የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት በማንኛውም ወገን የሚደረግ “የጦርነት ጉሰማን” እቃወማለሁ አለ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት በየትኛውም ወገን የሚደረግ “የጦርነት ጉሰማን” እንደሚቃወም አስታወቀ። ጥምረቱ በኢትዮጵያ በአዲስ መልክ ያንዣበበው ጦርነት ዳግም እንዳይቀሰቀስ የጠየቀ ሲሆን የፌደራል መንግስት፣ ህወሓት እና “ኦነግ ሸኔ” የሰላም ጥሪን እንዲከተሉም አሳስቧል።

ጥምረቱ ጥያቄውን ያቀረበው ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 24፤ 2014 በአዲስ አበባ ቦሌ ማተሚያ ቤት አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ ነው። በነሐሴ 2013 ዓ.ም የተመሰረተው ይኸው ጥምረት፤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ ሶስት መቶ ገደማ አባላትን በስሩ ያቀፈ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረት በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው በኢትዮጵያ የተከሰተው እና በቅርብ ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል ተብሎ የተፈራው “የእርስ በእርስ ጦርነት” ነው። ጥምረቱ “በሀገራችን ከተከሰቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች አንዱና ዋነኛው” ሲል የገለጸው የሰሜኑ ጦርነት፤ ሀገሪቱን “እጅግ ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል” ብሏል።

“በጦርነቱ ምክንያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ህይወት ተቀጥፏል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። አያሌ ሴቶች፣ ህጻናትና አረጋውያን ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል። በተለይም ሴት እህቶቻችን ጾታዊ ጥቃት [ደርሶባቸዋል]፤ ሰብዓዊ ክብራቸውም ተደፍሯል” ሲል ጥምረቱ ጦርነቱ ያደረሳቸውን ጉዳቶች ዘርዝሯል።  

ጦርነቱ “ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ ስደት እና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት” ማስከተሉን በተጨማሪነት የጠቀሰው ጥምረቱ፤ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል “የጎላ ክፍተት” በመፈጠሩ “የጥቁር ገበያ ህገወጥነት ይበልጥኑ መስፋፋቱን” አመልክቷል። ኢትዮጵያ በቀደመው ጦርነት ከደረሰባት እኒህን መሰል “ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች” እንዲሁም “የስነ ልቦና ስብራቶች” ሳታገግም ለዳግም ግጭት መነሳት በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጥምረቱ አስታውቋል። 

የጥምረቱ ሰብሳቢ እና የተቃዋሚው የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ የመንግስት ጉዳይ ተጠሪ የሆኑት ነቢሃ መሐመድ “አሁን በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ዳግም ወደ ጦርነት እንግባ ካልን ችግራችንን እጥፍ ድርብ ነው የሚያደርግብን” ሲሉ በመግለጫው ላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ አስተጋብተዋል። “በጦርነት የሚገኝ ጥቅም የለም ትርፍም የለም። በጦርነት ምክንያት ወላጆች እናጣለን፣ ህጻናቶችን እናጣለን፣ አረጋውያንን እናጣለን፣ ንብረት እናጣለን። ለዚህ ሁሉ ግንባር ቀደም ተጋላጯ ደግሞ ሴት ናት” ሲሉ ሰላምን በማፈላለግ ረገድ ሴቶች “ግንባር ቀደሞች” ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።   

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ጥምረትም በመግለጫው ላይም ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቋል። “በማንኛውም ሁኔታ ለሚቀሰቀስ የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጎዱት ሴቶች ናቸው። ስለዚህም ያንዣበበው ጦርነት ዳግም እንዳይቀሰቀስ አጥብቀን እንጠይቃለን” ሲል ጥምረቱ አቋሙን በመግለጫው አስፍሯል። 

የጥምረቱ ሰብሳቢ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሰላም ለማውረድ “የኢትዮጵያ መንግስትም፣ በሰሜኑ ክፍል ያለው አካልም፣ ሸኔም ሁሉም ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት መቻል አለባቸው” ብለዋል። “ድርድር ለማድረግም ሰላም ያስፈልጋል” ያሉት ነቢሃ፤ “ሰላም በሁሉም ወገን ፈላጊነት ካልሆነ በስተቀር ውጤታማ ሊሆን አይችልም” ሲሉ አስገንዝበዋል። ለሰላም የሚደረገው ውይይት “የሀገሪቷን ሉዓላዊነት እና መብት ባስጠበቀ እና ባስከበረ መልኩ” የሚካሄድ እና “የዜጎችን ችግር መፍታት” የሚችል መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ጥምረቱ በመግለጫው መንግስት በቀደመው ጦርነት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች “ከአስቸኳይ ሰብዓዊ እና የህይወት አድን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው” ጠይቋል። ሌላው በዛሬው የጥምረቱ መግለጫ የተነሳው ጉዳይ፤ መንግስት ከሰሞኑ እያካሄደው የሚገኘው “የህግ ማስከበር ዘመቻ” እና በሂደቱ ተስተውለዋል የተባሉ ችግሮች ናቸው። 

በቁጥጥር ስር የሚውሉ ግለሰቦች የእስር ሂደት ግልጽ አለመሆን፣ የእስር ሂደቱ የህግ አግባብን በተከተለ መልኩ አለመሆን እና በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች በፍትህ ተቋማት ቀርበው ውሳኔ አለማግኘታቸው በጥምረቱ መግለጫ የተዘረዘሩ “ችግሮች” ናቸው። ለእነዚህ ችግሮች መንግስት የተለያዩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን እና ስራዎችን መስራቱን የጠቀሰው የጥምረቱ መግለጫ፤ “ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንጻር ስንገመግመው ከባህር በጭልፋ የመቅዳት ያህል ነው” ብሏል። 

መንግስት በየትኛውም ሁኔታ ቢሆን “መሰረታዊ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብርም” ጥምረቱ አጥብቆ እንደሚጠይቅ በመግለጫው አስታውቋል። ጥምረቱ ሀገሪቱ ገብታበታለች ካለው “አስከፊ ችግር” እንድትወጣ መንግስት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸውም በመግለጫው አመልክቷል። 

የኢትዮጵያን “ዘመን ተሻጋሪ ችግሮች እና አሁናዊ ምክንያቶች” ለመፍታትም “ሁሉን አካታች ብሔራዊ ምክክር በአፋጣኝ መደረግ አለበት” የሚል እምነት እንዳለውም ጥምረቱ አስታውቋል። ሀገራዊ ምክክሩ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ተፋላሚ አካላት ጭምር ማሳተፍ እንዳለበትም አቋሙን አንጸባርቋል። 

በአሁኑ ወቅት በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታነት እያገለገሉ የሚገኙት የጥምረቱ ሰብሳቢ ነቢሃ መሐመድ “መሳሪያ የታጠቀ አካልም፣ ያልታጠቀ አካልም ጥያቄ ያለው አካልም በዚህ ምክክር ሊገባ ይገባል” ሲሉ የጥምረቱንን አቋም አስተጋብተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)