ሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በአማራ ክልል አለ ያሉት “አፈና” እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

በሃሚድ አወል

ሶስት ተቃዋሚ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራ ክልል እየተደረገ ነው ያሉት “መንግስታዊ አፈና” እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ። ፓርቲዎቹ በጋራ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 23፤ 2014 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሌላ ውድመት እንዳያደርስ የሰላም አማራጮች ሁሉ እንዲተገበሩም ጠይቀዋል።

የጋራ መግለጫውን የሰጡት እናት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ናቸው። ሶስቱ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመኢአድ ዋና ጽህፈት ቤት የሰጡት መግለጫ ዋነኛ ትኩረቱ መንግስት ከሰሞኑ እያካሄደው የሚገኘው “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ነው።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ጋዜጠኞች፣ ማህበረሰብ አንቂዎች፣ የፋኖ አባላት፣ ምሁራን፣ ተመላሽ የጸጥታ አባላት እና የፖለቲካ አመራር አባላት “በህግ ማስከበር ሰበብ ታፍነዋል” ሲሉ ወንጅለዋል። መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻውን “የማህበረሰቡን ቅስም ለመስበር፣ የኃይል ሚዛንን ለማስጠበቅ፣ መሪ ለማሳጣት እና በዚሁ አጋጣሚ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን፣ የማህበረሰብ አንቂዎችን ከመከላከያና ልዩ ኃይል ተመላሾችን ለማሳደድ እየተጠቀመበት ነው” ሲሉም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ከስሰዋል። 

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የመኢአድ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ “ሰላማዊ የሆኑ ሰዎችን ሰበባ ሰበብ እየፈለጉ ማሰር እና ማፈን ተገቢ አይደለም። በህግ ማስከበር ስም ህገ-ወጥ ስራን መስራት ትክክል አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል። ሶስቱ ፓርቲዎች በጋራ መግለጫቸው ላይ “የታፈኑ” ያሏቸው ግለሰቦች እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ ማህበራዊ አንቂዎች እና ፖለቲከኞች ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

በፓርቲዎቹ  መግለጫ የተነሳው ሌላው ጉዳይ በፋኖ ኃይል ላይ መንግስት እየወሰደ ነው የተባለው እርምጃ ነው። የፋኖ ኃይልን “ሀገር በጭንቅ ጊዜ ‘ድረስልኝ’ ብላ የጠራችው ባለውለታ” ሲሉ የጠሩት ፓርቲዎቹ፤ ስብስቡ “ለሹመት እና ለሽልማት የመጣ ባለመሆኑ መንግስት አጉል ስጋቱን አስወግዶ አካሄዱን እንዲፈትሽ” ይገባል ብለዋል። 

የመኢአድ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት “መንግስት የማይፈልጋቸውን እና ‘ለስልጣኔ ያሰጉኛል’ የሚላቸውን በፋኖነት ስም አሳብቦ፤ ግማሹን መሸለም ግማሹን ማፈን እና ማሰር ተገቢ አይደለም። ይኼ ለማንም አይጠቅምም” ሲሉ የመግለጫውን ሃሳብ አጠናክረዋል። 

ሶስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላው በመግለጫቸው ያነሱት፤ 19 ወራት ያስቆጠረውን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ነው። ፓርቲዎቹ ጦርነቱን በሚመለከት ሁለት ቢሆኖችን (scenario) በመግለጫቸው ያስቀመጡ ሲሆን፤ ቅድሚያ የሰጡት ጦርነቱ በሰላም መቋጫ የሚያገኝበትን መንገድ ነው። ሶስቱ ፓርቲዎቹ ጦርነቱ ካደረሰው ውድመት በላይ ሌላ ውድመትና እልቂት እንዳያደርስ “ያሉት የሰላም አማራጮች ኹሉ እንዲተገበሩ” በመግለጫቸው ጠይቀዋል። 

የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈሥላሴ አያሌው “ኢትዮጵያ ጦርነትን ልታስተናግድ የምትችልበት ኢኮኖሚም ጫንቃም የላትም የሚል ጽኑ እምነት አለን” ብለዋል። ዶ/ር ሰይፈሥላሴ አክለውም “በተቻለ መጠን መውጫ መንገድ ተፈልጎ ጦርነት ሊኖር የማይችልበት መንገድ በየትኛውም ጥግ መፈለግ አለበት” ሲሉ የመግለጫውን ሃሳብ አስተጋብተዋል።

የመኢአዱ አቶ አብርሃም በበኩላቸው “ሰላም ይውረድ ከተባለ፤ ድርድር ይደረግ፣ ውይይት ይካሄድ ከተባለ፤ ሶስታችንም በመጀመሪያ ህወሓት ትጥቅ መፍታት እና ለድርድር በሩን ክፍት ማድረግ አለበት ብለን በጽኑ እናምናለን” ሲሉ የሶስቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቋም አስረድተዋል። 

ሶስቱ ፓርቲዎች ህወሓት የሰላም አማራጮችን ገፍቶ ወደ ጦርነት ከገባ “ተገቢውና የመጨረሻውን ቅጣት ያገኝ ዘንድ” የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ዝግጅት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። የኢህአፓ ሊቀመንበር አቶ ዝናቡ አበራ “የጥቅምት 24 [2013] ‘መብረቃዊ ምት መተናቸዋል’ የሚለው መደገም የለበትም። ከመብረቃዊ ምት በፊት መዘጋጀት አለብን” ብለዋል። ዶ/ር ሰይፈስላሴም “ጦርነቱን ማስቀረት የማይቻል ከሆነ ተገቢውን ዝግጅት አድርጎ ይህን ወራሪ ኃይል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ መስጠት ያስፈልጋል” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። 

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ መንግስት “በየምዕራፉ እያቆመ መቀጠሉ” የጦርነቱን አውዳሚነት “በብዙ መልኩ ጨምሮታል” ሲሉ በመግለጫቸው ተችተዋል። “ዛሬ ላይ የህወሓት የጦርነት ነጋሪት መጎሰም የፌደራል መንግስት በህዳር እና ታህሳስ ወራት ያካሄደውን ዘመቻ መቋጫ ሳያበጅለት ዝርው ሆኖ መተዉ ነው” ሲሉም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት በጦርነቱ ላይ የተከተለውን አካሄድ ነቅፈዋል።  

መኢአድ፣ ኢህአፓ እና እናት ፓርቲ በጋራ ባወጡት የዛሬው መግለጫቸው ሌሎችም ጉዳዮች አንስተዋል። በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት እና በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው የማዳበሪያ ዋጋ በጋራ መግለጫው ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል። ሶስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ እየተስተዋለ ነው ያሉትን “ጠቅላይነትም” በመግለጫቸው ኮንነዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)