በሃሚድ አወል እና በተስፋለም ወልደየስ
“ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መዓዛ መሐመድ ዛሬ ጠዋት በፖሊስ ተይዛ መወሰዷን የስራ ባልደረባዋ እና ጓደኛዋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገረች። የጋዜጠኛዋ እስር በኢትዮጵያ ከሰሞኑ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞችን ቁጥር 19 አድርሶታል።
“ሮሃ ሚዲያ” ጋዜጠኛ ምስራቅ ተፈራ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገረችው፤ ጋዜጠኛ መዓዛ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ በለበሱ ሁለት ፖሊሶች እና የሲቪል ልብስ ባደረጉ ሶስት የጸጥታ ኃይሎች የተያዘችው በአዲስ አበባ ሰሚት ኮንዶሚኒየም ከሚገኘው የእርሷ መኖሪያ ቤት ነው። የጸጥታ ኃይሎቹ መዓዛን ለ“ጥያቄ እንፈልጋታለን” በሚል ምክንያት ቢይዟትም ወዴት እንደሚወስዷት ለመናገር ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ጋዜጠኛዋ አስረድታለች።
መዓዛ እርሷ ቤት ያደረችው ያላጠናቀቁትን ስራ ለመጨረስ እንደነበር የምትናገረው ምስራቅ፤ ጠዋት ሶስት ሰዓት ገደማ የመኖሪያ ቤቷ ሲንኳኳ በከፈተችበት ወቅት ሁለት ፖሊሶችን እና ሌሎቹን የጸጥታ ኃይሎች በበር ላይ ማግኘቷን አስታውቃለች። የፍርድ ቤት መጥሪያ “አልያዙም ነበር” የተባሉት የጸጥታ ኃይሎቹ፤ የመዓዛን አድራሻ እና መታወቂያዋ ላይ ያለውን መረጃዎች ከመዘገቡ በኋላ በያዙት ካሜራ ፎቶ እንዳነሷት ጋዜጠኛ ምስራቅ አብራርታለች።

ከሰሞኑ በርካታ ጋዜጠኞች እየታሰሩ በመሆኑ፤ ፖሊሶቹ መዓዛን ሊይዙ በመጡበት ወቅት “ብዙም አለመደናገጣቸውን” የሮሃ ሚዲያ ባልደረባዋ ምስራቅ ገልጻለች። የፌደራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ ሰዎች ስለነበሩ ቢያንስ “የህግ አካል” የሆኑ ሰዎች ይዘዋት እንደሄዱ ማረጋገጫ እንደሰጣቸውም አክላለች።
ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በአምስት ወራት ውስጥ ለእስር ስትዳረግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ጋዜጠኛዋ ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆየች በኋላ ጥር አጋማሽ ላይ ከእስር ተፈትታለች።
መዓዛ በዚያን ወቅት የታሰረችው በጥቅምት ወር ላይ ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ነበር። ፖሊስ መዓዛን “ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሱ” መልዕክቶችን በማስተላለፍ መጠርጠሯን ቢገልጽም አንድም ጊዜ ችሎት ፊት አለማቅረቡ ይታወሳል።

ትላንት አርብ ግንቦት 19፤ 2014 በቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውም እንዲሁ ከዚህ ቀደም ለእስር ተዳርጎ ነበር። በቃሉ በጥቅምት 2013 በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ከስራ ቦታው ተወስዶ ለ16 ቀናት ከታሰረ በኋላ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቱ ይታወሳል። ጋዜጠኛው በዚያን ወቅት የተጠረጠረው “ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እና የመንግስት ስም በማጥፋት ወንጀል” ነበር።
“አውሎ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን ዋና አዘጋጅ የነበረው በቃሉ ከመጀመሪያው እስሩ ዘጠኝ ወራት በኋላ በድጋሚ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ አይዘነጋም። በቃሉ እና አብረውት ታስረው የነበሩት ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በወቅቱ ተጠረጥረው የነበረው “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ነበር።
ጋዜጠኛ በቃሉ እና አብረውት የነበሩት ሌሎች ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ49 ቀናት ከቆዩ በኋላ በዋስትና ተለቅቀዋል። በቃሉ ከእስር ከተለቀቀ ከወራት በኋላ “አልፋ ቴሌቪዥን” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስርቶ ዜናዎችን እና ውይይቶችን ማቅረብ ጀምሮ ነበር።
ጋዜጠኛው ትላንት አርብ አራት ኪሎ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በፖሊስ ከተወሰደ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኝበት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩን ተረጋግጧል። በቃሉ ከተያዘበት ሰዓት ጀምሮ ከቤተሰብ ጋር አለመገናኘቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል።
በቃሉ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 20፤ 2014 በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በአካል ቀርቧል። ጋዜጠኛው “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” መጠርጠሩን ለችሎት የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ በጋዜጠኛው ላይ ምርመራ ለማድረግ 14 የምርመራ ቀናትን ጠይቋል።
ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመጣው መርማሪ ፖሊስ፤ በቃሉ “በተለያዩ በመንግስት ሚዲያ ቀርቦ ቃለ መጠይቅ በማድረግ መንግስት እንዲጠላ እና ሀይማኖታዊ ግጭት እንዲፈጠር ተንቀሳቅሷል” ብሏል። ፍርድ ቤት ያለ ጠበቃ የቀረበው ጋዜጠኛ በቃሉ በበኩሉ “ስራ እንዳልሰራ ተደርጌያለሁ በመንግስት ሚዲያም ቀርቤ አላውቅም” ብሏል።
በቃሉ በችሎቱ ላይ “ጉዳዩ መታየት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ነው” ሲል የተከራከረ ሲሆን የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለትም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። የጋዜጠኛውን ጉዳይ መርማሪ ፖሊስ “ጋዜጠኛው በዋስትና ከወጣ ይጠፋል። ግብረ አበሮቹንም ያባብላል” በሚል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል።
የጋዜጠኛ በቃሉን ጉዳይ በጽህፈት ቤት በኩል የተመለከተው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ፤ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ቀናት በሁለት ቀንሶ 12 ቀናትን ፈቅዷል። በመጪው ሰኔ 2፤ 2014 በሚኖረው ቀጣይ ቀጠሮም ፖሊስ በተሰጡት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት አንዲያቀርብ በማዘዝ ፍርድ ቤቱ የዛሬውን ውሎውን አጠናቅቋል።
የበቃሉን እና ከትላንት በስቲያ በተመሳሳይ ሁኔታ በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለችውን የ“ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድን አስመልክቶ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው አጭር መግለጫ፤ በቅርቡ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች ቁጥር 18 መድረሱን አስታውቋል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የጋዜጠኞችን እስር “ህገወጥ” ሲሉ ተችተውታል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የቅደመ ክስ እስርን በግልጽ እንደሚከለክል የጠቀሱት ዶ/ር ዳንኤል፤ በዚህ መሰረትም ሁሉም የታሰሩ የመገናኛ ብዙኃን ሊለቀቁ ይገባል ብለዋል። በመጋቢት 2013 ዓ.ም. የጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፤ “በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፤ በወንጀል ስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ህግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት” ሲል ይደነግጋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)