በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኞ ቀጠሮ ተሰጠ

በሃሚድ አወል

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኞ ግንቦት 22፤ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ። ቀጠሮውን የሰጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። 

ተመስገን የተጠረጠረው “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” መሆኑን መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል። ጋዜጠኛው ህዝብ በሀገር መከላከያ እና በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ እና እንዲያምጽ “ገንዘብ ተከፍሎት ተንቀሳቅሷል” ሲልም መርማሪ ፖሊስ ተመስገን ደሳለኝን ወንጅሏል።  

የጋዜጠኛው ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ በበኩላቸው ተፈጸመ የተባለው ወንጀል በመገናኛ ብዙኃን መፈጸሙን እና ደንበኛቸውም ጋዜጠኛ መሆኑን በማንሳት “ክርክሩን በመደበኛው የወንጀል ስነ ስርዓት ማድረግ የህግ ድጋፍ የለውም” ሲሉ ተከራክረዋል። የደንበኛው የዋስትና መብት እንዲከበርም ጠይቀዋል። 

ችሎቱ ከሶስት ቀናት በኋላ በሚኖረው ቀጠሮ ጋዜጠኛው በጠበቃው በኩል ላቀረበው የዋስትና ጥያቄ፤ እንዲሁም መርማሪ ፖሊስ በጠየቀው የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ላይ ብይን ይሰጣል። ዛሬ አርብ ግንቦት 19፤ 2014 በአዳራሽ በተከናወነው የችሎት ውሎ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአካል ተገኝቷል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ዛሬ ከሰዓት ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት፤ በአዲስ አበባ አድዋ ድልድይ አካባቢ በሚገኘው የ“ፍትሕ” መጽሔት ዝግጅት ክፍል ተወስዶ ነበር። በዚያም ከረፋድ አምስት ሰዓት ገደማ አንስቶ ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየ ብርበራ በመርማሪዎች ሲካሄድ ቆይቷል። በብርበራው ማጠናቀቂያ ላይም ፖሊሶች የ“ፍትሕ” መጽሔት የቆዩ እትሞችን፣ ሃርድ ዲስክ፣ ሲዲዎች፣ በኮምፒውተር እና በእጅ የተጻፈባቸው ወረቀቶችን ለምርመራ በሚል ምክንያት ወስደዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)