በጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ ላይ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

በሃሚድ አወል

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከአስር ቀናት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋለው ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ ላይ ሰባት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎው፤ እንደ ጋዜጠኛ ሰለሞን ሁሉ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” በተጠረጠረችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ላይ ተመሳሳይ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። 

“ገበያኑ” የተሰኘው የመገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ሰሎሞን ዛሬ ሰኞ ግንቦት 22 ፍርድ ቤት ፊት የቀረበው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ግንቦት 20 በፌደራል ፖሊስ የተያዘችው መዓዛ በበኩሏ በችሎት ስትገኝ የዛሬው የመጀመሪያዋ ነው። 

የሁለቱን ጋዜጠኞች ጉዳይ በተለያየ መዝገብ የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ በመርማሪ ፖሊሶች እና የተጠርጣሪ ጠበቆች የቀረቡ አስተያየቶችን እና መከራከሪያዎችን አድምጧል። ፍርድ ቤቱ በጠበቆች በኩል የቀረቡትን የዋስትና ጥያቄዎች እና በመርማሪ ፖሊሶች በኩል የቀረቡት የምርመራ ቀናት ይፈቀድልን ጥያቄን ተመልክቶም ብይን ሰጥቷል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የጋዜጠኛ ሰለሞን ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ከመመልከቱ በፊት፤ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት በተሰጠው ዘጠኝ የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት አድምጧል። ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ገለጻ፤ ከተጠርጣሪ እጅ የያዛቸውን የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች “ለሚመለከተው መርማሪ አካል” ልኮ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውቋል። 

ከዚህም በተጨማሪም የተጠርጣሪውን የገንዝብ ዝውውር ለማወቅ ለባንኮች ደብዳቤ መጻፉን እንደዚሁም ጋዜጠኛ ሰለሞን ወንጀሉን ፈጸመ የተባለበት “ገበያኑ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን ህጋዊ ፍቃድ ያለው ስለመሆኑ ለማወቅ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በደብዳቤ መጠየቁንም መርማሪ ፖሊስ ጠቅሷል። ፖሊስ በደብዳቤ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚያገኝ እና ቀሪ ምርመራዎችን ለማከናወን 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ችሎቱን ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ ከሚያጣራቸው ጉዳዮች ውስጥ ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም ለጋዜጠኛ የተናገረው ንግግር በህግ የሚያስጠየቅ መሆን አለመሆኑ ይገኝበታል። ጋዜጠኛ ሰለሞን ተናገረ የተባለው ይኸው ንግግር “መንግስት ህገ መንግስቱን ማስከበር ስላልቻለ እያንዳንዱ ግለሰብ ህጉን ማስከበር አለበት” የሚል መሆኑን ፖሊስ ለችሎቱ ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ሰለሞንን ወክለው በችሎት የተገኙት ሁለት ጠበቆች የደንበኛቸው ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መታየት እንዳለበት በማንሳት ችሎቱ የዋስትና መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ጠይቀዋል። በላይ መሸሻ የተባሉት ጠበቃ “ወደ ፊት ይመጣሉ የሚባሉት ሰነዶች ከመንግስታዊ ተቋማት ስለሚመጡ በተጠርጣሪው ግለሰባዊ አቅም ሊቀየሩ፣ ሊዛቡ እና ሊቀሩ የሚችሉ አይደሉም” ሲሉ ደንበኛቸውን በእስር ለማቆት በቂ ምክንያት አለመሆኑን አንስተው ተከራክረዋል። 

“ሚዲያው ህጋዊ በመንግስት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ነው” ያሉት ሌላኛው ጠበቃ አቶ በፍቃዱ ስዩም፤ ደንበኛቸው አደረጉ የሚባለው ንግግር በድረ ገጽ ላይ የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ የጋዜጠኛ ሰለሞን የዋስትና መብት እንዲጠበቅ አመልክተዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ጋዜጠኛው በዋስ ከወጣ “የምርመራ ስራውን ለማከናውን ስለምንቸገር በእስር ይቆዩ” በሚል ጠበቆቹን ዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል።  

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጠበቆቹን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የሰባት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ በመጪው ግንቦት 29 በሚኖረው ቀጠሮም፤ ፖሊስ “የፋይናንስ ድጋፉ ከማን እንደሚደረግ እና ለምን አላማ እንደሚውል አጣርቶ እንዲያቀርብ” ትዕዛዝ አስተላልፏል። 

“ሻይ ቡና” በተሰኘው የቴሌቭዥን ፕሮግራም ይበልጥ የሚታወቀው ሰለሞን ሹምዬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ግንቦት 12፤ 2014 ነበር። ጋዜጠኛው በፖሊስ የተያዘው፤ የዚያኑ ዕለት ከእርሱ መኖሪያ ቤት ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች የተያዘችው እህቱን ለማስለቀቅ በሄደበት መሆኑን እህቱ ትግስት ሹምዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች።

ጋዜጠኛ ሰለሞን ከተያዘበት ዕለት ጀምሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኝበት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደሚገኝ ትግስት ጨምራ ገልጻለች። በተመሳሳይ መልኩ በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የምትገኘው “ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መዓዛ መሐመድ፤ ከጋዜጠኛ ሰለሞን ጋር አንድ ላይ በመሆን ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርባለች። 

መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኛ መዓዛን የጠረጠራት፤ ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ አጥቶ እንዲያምጽ እና ሀገር እንዳይረጋጋ “ገንዘብ ተከፍሏት ተንቀሳቅሳለች” በሚል ወንጀል እንደሆነ ለፍርድ ቤት አስረድቷል። በጋዜጠኛዋ ላይ የሰው እና ሰነድ መስረጃ ለማሰባሰብ፣ የጋዜጠኛዋን ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ለመላክ እንዲሁም ግብረ አበሮቿን ለመያዝ ፖሊስ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ችሎቱን ጠይቋል።  

ጋዜጠኛዋን ወክለው በችሎት የተገኙት ሶስት ጠበቆች በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት የጸደቀውን የመገናኛ ብዘኃን አዋጅ በማንሳት የጋዜጠኛዋ የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ከጠበቆች ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ ቤተማርያም አለማየሁ “የደንበኛዬ እስር ዓላማው ሞጋች የሆነ ጋዜጠኛ እንዳይኖር ካለም እንዲፈራ እና እንዲጠነቀቅ እና ራሱን ሳንሱር እንዲያደረግ ነው” ሲሉ ከጋዜጠኛዋ እስር ጀርባ አለ ያሉትን ምክንያት ለችሎቱ አስረድተዋል።

መርማሪ ፖሊስ የዘረዘራቸውን ተግባራት ለማከናወን ጋዜጠኛዋን በእስር ማቆየት አስፈላጊ አለመሆኑን ያነሱት ጠበቃ ቤተማርያም፤ ፖሊስ የጠየቀው የምርመራ ጊዜ እንዳይፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ሌላኛው የመዓዛ ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ በተመሳሳይ “ወንጀል ስለመፈጸሙ ለማጣራት እንጂ ተጠርጣሪ ይኼን ወንጀል ፈጽመዋል በሚል አይደለም የጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀ ያለው” ሲሉ ፖሊስ የጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ተቃውመዋል።  

ሶስተኛው ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ በበኩላቸው “ፖሊስ ወደ ፊት መረጃ አሰባስቤ ወንጀል አገኝባቸው እንደሆነ ብሎ ነው ያስራቸው” ሲሉ መዓዛ ወንጀል በመፈጸሟ ምክንያት አለመታሰሯን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። አቶ ሔኖክ “ወንጀል አልተፈጸመም” ለሚለው ክርክራቸው በአስረጂነት ያነሱት፤ ፖሊስ ጋዜጠኛዋ ፈጽማለች ያለውን ወንጀል መቼ እና የት እንዳደረገችው አለመጥቀሱን ነው። 

የመዓዛ ጠበቆች ያነሱትን የዋስትና ጥያቄ የተቃወመው መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኛዋን “በመገናኛ ብዙሃን አይደለም የጠየቅነው በወንጀል ህግ ነው” ሲል ተከራክሯል። ፖሊስ ጋዜጠኛዋ “ጦርነት ቀስቃሽ ንግግሮችን በማህበራዊ ሚዲያ ስታሰራጭ ነበር” ሲል ወንጅሏል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ ምርመራው ጅምር በመሆኑ እና ጋዜጠኛዋ “የገንዘብ ድጋፍ ታገኛለች” መባሉን በምክንያትነት በመጥቀስ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ጊዜ በግማሽ ቀንሶ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ ፖሊስ በተጠርጣሪዋ ላይ የሚያከናውን የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅ ለሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ግንቦት 29፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቷል። ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ለጋዜጠኛዋ ተደረገ የተባለው የገንዝብ ድጋፍ ከማን እንደተደረገ እና ለምን አላማ እንደዋለ አጣርቶ እንዲያቀርብም በፍርድ ቤት ታዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)