪዎቹ በበኩላቸው ጋዜጠኛው ወንጀሉን ፈጸመባቸው ያሏቸው “አሁን መግለጽ አስፈላጊ ያልሆኑ ብዙ የሚዲያ ተቋማት አሉ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። መርማሪዎች የሚዲያ ተቋማቱን “መግለጽ አስፈላጊ አይደለም” ቢሉም ያየሰው አዘጋጅ የነበረበትን “ኢትዮ ፎረም” የተሰኘውን የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን ግን በስም ጠቅሰዋል።
በሀገሪቱ ላይ “የሚዲያ እና የኢኮኖሚ ጦርነት” ታውጇል ያሉት መርማሪ ፖሊሶች “የሚዲያ ጦርነቱን ይመራል ብለን የምናስበው ተጠርጣሪው ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። ከመርማሪዎቹ ውስጥ አንዱ “የሚዲያ ጦርነቱን የሚመራ የተደራጀ ስውር ቡድን አለ። በስውር የተደራጀው ኃይል ይኼ ተጠርጣሪ ያለበት ኃይል ነው” ሲሉ አክለዋል።
“የሚዲያ ጦርነት አሁን ገና መስማታችን ነው” ያሉት ጠበቃ ታደለ፤ ደንበኛቸው “በዘፈቀደ እንደተያዙ የሚያሳይ የምርመራ ሂደት ነው” ሲሉ ጋዜጠኛ ያየሰው በዋስትና እንዲፈታ ጠይቀዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ወክለው የመጡት መርማሪዎች ጋዜጠኛው በዋስትና ከእስር ከወጣ “ምስክሮችን ሊያባብልብን ይችላል” ሲሉ ጥያቄውን ተቃውመዋል። በጋዜጠኛው ላይ ምርመራ ለማካሄድም 14 ቀናትን እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል።
ፖሊስ በጋዜጠኛው ላይ የምርመራ ቀናት ለመጠየቅ አምስት ምክንያቶችን አቅርቧል። የመጀመሪያው ምክንያት የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ተጠርጣሪውን በምስክሮች በማስመረጥ የምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ለምርመራ ጊዜ መጠየቂያነት የቀረቡ ሁለት ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሌሎች በመርማሪ ፖሊስ የቀረቡ ምክንያቶች የተጠርጣሪውን “ግብረ አበሮች” ተከታትሎ መያዝ፣ የጋዜጠኛውን ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት መላክ እና ከወንጀሉ ጋር ግንኑነት ያለቸውን ማስረጃዎች ማሰባሰብ የሚሉ ናቸው።
የጋዜጠኛው ጠበቃ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ሳይቀበል የቀረው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ጊዜ በአራት ቀናት አሳንሶ 10 የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ በቀጣዩ ቀጠሮ “የተጠርጣሪ መዝገብ እና የተሰሩ ስራዎች በዝርዝር እንዲቀርቡ” ለመርማሪ ፖሊስ ትዕዛዝ ሰጥቷል።፡
በጽህፈት ቤት በኩል የተካሄደውን የዛሬውን የችሎት ውሎ በአካል ተገኝቶ የተከታተለው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ፤ ለዳኞች ባቀረበው ገለጻ በትላንትናው ዕለት መኖሪያ ቤቱ መበርበሩን ተናግሯል። “ቤቴን በርብረው ያገኙት ነገር በ2008 ዓ.ም. በስሜ የተጻፈ መጽሐፍ ብቻ ነው። በእኔ ላይ ምንም ያገኙት ነገር የለም” ሲልም ገልጿል።
በንግግሩ “እነሱ” እና “መንግስታችው” የሚሉትን ቃላት በተደጋጋሚ ሲጠቀም የነበረው ያየሰው፤ “እኔን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ነው የያዙኝ፤ በየትኛው ጊዜ እና የትኛው ዩቲዩብ ላይ የእነርሱን መንግስት ከህዝብ ጋር ለማጋጨት እንደሞከርኩ አላስቀመጡም” ሲል ለችሎቱ አስረድቷል።
ጋዜጠኛ ያየሰው የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለሶስት ጊዜ ያህል ለእስር ተዳርጓል። ጋዜጠኛው ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረው ከሁለት ዓመት በፊት መጋቢት 2012 ዓ.ም ነበር። ያየሰውን በወቅቱ ለእስር ያበቃው ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ “ሐሰተኛ መረጃ አሰራጭቷል” በሚል ነበር። ጋዜጠኛው በዚህ ውንጀላ ለአንድ ወር ገደማ ያህል በእስር ከቆየ በኋላ በሚያዚያ ወር አጋማሽ 2012 ከእስር ተፈትቷል።
ያየሰው ለሁለተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ነው። ያየሰው እና በወቅቱ አብረውት ታስረው የነበሩ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተጠረጠሩት “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ነበር።
ጋዜጠኛው በአፋር ክልል በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ49 ቀናት ከታሰረ በኋላ በዋስትና ከእስር መውጣቱ ይታወሳል። ያየሰው ለሶስተኛ ጊዜ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋለው ትላንት ሐሙስ ግንቦት 18፤ 2014 ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)