ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድ ከእስር ተለቀቀች

የ“ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድ ዛሬ ረፋዱን ከእስር መለቀቋን የጣቢያው ዋና ዳይሬክተር ለሚ ታዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ጋዜጠኛ ሶቦንቱ የተለቀቀችው በቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

ጋዜጠኛ ሶቦንቱ በፖሊስ ቁጥጥር የዋለችው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ግንቦት 18፤ 2014 አመሻሽ ላይ ከስራ ቦታዋ ስትወጣ መሆኑን በወቅቱ ተገልጾ ነበር። በ“ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” ቴሌቪዥን ጣቢያ ዜና አንባቢ እና የመዝናኝ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነችው ሰቦንቱ በማግስቱ ወደ ቢሾፍቱ ከተማ መወሰዷን የጣቢያው ዋና ዳይሬክተር ተናግረው ነበር። 

ያለፉትን ሶስት ቀናት በእስር ያሳለፈችው ሰቦንቱ፤ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 22 ከጠዋቱ አራት ሰዓት ተኩል ገደማ በዋስ መለቀቋን አቶ ለሚ ገልጸዋል። ጋዜጠኛዋ ከእስር ከተለቀቀች በኋላ በስልክ እንዳነጋገሯት የገለጹት የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ዳይሬክተር፤ የኦሮሚያ ፖሊስ “ስንፈልግሽ ትመጫለሽ” በሚል እንደፈታት  እንደነገረቻቸው አስታውቀዋል። 

የሰቦንቱን ከእስር መለቀቅ የኦሮሚያ ጋዜጠኞች ማህበርም አረጋግጧል። ማህበሩ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው አጭር መረጃ በጋዜጠኛዋ መለቀቅ የተሰማውን ደስታ ገልጾ፤ በጉዳዩ ላይ ትብብር ያደረጉ የኦሮሚያ የጸጥታ አካላትን አመስግኗል። የጋዜጠኞች ማህበሩ ባለፈው አርብ ባወጣው መግለጫ “ባልታወቀ ምክንያት የታሰረችው ጋዜጠኛ በአስቸኳይ እንድትፈታ” መጠየቁ ይታወሳል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)